በደብረ ብርሀን ከተማ ምን እየተካሄደ ነው?
(መሠረት ሚድያ)- በፍጥነት የኢንደስትሪ ከተማ እየሆነች የመጣችው የደብረ ብርሀን ከተማ ከሰሞኑ አንድ እጅግ አሳሳቢ ችግር ገጥሟታል።
በአንፃራዊነት በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት እምብዛም ያልጎዳት ከተማዋ አንጻራዊ ሰላም ያለባት ከተማ ተደርጋም ትወሰዳለች።
ከሰሞኑ ግን ሰላሟ ተናግቷል፣ ነዋሪዎቿም ፍርሀት ገብቷቸዋል።
ነገሩ እንዲህ ነው: ሰሞኑን ያለማቋረጥ ነጋዴዎች እና ብር ያላቸው ሰዎች እየታገቱ እስከ 5 ሚልዮን ብር አስገቡ እየተባሉ ይገኛሉ። መሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ እንደሚጠቆመው ሰዎች አላቸው ተብሎ በሚገመተው ልክ ከ700,000 ሺህ ብር እስከ 5,000,000 ብር እየከፈሉ ይገኛሉ።
ይሁንና እነዚህ ሰዎች ተሳክቶላቸው ከፍለው ተለቀው ነገሩ ይቆማል ተብሎ ቢታሰብም በየቀኑ የባንክ አካውንታቸው እና ያላቸው ሀብት በተደራጀ መልኩ እየታየ ድጋሜ እየታገቱ ይገኛሉ።
"በዚህ ሁኔታ ያለህን ሃብት በሙሉ ወደ እነሱ አካውንት ትገለብጣለህ፣ እሚገርመው ለማን እንደሚላክ እንኳን ይታወቃል። የሚያሳዝነው ከእገታ ተመልሰህ ይህን አካውንት በፍርድ ቤት ማሳገድ እንዳትችል ሁሉ ያደርጉሃል" ያሉን የገፈቱ ቀማሽ የሆኑ አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የከተማው ነዋሪዎች ናቸው።
"አጋቾቹ የመንግስት አካላት ጭምር መሆናቸው ይበልጥ ያስፈራል" የሚሉት ነዋሪዎች "ሰላም አስከብር ተብሎ የተላከ ሃይል አይን አውጥቶ በጠራራ ጸሃይ ዘራፊ ሁኖ ሲመጣ ምን ይባላል?" ብለው ይጠይቃሉ።
ሚድያችን ከሰሞኑ በተደጋጋሚ የሚደርሱት ጥቆማዎች እንደሚያሳዩት በርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሰሞኑ እንደ አዲስ አበባ ወዳሉ ከተሞች ይህን ድርጊት በመስጋት እየሄዱ ይገኛሉ።
ችግሩ በስፋት እየተከሰተ እንደሆነ አንዱ ማሳያ በከተማው አመራሮች ጭምር የታመነበት ጉዳይ መሆኑ ነው።
በጠባሴ ክፍለ ከተማ የ2ኛ ዙር የሚሊሻ ምረቃ ፕሮግራም ከቀናት በፊት ሲካሄድ የደብረ ብርሀን ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ከተማዋ የራሷን ሰላም በራሷ ለማስጠበቅ ሁሉን አቀፍ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ ገልፀው "ሰልጣኞች ከዛሬዋ ቀን ጀምሮ በአካባቢያችሁ የሚፈጠሩ እገታ እና ዘረፋ ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር ማስቆም አለባችሁ" ብለው ነበር።
መረጃን ከመሠረት!



