ሰብዓዊ ድጋፍ የተቋረጠባቸው በሐይቅ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች ከፆም በኋላ ከዱር በሚሰበሰብ ፍሬ ለማፍጠር እየተገደዱ መሆኑን ተናገሩ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰባት ዓመት በፊት በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች እና ወረዳዎች ይኖሩ የነበሩ የአማራ ክልል ተወላጆች ተፈናቅለው በተለያዩ ወረዳዎች ላይ ሰፍረው እንደሚገኙ ይታወቃል።
በተለይ በደቡብ ወሎ ሐይቅ ከተማ አቅራቢያ መካነ-እየሱስ፣ ጃሬ ቁጥር አንድ እና ቁጥር ሁለት ተበለው በሚጠሩ የመጠለያ መንደሮች ውስጥ አራት ሺህ አምስት መቶ ሰባት (4,507) ተፈናቃዮች ይገኛሉ።
የተፈናቃዮቹ አስተባባሪ እና ተወካዮች ለመሠረት ሚዲያ እንዳሉት በሦስቱ መንደሮች የሚገኙ ተፈናቃዮች በያዝነው ዓመት ከሕዳር ወር ጀምሮ ሲቀርብ የነበረው መቁኑን/እርዳታ ተቋርጦብናል ብለዋል።
በሦስቱም መጠለያ መንደሮች የሚገኘት ተፈናቃዮች አብዛኛዎቹ ሙስሊሞች ናቸው ያሉት አስተባባሪዎቹ በያዝነው የረመዳን ፆም “የሚላስ የሚቀመስ ባለመኖሩ አንዳንዶቻችን በሃያ አራት ሰዓት አንድ ጊዜ ነው እህል የምንቀምሰው፣ ይህንንም የማያገኝ አለ። ብዙዎቻችን ግን የምናፈጥረው ቁርቁራ ተብሎ በሚጠራው የዱር ፍሬ ነው” ይላሉ።
“በሐይቅ፣ በደሴ እና በአካባቢዋ በሚገኙ መስጂዶች ተጠግተን የረመዳንን ወር ለማሳለፍ ስንሞክር ገፅታ ታበላሻላችሁ በሚል ወደ ከተማ እንዳንገባ ተከልክለናል” ሲሉ ነው አስተባባሪዎቹ የነገሩን።
በመጠለያ መንደሮቹ የሚገኙ ተፈናቃዮች ብዙዎቹ አረጋውያን እና ሕፃናት ናቸው ሲሆኑ እድሜያቸው የደረሰ እና ሰርተው መብላት የሚችሉት ግን መንደሩን ለቀው ከወጡ ቆይተዋል።
“መጠለያዎቹ ከሰባት ዓመት በፊት የቆሙ የሸራ ድንኳኖች በመሆናቸው አርጅተው ተቀዳደዋል። ይህንን እንኳ ጠግነን ለመኖር የሚያስችል ድጋፍ ልናገኝ አልቻልንም” ሲሉ አክለዋል።
በምግብ እጥረት ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎች እየተጋለጥን ነው የሚሉት ተፈናቃዮቹ በርሀብ የሞቱ ሰዎች መኖራቸውንም አልሸሸጉም።
"በተለይ ሕፃናት ከእንቅልፋቸው ተነስተው ምግብ እንዳይጠይቁን በጧት ከመጠለያ ካምፑ ርቀን እንውላለን። ልጆቻችን በርሀብ ቀንጭረዋል። ወዴት እንሂድ?" ሲሉም የመሠረት ሚዲያ ሪፖርተርን መልሰው ጠይቀዋል።
ሚድያችን ሚዲያ በደቡብ ወሎ ሐይቅ ከተማ አቅራቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮችን አስመልክቶ በተደጋጋሚ ዜና መስራቱ ይታወሳል።
-መሠረት ሚድያ-



