በዘንድሮ ምርጫ ዲሞክራሲን አትጠብቋት፣ ምክንያት ግን ፈልጉላት
ከተስፋዬ ወልደዮሐንስ ሀይሌ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- ሐዋሳ ዩኒቨርስቲ የሲዳማ ክልል የምርጫ አስፈፃሚዎች ስልጠናን ለመስጠት የተገኘሁበት የስልጠና ክፍል ድንገት በር ተንኳኳ። አብሮኝ ስልጠናውን የሚያመቻቸው የዲላ ዩንቨርስቲ መምህር በሩን ከፍቶ ፊት ለፊት ከቆመው ባለሱፍ ለባሽ ጋር መጨቃጨቅ ጀመረ። በመጨረሻ የእኔንም በክፍሉ ውስጥ ያሉ ሰልጣኖችንም ትኩረት ሳበ። ወደበሩ ቀርቤ ተራዬን ጀመርኩት። ምን እንደፈለገ በግልጽ ጠየቅኩት፣ የክልሉ ፕሬዝዳንት ጥበቃ መሆኑንና ሰልጣኞችን በሻይ ሰዓታቸው ማነጋገር እንደሚፈልጉ ሊያሳውቀን መምጣቱን፣ እሳቸውም ግቢው ውስጥ መሆናቸውን ነገረን።
መልሴ አንድና አንድ ነበር: ተመልሰህ ሂድና እንደማይቻል ነግረህ እንዲመለሱ ንገራቸው የሚል። ፊቱን ኮስተር ሰብሰብ አድርጎ ማንንና ምን እየተናገርክ እንደሆነ ታውቃለህ አለኝ። የለውጡ እንፋሎት ያልበረደበት፥ የወከልኩት ምርጫ ቦርድም ዲሞክራሲን ለመስበክ፥ ተቋማዊት አሰራርን ለማስፈን ፊሽካውን ነፍቶ እኔን መሰሉ በርካቶች ሙያዊ ግልጋሎት ለመስጠት የተሰለፍንበት ብዙ ኪሎ ሜትሮችን አቋርጠን የመጣንበት መርህ፥ የህግ በላይነት፥ የዲሞክራሲ ግንባታ፥ ተቋማዊ ልህልናና ነፃነት እያልኩ የልብ ልብ መሰማት ላይ ነበርኩና ለመልሴ ወደኃላ አላልኩም።
የምትነግራቸው ትህዛዝህን እንዳከብር ለላኩኝ አለቃህ ነው። ሌላ ጊዜ አሰራሩ ከፈቀደላቸው በራሳቸው ወጪ ሰልጣኖች ስብሰባ መጥራት ይችላሉ፣ ለዛሬው ግን ለእረፍት ሻይ ሰዓት 15 ደቂቃዎች ብቻ የቀሩት ቢሆንም የሻይ እረፍት እንደማይኖር ጮክ ብዬ ተናግሬ የስልጠና ክፍሉን በር ዘግቼ ስልጠናዬን ቀጠልኩኝ። ያ ሰው ታዲያ የአሰልጣኙ ቡድኑ ያረፈበት ባለኮከብ ሆቴል ሲመላለስብኝ ሰነበተ።
ምርጫውን ያለ ምንም እንቅፋት ለማካሄድ ደፋ ቀና የተባለለት ሂደት እንዴት ድንቅ የሆነ አደረጃጀት፥ አሰራርና መቆጣጠሪያ ስልቶች ሁሌም የምደነቅባቸው ነበሩ። እታች ሲወርድ ምርጫው ሲካሄድ የተመለከትነው ሌላ ቢሆንም ቅሉ። ዝርዝሩ ብቻ ብዙ ነው።
የጊዜው መሮጥ ግን ድንቅ ነው። አምስት ዓመታት ነጉዶ እነሆ ሌላ ምርጫ ፍፁም የተለየ የፖለቲካ ምህዳር፥ አሰላለፍና ስሜት ታጅቦ ዘንድሮም ለመካሄድ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም የጊዜ ሰሌዳ ተነድፎት፥ በጀት ተቀምሮለት 7ተኛው ዙር ጠቅላላ ሀገር አቀፍ ምርጫ ሊካሄድ ነው። እርግጥ ነው የፖለቲካ ተደራሽነትና ሽፋን የአየር ሰዓት አጠቃቀም ድልድል ላይ ፍትሀዊዊ ባይሆንም ቅሉ የሚዲያ ሽፋን ተሰጥቷቸው መኮምኮም ጀምረናል። ይሁን እንጂ እውን ከዚህ ምርጫ በውጤቱ የምንጠብቀው የተለየ ነገር አለን ወይ ብዬ ራሴን እንድጠይቅ ያደርገኛል።
የአንድ ሀገር ዜጎች ፍላጎታቸውን የሚገልጹበት፥ መብታቸውን ከሚጠቀሙበት አንዱ መንገድ በመንግሥት ውስጥ የሚወክሏቸውን ሰዎች በመምረጥ ነው፡፡ ከዲሞክራሲያዊ መርዕዎች መገለጫዎች መካከል ምርጫና የምርጫ ስርዓት ነው የሚባለው። ሂደቱም ከምርጫ በፊትም ሆነ በኋላ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ማስፈራራት፣ ሙስና፣ እና ማጎሳቆል ሳያሳስባቸው ይህ ነገር ይደርስብኛል ሳይሉ በተጨማሪም መራጮችን የሚያውኩ እንቅፋቶች በፍጹም ነፃነትና ፍቃድ ሚያደርጉት ልምምድ መሆኑ እሙን ነው። ይህም መደበኛ፥ ነፃና ሚዛናዊ ሲሆን የዜጎችን ተሳትፎ፥ ያገባናል ባይነትና አንድነት በመገንባት ብሔራዊ መግባባትን ለማምጣት፥ ሀገርን በመደበኛነት በህግና በህግ ብቻ ለመምራት፥ ሰላም ፀጥታንና ደህንነትን ለመጠበቅ ቁልፍ ሚናን ይጫወታል።
የምርጫው ምህዳር ምን ይመስላል?
ባለፉት የብልጽግና ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያ በብዙ አጣብቂኝ ውስጥ ያለፈችበት ጊዜ ነበር። ብልጽግናና ልማትን ተቀዳሚ ግቤ ናቸው ብሎ ለተነሳው ፓርቲ የኦሮሚያ ሸኔ ጦር፥ የትግራይ ጦርነት፥ የአማራ ፋኖ ትግል፥ የቤንሻንጉል ሰላም ማጣት እንዲሁም በየቀኑ የአዲስ አበባ ጫፍ ቡራዩን ጨምሮ በወልቂጤ፥ ወሊሶ፥ አርሲ እያልን የምንጠራቸው በነፃነት፥ በሀይማኖት፥ በብሔር፥ በወሰንና ድንበር ይገባናል የሚለኮሱ የግጭት እሳቶች ዛሬም ማብረጃ አልተገኘላቸውም። መንደሮች በነፃነት ፈላጊዎችና አውጪዎች ተኩስ አልያም የመንግስት ድሮኖች ከማስተናገድ ወደኃላ አላሉም። ሀገራዊ መግባባት፥ ብሄራዊ እርቅ መነጋጋር መወያየት የጋራ የጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሔ ፍለጋ ግድም ቦታም ትኩረት የተነፈገው ይመስላል።
በዚህ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ለመካሄድ በዝግጅት ላይ የሚገኘው ሀገራዊ ምርጫ ገዢው ፓርቲ ብቻውን ሳይሆን እንደወትሮው ሁሉ ብቻውን ሳይሆን በብዛት አምስቱን ዓመት የማናያቸው አንዳንዶቹ ጭራሽ ከነመኖራቸውም የዘነጋናቸው የተቀሩት ደግሞ በስልጣን መጋራት ስም ሌላ ብልጽግና ሆነው የተከሰቱ 10934 እጩዎች ከእነዚህም ውስጥ 2098 የፌዴራሉን መንግስት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበርን ለማግኘት 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ማካሄዳቸውን ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል።
የምርጫው ምህዳር እንደዚህ ቀደሞቹ (ከ1997 እና 2013 ውጪ) የተለመደው ምርጫ ከመሆን ምን የተለየ ነገር አለው ብለን ብንጠይቅ ምላሹ በጣም የተቀዛቀዘ የሚለውን ከብዙ አቅጣጫ አደምጣለሁ።
አንድም የህዝብ ገዢው ፓርቲ ካለው የመንግስት መዋቅሩን፥ ስልጣኑን፥ የህዝቡን ገንዘብና ሃብት በመጠቀም ካለው የተቆጣጣሪነት፥ የማፈንና፥ ምርጫን በሚፈልገው መንገድ የመምራት ልምዱን በመመልከት በእውነተኛ ምርጫ የኢትዮጵያን ገዚዎች በድምፄ በመራጭነት ካርዴ እለውጠዋለሁ ብሎ ማሰብ ባለው ኢኮኖሚኣዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች፥ ጠንካራና ተጽህኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ትብብርና ህብረቶች ተጠናክረው ህዝባዊ ቅቡልነት ተወዳደሪነታቸውን የሚገዳደር አዲስ ስትራቴጂና መንገድ ካለማምጣታቸው ጋር ተያይዞ ተስፋ እያስቆረጠው ስለመጣ ና ሌሎች ምክንያቶችን መደርደር ይቻላል።
ምርጫ ለብልጽግና እንደመንግስት ምን ያደርግለታል?
ወራሽነቱን ተሰናብቶ በአዲስ ስም ያለፉትን አምስት ዓመታት ሀገሪቱን በከፊል ማስተዳደር የቻለው ብልጽግና ያስመዘገባቸው አውንታዊና አሉታዊ ጉዳዮችን ሸክፎ ለዚህኛው ምርጫ የቀጣዩን አምሰት ዓመታት እንደመንግስት ለመቆየት በዘላቂነት ለመሰንበት ካሰበው ህልም ደግሞ ሁለተኛውን ዙር ለመቀበል ከመድረኩ ተከስቷል።
ብልጽግና የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ ይህንን ምርጫ ማሸነፉ የማይጠበቅ አዲስ ዜና አይመስለኝም። ከባለፉት ዓመታት የተጠቀሙባቸውን ቴክኒክና ታክቲኮች ዘመኑን በሚዋጅ መልኩ እንደሚጠቀምባቸው ሳይታለም የተፈታ ነው። እንደዚህ ቀደም 100 ፐርሰንት ክልልና የፓርላማ መቀመጫ የማገኘት ፍላጎትም ይኖረዋል ብዬ አላስብም፣ እንደባለፈው በተሳትፎ ኮታ የሰጠውን ሚኒስትርነት፥ የሚኒሰቴር ዲኤታነትንና የቢሮ ሃላፊነት ቦታን ግን በእደላ ከመስጠት ይልቅ በምርጫው ተወዳዳሪዎችን በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ባለማቅረብ የመሳሰሉ ስልታዊ አካሄዶችን መጠቀም የበለጠ ምርጫው አሳታፊ እንደሚያደርገው እገምታለሁ።
ብልጽግና ይህንን ምርጫ የሚፈልግበት ዋነኛ ምክንያት የመሸነፍና የማሸነፍ ጉዳዮች አሰሳስበውት ሳይሆን ከአለማቀፉ ማህበረሰብ፥ ከዲፕሎማቲክ ማህበረሰብና ተቋማት የቅቡልነት ካባን ደርቦ ስለሚሰጠው ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ከላይ ያነሳናቸው 46 ፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደዚህ ቀደሙ ይደርስባቸው የነበረውን መዋከብ፥ ዛቻና እስር በመቀነስ እንክብካቤን በማብዛትና ዲጅታል ሰራዊቱን ሚና በማጎልበት ህይወት ህይወት የሚሸት ምርጫን የበለጠ ተቀባይነቱን በሚያጎላ መልኩ ያስኬድለታል።
ለዚህ ምርጫ ብልጽግና በጥቂቱም ያሳጡኛል አልያም በመሃሉ ያፈነግጣሉ ለሚላቸው ለተቃዋሚ ፓርቲዎች ከሚመዛቸው ካርዶች ውስጥ አንዱ ምርጫውን ከብሔራዊ ጥቅም ጋር ማያያዝ ነው። ብሔራዊ ጥቅም የብልፅግና አዲሱ ዜማ ፖለቲካ ፓርቲዎችን በሂደቱ ከውድድሩ ቢወጡ፥ ቅድመ ሁኔታ ቢያስቀምጡ፥ ራሳቸውን ቢያገሉ የሚጠብቃቸው ከኤርትራ አልያም ሀገር ውስጥ ካሉ የመሳሪያ ትግል ከሚያደርጉ ቡድኖች ጋር በመመሳጠር፥ በመስራት፥ በማሴር የመሳሰሉ ቃላት ህልውናቸው ላይ የመፍረድ አልያም እንደዚህ ቀደሙ ሁሉ የፓርቲው ስንጥቅ/ሀይ ኮፒ ስልት መጠቀምን አማራጭ መንገድ ያደርገዋል።
የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡም ቢሆን ያለው ዘፈን አንድ አይነት ነው። የፓለቲካ ፓርቲዎቹን እየሰበሰቡ በኤምባሲዎቻቸው ያነጋግራሉ። ለምርጫ የሚሆን የተወሰነ የበጀት ድጋፍ ያደርጋሉ። ስርአቱ፥ ህጉና አፈፃፀሙ እንደማይሰራ እያወቁትም ተወዳደሩ መወዳደሩ ለድርድር መቅረብ የለበትም በውጤቱ ካልተስማማቹ ፍርድ ቤት ቆሞ መከራከር ይቻላል የሚለውን ዘፈን በየምርጫ እንደአዲስ ዘፈን ተናጋሪ አምባሳደሮቻቸውን እየቀያየሩ ይጫወቱታል።
የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች አሁናዊ ሁኔታ
የፖለቲካ ፓርቲዎች በሌሉበት ዘመናዊ የውክልና ዲሞክራሲን ማሰብ አይቻልም፡፡ ፓርቲ ግለሰቦችን በአባልነት የሚይዝ የዜጎች ማህበር ሲሆን ዜጎች በቋሚነት የተደራጀ ፖለቲካዊ አስተሳሰቦቻቸውንና ውሳኔያቸውን መሰረት በማድረግ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው የሚያስችሏቸው መድረክ ናቸው፡፡ ፓርቲዎች የተለያዩ ፍላጎቶችን፣ ራእዮችን እና ሃሳቦችን ማቀናጀት እና መግለጽ ከመቻላቸውም በላይ የፖለቲካ ልሂቃንንም ለማግኘት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምንጭነት ያገለግላሉ፡፡ ለዚህም ግባቸው መሳካት በምርጫ መሳተፍን፣ የመራጮቻቸውን ልብ በሚያቀርቡት ሀሳብ ማሸነፍንና የመንግስትነት ስልጣንንን መጨበጥ መዳሻቸው በማድረግ ለፖለቲካው ምህዳርና ለዲሞክራሲ ግንባታ ያላቸውን ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች የዜጎች ቋሚ ማህበራት ናቸው ሲባልም በነፃ የግል ፍላጎት አባልነትና የተቀረጹ ፕሮግራም ያላቸው፣ በምርጫ በመሳተፍ ሥልጣን ለመያዝ የሚፈልጉ፣ ሊፈቱ በሚገባቸው ማህበራዊ ችግሮች ላይ እና በወሳኝ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ያሏቸውን ፖለቲካዊ አቋሞቻቸውን በመሪዎቻቸው በኩል የሚገልጹ ማለትን ያጠቃልላል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖርም መንግሥት ለሚሠራቸው ነገሮች ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆን በማድረግ፣ ሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ ልምዶችና ተሞክሮዎች እንዲኖሩትና እንዲያዳብረው ማስቻል፣ የሕዝብን ፍላጎቶች ጠቅለል አድርገው ማቅረብ መንግሥት ለመመሥረትና በዘላቂነት መቻቻል እንዲኖር በማስቻል ለዲሞክራሲ ግንባታ ዓይነተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡
ነገር ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ የምርጫ ስርአት ውስጥ አንድም እውነተኛ ተፎካካሪነት በሌላ በኩል ደግሞ የሚዜነት ሚናቸው እጅጉን የጎላ ነው። ከሁሉም ከሁሉም የከፋው ደግም ተከፍሎትም ይሁን ቃል ተገብቶለት የአሙቁልኝ ገፀ ባህሪ መጫወት ነው።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ዲሞክራሲን የመገንባት ትልም የዜጎችን ህይወት ከመለወጥ ዓላማ ጋር ከመያያዝ ይልቅ ግቡን ከግለሰቦች የስልጣን ጥምና ሽኩቻ ያደርጉታል፡፡ ለህዝብ ጥቅም ከመሄድ ይልቅ ለግል ፍላጎታቸው ለማዋል መራኮትን ምርጫቸው ያደርጋሉ፡፡ ከትምህርት፣ ስልጠና፣ ንባብና የስትራቴጂክ የሆኑ ምላሽ መስጫ ጉዳዮች ላይ ከማተኮር ይልቅ በየእለቱ የፅህፈት ቤት ስራ ላይ በማተኮር የተለመደውን መንገድ እየሄዱ የህዝቡን ድጋፍ ማግኘት፣ ፖለቲካዊ ድልን ማምጣት ምርጫን ማሸነፍ በግብነት ሳይሆን በምኞት ደረጃ ያስቀምጣሉ፡፡
ምርጫ የአንድን ስርዓት ዲሞክራሲያዊነት ማረጋገጫ ምሰሶዎች መካከል አንዱ ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ይህንን በስልጣን ሽግግር ውስጥ ይጠብቁታል፡፡ ፓርቲዎቻችን የህዝቡን የአባላቶቻቸውን ድጋፍ ፍለጋ የሚራወጡት በምርጫ ዋዜማ ሲሆን ውጤቱ ደግሞ ከሜዳው የመጥፊያ ፊሽካ ይሆንላቸዋል፡፡ ዲሞክራሲን፣ ዲሞክራሲያዊ አሰራርንና ተቋማትን መገንባት የልምምድ ሂደትና ውጤት ነው። ለዚህም ፖለቲካዊ ምህዳሩ፣ የሁሉም አጋሮች የነቃ ተሳትፎና ቁርጠኝነት ይወስኑታል፡፡ የፓለቲካ ፓርቲዎች የድክመት ምንጭ ምርጫን ብቻ እንደመጨረሻ ግብ ወስዶ መስራታቸው ይሆናል፡፡ ጠንካራ የሆኑ ሲቪል ማህበራት በሌሉባት አገር የፖለቲካ ፓርቲዎች ሌላኛው ሚና ህዝቡን ማንቃት፣ ዘላቂ ድጋፍ ማግኘትና የእኔነትን ስሜት መፍጠር የእነሱ ሃላፊነት መሆኑን ይዘነጉታል፡፡
አይደለም ብልጽግናን የመሰለ የህዝብንና ሀላፊነት የተሰጠውን የመንግስት ሀብትና ንብረት ለፖለቲካ ፓርቲ መጠቀሚያና መገልገያ ካደረገ ድርጅት ጋር ተወዳድረው ተፎካክረው ለማሸነፍ፥ ለመቆት የህዝቡን ይሁንታና ተስፋ ለማግኘት ፓርቲዎች በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ አባላትን በማበራከት፣ እውቀትና መርህ ላይ የተመሰረተ ትስስሮሽ መተግበር፣ መሪዎቻቸው ራሳቸውን መመልከት፣ መገምገም፣ ግብ ማስቀመጥና ሚናቸውን መለየት ካልቻሉ በዚህም ምርቻ ከሚዜነት ካጃቢነትተለመደውምርቻ ቦርድ ምርቻ ማስፈፀሚያ ድጎማ ብር ጥል ወጥተው መመልከት የሚቻል አይመስለኝም።
ታዲያ ከዚህ ምርጫ ምን እንጠብቃለን?
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።



