ወልድያ ከተማ ውስጥ አንድ የቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በጥይት ተመትተው መገደላቸው ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በሰሜን ወሎ ዞን የወልድያ ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ካቴድራል አስተዳዳሪ መልዓከ ምሕረት አባ ዐይናለም አማረ /ቆሞስ/ ዛሬ መጋቢት 4 ቀን 2018 ዓ.ም በሚያገለግሉበት ቤተ-ክርስቲያን ውስጥ መገደላቸውን የመሠረት ሚዲያ ምንጮች ጠቆሙ።
የካቴድራሉ አስተዳደር ባልደረባ ለሚዲያችን እንደተናገሩት “ቀደም ሲል በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ በመንግሥት ታጣቂዎች ዘንድ ጥርስ ተነክሶባቸው ነበር" ብለው ገልፀው "ነገር ግን ለሞት ያበቃቸዋል ብለን ትኩረት ሰጥተነው አናውቅም፣ በሌሊት ወደ ቤተክርስቲያኑ ግቢ በመዝለቅ በጥይት ደብድበዋቸው ሄደዋል” ሲሉ ነግረውናል።
መልዓከ ምሕረት አባ ዐይናለም አማረ መንግሥት ከታጣቂዎች ጋር እያደረገ ያለውን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም እንዲቋጭ በግልፅ አደባባይ ሲናገሩ እንደነበር ተገልጿል።
በሥርዓተ ቀብራቸው የተገኙት የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ ባስተላለፉት ቃለ-ምእዳን “መልአከ ምሕረት አባ ዐይናለም እግዚአብሔር በቆረጠው ቀን አርፈዋል፤ ነገር ግን በቀናቸው ለተጠሩት አገልጋይ መሞት ምክንያት የሆነ ሰው ባይወለድ ይሻለው ነበር” ብለዋል።
ለሞት ያበቃቸው ምክንያትን አስመልክቶ ብፁዕነታቸው ሲናገሩም “መልአከ ምሕረት አባ ዐይናለም አማረ ነጻና ፊት ለፊት የሚናገሩ፣ ለልማትና ለቤተ ክርስቲያን እድገት በቆራጥነት ሰርተው የሚያሰሩ ትጉኅ እረኛ ነበሩ” ማለታቸውን የካቴድራሉ አስተዳደር ባልደረባ ለመሠረት ሚዲያ ተናግረዋል።
ከሳምንት በፊት በደቡብ ወሎ ዞን መሀል ሳይንት ወረዳ የሚገኝው ታሪካዊው ታዕካ ነገስት አትሮንሰ ማርያም ቤተክርስቲያን ከመንግስት ሀይሎች በተተኮሰ ከባድ መሳርያ ተመትቶ አምስት ምዕመናን መገደላቸው ይታወሳል።
-መሠረት ሚድያ-


