ጭምብል የለበሱ ሰዎች የአዲስ ስታንዳርድ ማኔጂንግ ኤዲተርን ከቢሮው አግተው መውሰዳቸውን ሚድያው አስታወቀ?
(መሠረት ሚድያ)- የአዲስ ስታንዳርድ ሚድያ ባልደረባ የሆነው ጋዜጠኛ ሚሊዮን በየነ ዛሬ ሚያዝያ 7/2018 ዓ.ም ረፋድ 4፡40 ገደማ ማንነታቸው ባልታወቁ እና ሲቪል ልብስ በለበሱ ሰዎች ከመስሪያ ቤቱ ተወስዶ የደረሰበት አለመታወቁን ሚድያው አስታውቋል።
እነዚህ ግለሰቦች ጋዜጠኛ ሚሊዮንን "ለጥያቄ ትፈለጋለህ" ካሉት በኋላ ወደ አልታወቀ ስፍራ ይዘውት ሄደዋል ያለው ሚድያው የደህንነት ካሜራ (CCTV) ምስል እንደሚያሳየው በርካታ ሲቪል ልብስ የለበሱ ግለሰቦች በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ ተከታትለው ወደ ህንጻው ሲገቡ ይታያል ብሏል።
"በምስሉ ቢያንስ ሦስት ባርኔጣና ማስክ ያደረጉ፣ እንዲሁም አንድ ባርኔጣና ማስክ ያላደረገ ግለሰብ በደረጃው አካባቢ ሲንቀሳቀሱና ተግባራቸውን ሲያቀናጁ ታይተዋል። ጥቂት ቆይቶም ጋዜጠኛ ሚሊዮን በቡድኑ ታጅቦ ከቢሮው ሲወጣ ይታያል። ግለሰቦቹ ድርጊቱን በታቀደና በተደራጀ መልኩ ሲፈጽሙ የታየ ሲሆን፣ አንደኛው እየመራ ሌሎቹ ደግሞ ተከታትለውት ከህንጻው በጋራ ወጥተዋል" በማለት ክስተቱን አብራርቶ ፅፏል።
ከድርጊቱ በኋላ የጃኬን አመራሮችና የህግ ቡድን ጋዜጠኛ ሚሊዮን ያለበትን ቦታ ለማወቅ ቀኑን ሙሉ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና የመሪ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ ሚሊዮን በየነ በእነሱ ቁጥጥር ስር አለመሆኑን መናገራቸው ታውቋል።
ጋዜጠኛ ሚሊዮን በየነ ቤተሰቡን የሚያስተዳድር፣ በመንግስትም ሆነ በግል መገናኛ ብዙኃን የብዙ ዓመታት ልምድ ያለው አንጋፋ ጋዜጠኛ ሲሆን ይህ እገታ የተፈጸመው ባለፉት ጥቂት ወራት በአዲስ ስታንዳርድ የዜና ክፍል እና ስራዎች ላይ ተደጋጋሚና እየበረታ የመጣ የጸጥታና የአስተዳደራዊ ጫናዎች ባሉበት ወቅት ነው ተብሏል።
የአዲስ ስታንዳርድ ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር "ይህን አስደንጋጭ ድርጊት አጥብቀን እናወግዛለን" ያለ ሲሆን "ጋዜጠኛ ሚሊዮን በየነ ማንነታቸው ባልታወቁ ግለሰቦች መወሰዱ ተቀባይነት የሌለውና እጅግ አሳሳቢ ነው። በአስቸኳይ እንዲለቀቅ እንጠይቃለን፤ የሚመለከታቸው አካላትም የእሱን ደህንነት ለማረጋገጥና የህግ የበላይነትን ለማስከበር በፍጥነት እንዲንቀሳቀሱ እናሳስባለን"ብሏል።
-መሠረት ሚድያ-


