ከአልሸባብ እና ሌሎች የሽብር ቡድኖች ጋር በመተባበር ተጠርጥረዋል የተባሉ አምስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ፍርድ ቤት ቀረቡ
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ በርካታ ሰዎች በመላው ሀገሪቱ ለእስር እየተዳረጉ እንዳሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ የሲቪል ልብስ በለበሱ የፀጥታ አካላት ታፍነው ተወስደው ደብዛቸው እየጠፋ መሆኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሚድያችን ዛሬ የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው የሽብር ቡድኖችን ተልዕኮ ተቀብለው ሲንቀሳቀሱ ነበር ተብለው በፌደራል ፖሊስ የተጠረጠሩ
አምስት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች በትናንትናው ዕለት ፍርድ ቤት ቀርበዋል።
ፌደራል ፖሊስ እንዳለው ተጠርጣሪዎቹ አልሸባብ እና አይ ኤስ ከተባሉት ዓለም አቀፍ አሸባሪዎች ጋር ትስስር በመፍጠር እና በሶማሊያ የሽብር ስልጠና ወስደው በአዲስ አበባ ሲንቀሳቀሱ አግኝቻቸዋለሁ ብሎ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የሕገ-መንግስት እና የየፀረ-ሽብር ችሎት አስረድቷል።
ተጠርጣሪዎቹ በበኩላቸው “እምነታችን ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ሲሆን ስራችንም ቤተክርስቲያንን ማገልገል ነው። ከተባለው ቡድን ጋር በእምነትም ሆነ በግብርም የሚያገናኘን አንዳችም ክር የለንም። ሶማሌያ የተባለ አገርም በስም ካልሆ በስተቀር በየት በኩል እንዳለ እንኳ አናውቅም” ሲሉ ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።
የፌደራል ፖሊስ በበኩሉ ይህንን የሚያስረዳ ማስረጃ እያሰባሰብኩ በመሆኑ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን የጠየቀ ሲሆን ይህንኑ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ ግን ተጠርጣሪዎቹ ተቃውመዋል።
“ለምርመራ በሚል ሌሊት ከታሰርንበት ክፍል በማስወጣት ፊታቸውን በጭንብል የሸፈኑ ወታደሮች ከአልሸባብ እና ከኤይ ኤስ ተልዕኮ ተቀብለናል ብላችሁ ፈርሙ በሚል እየደበደቡን ነው። አሁንም ተጨማሪ ቀጠሮ የጠየቀው ለድብደባ ፍቃድ እንጂ አንዳችም ማስረጃ ለመፈለግ አይደለም፣ እንደሌለም ያውቃል። ተጨማሪ ቀጠሮ ከተሰጠው በቀጣይ በሕይወት አንገናኝም" ሲሉ ቀሳውስቱ በየተራ እያለቀሱ ተናግረዋል።
ፍርድ ቤቱም "በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተፈፀመ የተባለው ድርጊት እውነት ከሆነ አግባብ አይደለም። ነገር ግን ለምርመራ ተጨማሪ ቀጠሮ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ይሄው ተፈቅዶለታል ሲል" በይኗል።
ተጠርጣሪ ቀሳውስቱ የሚያገለግሉት በአዲስ አበባ አገረ ስብከት ስር በሚገኙ የተለያዩ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት መሆኑን የመሠረት ሚዲያ ምንጮች ጠቁመዋል።
-መሠረት ሚድያ-


