በታሪካዊው ታዕካ ነገስት አትሮንሰ ማርያም ቤተክርስቲያን ላይ የመንግስት ሀይሎች ትናንት ቅዳሜ ጠዋት የከባድ መሳርያ ጥቃት መፈፀማቸው ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- ታሪካዊው ታዕካ ነገስት አትሮንሰ ማርያም ቤተክርስቲያን በደቡብ ወሎ ዞን መሀል ሳይንት ወረዳ የሚገኝ ሲሆን በቅርስነት ተመዝግቦ ይገኛል፣ ከ400 ዓመት በላይ ታሪክ እንዳለው ታሪካዊ መዛግብት ያሳያሉ።
በቅርቡ በፌደራል የቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዕድሳት የተደረገለት ይህ ቤተክርስቲያን ትናንት ቅዳሜ ጠዋት 3 ሰአት ላይ በመንግስት ሀይሎች በከባድ መሳርያ እንደመቱት ታውቋል።
በጥቃቱ ሁለት የደብሩ አገልጋይ ቄሶች፣ ሁለት ዲያቆኖች እና የደብሩ አቃቤ ህይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች 20 ገደማ ሰዎች መቁሰላቸውን የአካባቢው ምንጮች ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
ድንገተኛ ጥቃቱ የተፈፀመው በአዋሳኝ ከሚገኘው ከአማራ ሳይንት ወረዳ 'መለስ ሳንካ' ከተባለ አካባቢ መሆኑን ምንጮቻችን ጠቁመዋል፣ በህንፃው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።
"ደጀ ሰላሙ በድብደባው ምክንያት ፈርሷል" የሚሉት በስፍራው የሚገኙ ታዛቢዎች በዚህ በተረሳ አካባቢ ህዝቡ ላለፉት ጥቂት አመታት በመንግስት እና ፋኖ ሀይሎች መሀል በሚደረግ ውጊያ ለከፍተኛ እንግልት እና ስቃይ እያስተናገደ እንደሚገኝ ይናገራሉ።
"ፋኖም በአካባቢው ለመንግስት ችግር ፈጣሪ ነው፣ ይሁንና ይህ ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት ከአካባቢው ለቀው ወጥተው ነበር። ታድያ ቤተክርስቲያን ምን ያድርግ? ቄስ እና ምዕመኑ ምን ያድርግ" በማለት በምሬት ሁኔታውን አስረድተዋል።
በቅርቡ በስፍራው ተገኝተው እንደነበር የሚሀልፁት ሌላ ምንጫችን ደግሞ "ትራንስፖርት እንኳን በቅጡ የሌለበት አካባቢ ነው፣ በጦርነት እና ግጭት እንዲህ ሲታመስ ማየት ያማል" በማለት ተናግረዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን በመሀል አምሃራ ሳይንት የሚኘው ደብሩ የብዙ ቅርስ ባለቤትና ጥንታዊ ቤተክርስቲያን ሲሆን የተመሰረተው በ347 ዓ/ም በአብርሃ አፅብሃ ዘመነ መንግስት መሆኑ ይነገራል፡፡
ይሁን እንጅ ቤተክርስቲያኑ በዘመናዊ መልኩ የተሰራው ከ1460-1470 ዓ.ም በአፄ በእደ ማረያም በንግስናቸው ወቅት ነበር። አትሮንሰ ማርያም ወይም አትሮንሰ እግዝዕትነ ማርያም አጼብዕደ ማርያም በንግስና ዘመናቸው መጀመሪያ ገደማቀላንቶ በተባለ አከባቢ የመሰረቱት ገዳም ነው። የገዳሙን ግንባታ ያስጀመሩት የንጉሥ ብዕደ ማርያም አባት እንደነበር ታሪካዊ ድርሳናት ያሳያሉ፣ አባት በ1460ዎቹ ወደዚህ አከባቢ ታቦት ማምጣታቸው ይነገራል።
ገዳሙ ከደብረ ሊባኖስ ጋር ግንኙነት የነበረውሲሆን የገዳሙ አስተዳዳሪም መክብብ የሚል የክብርመጠሪያ ይሰጠው እንደነበር የመሃል አምሃራ ሳይንት ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት መረጃ ያሳያል። በዚህ የቤተክርስቲያን ጥቃት ዙርያ በመንግስት አካላትም ሆነ በመከላከያ በኩል የተሰጠ ሌላ መረጃ የለም።
-መሠረት ሚድያ-





