በአርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ከትናንት ጠዋት ጀምሮ ዳግም በተቀሰቀሰ ጥቃት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ አርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች ከትናንት ጠዋት ጀምሮ ከፍተኛ ጥቃት እና አለመረጋጋት መከሰቱን የአካባቢው ነዋሪዎችና የዓይን እማኞች ገለጹ።
ከሳምንታት በፊት በአካባቢው በደረሰው ጥቃት ሳቢያ የሚዲያ ትኩረት ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም ትናንት ጠዋት 3:00 አካባቢ ጀምሮ በነዋሪዎቹ ላይ አዲስ የተቀናጀ ጥቃት መከፈቱ ታውቋል።
እስካሁን ከተለያዩ የዓይን እማኞች በተገኘው መረጃ መሠረት ግጭቱ መጀመሪያ የተቀሰቀሰው በቢዮ ቀበሌ ሲሆን በአጭር ሰዓታት ውስጥ ወደሚከተሉት አካባቢዎች ተስፋፍቷ።
ጨፌ ቀበሌ፣ እሬቻ ሚካኤል ቀበሌ፣ ሌንጫ ኦዳ፣ በበራርቲ ጫካ ውስጥ፣ ኳስ ድሬ፣ ዲቡ፣ ሱንቴ ማርያምና ወራንቡስ ውስጥ በተከፈተው ተኩስ እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት ቢያንስ የ4 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተረጋግጧል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ጥቃቱ የተሰነዘረው ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ታጣቂዎች ሲሆን ቁጥራቸውም ከሺዎች በላይ ሊገመት እንደሚችልና ዓላማውም በአጭር ቀናት ውስጥ ነዋሪዎችን ሙሉ በሙሉ በማፈናቀልና ንብረት በመዝረፍ ቀውሱን በፍጥነት መቋጨት እንደሆነ ነዋሪዎች በከፍተኛ ስጋት ገልጸዋል።
ከወር በፊት ታሪካዊው የጠለታ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በተቃጠለበት ስፍራ ላይ ወደ 75 የሚጠጉ የፌደራል ፖሊስ አባላት ካምፕ ሰርተው ቢቀመጡም ታጣቂዎቹ የፀጥታ ኃይሉን አልፈው በመሄድ ጥቃት ሲፈጽሙ እንደታዩ ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።
በተጨማሪም ነዋሪዎች የወረዳው አመራሮችና ካድሬዎች ሆን ብለው የነዋሪዎችን መከላከያ መሣሪያዎች በመንጠቅ ሕዝቡን ባዶ እጁን እንዲቀር ማድረጋቸውንና ከታጣቂዎቹ ጋር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ይገልጻሉ።
"ትናንት ምሽት ጀምሮ በአካባቢው ያለው የኔትወርክ አገልግሎት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ ተደርጓል። አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የወረዳው ካድሬዎች በየቀበሌው እየዞሩ የሰዎችን ስልክ በመንጠቅና በማስፈራራት መረጃ ወደ ውጭ እንዳይወጣ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ ነው" በማለት አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለሚድያችን ተናግረዋል።
በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ያለው ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑና የጸጥታ ኃይሎች በአስቸኳይ ጣልቃ ገብተው ጥቃቱን ካላስቆሙ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት እልቂት ሊከሰት እንደሚችል ነዋሪዎች ድምጻቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።
| መሠረት ሚድያ |


