“ልጄ በፖሊስ የተወሰደችው ዘፈን ከፍተሽ አድምጠሻል ተብላ ነበር፣ ዛሬ ደግሞ በመንግሥት ሚዲያ ከአልሸባብ ጋር በመተባበር ሽብር ልትፈፅም ስትል ተያዘች በሚል ፎቶዋን ከሌሎች ሰዎች ጋር አየሁ”- ወላጅ አባት
(መሠረት ሚድያ)- ልጃቸው አዲሱን የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ሙዚቃ መኖሪያ ግቢዋ ውስጥ ከጓደኞቿ ጋር ከፍ አድርጋ ስታዳምጥ እንደነበር የገለፁ አንድ የታሳሪ ወላጅ አባት የፀጥታ ኃይሎች የመኖሪያ ቤታቸውን ሰብረው በመግባት ከእነጓደኞቿ ይዘዋት እንደ ሄዱ ለመሠረት ሚዲያ ተናግረዋል።
ለልጃቸው ደህንነት ሲሉ ስማቸውን ከመግለፅ የተቆጠቡት ወላጅ አባት “ለምን ይዘዋቸው እንደሚሄዱ የፀጥታ ሀይሎችን ብንጠይቃቸውም ለጥያቄ ፈልገናቸው ነው፣ ይመለሳሉ ብለው ይዘዋቸው ከሄዱ በኋላ በዘፈን ሰበብ ምርጫውን ለማደናቀፍ አመፅ እየቀሰቀሳችሁ ነው የሚል ጥያቄ እንደቀረበላቸው ዛሬ ፌደራል ፖሊስ ልጠይቃት ሄጄ ነገረችኝ” ይላሉ።
ወደ ቤቴ ስገባ ደግሞ በመንግሥት ሚዲያ ከአልሸባብ እና ከአይ ኤስ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ሽብር ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ ደረስኩባቸው የሚል መግለጫ ላይ የልጄን ፎቶ አየሁት ሲሉ የታሳሪዋ ወላጅ አባት ጨምረው ተናግረዋል።
የጓደኞቿን ፎቶ ደግሞ የጦር መሳሪያ ሲያዘዋወሩ ተያዙ ከሚባሉ ሰዎች ጋር አየኋቸው ሲሉም የታዘቡትን ነግረውናል።
"ልጄ የ12ኛ ክፍል ተማሪ ናት፣ ከትምህርት ቤት ውጭ የትም ወጥታ አድራ አታውቅም። ከተጠቀሰው አካል ጋር ልትተባበር ቀርቶ ጎረቤቶቿን እንኳ በውል አታውቅም። የተባለው ዘፈን ተከልክሎም ከሆነ በዚሁ ትጠየቅ እንጂ እንዴት ገና ታዳጊ ብላቴና ከሽብር ጋር ያገናኙብኛል” ሲሉ አምርረው ይወቅሳሉ።
ከእንግዲህ በኋላ በሰላም ብትለቀቅ እንኳ ስሟ እና ፎቶዋ “ሽብር ለመፈፀም ተያዘች” በሚል በሚዲያ ስለተለቀቀ እንዴት ብላ ነው ትምህርቷንስ የምትቀጥለው? ሲሉ መልሰው ይጠይቃሉ።
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በተለምዶ 3ኛ ፖሊስ ጣቢያ እና በፌደራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል ቢሮ ውስጥ ባሉ የእስረኛ ማረፊያ ጣቢያዎች የታሰሩ ልጆቻቸውን ለመጠየቅ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተሰልፈው ታይተዋል።
ብዙዎቹ ደግሞ ልጆቻቸው የታሰሩበት ጣቢያ ባለመታወቁ በየ ክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ እና ፖሊስ ጣቢያዎች እያለቀሱ ሲፈልጉ ውለዋል።
አሁን ከመሸ የፀጥታ ግብረ ኃይሉ ሚያዚያ 9 ቀን 2018 ዓ/ም ባደረኩት አሰሳ 138 ተጠርጣሪዎችን ያዝኩ ማለቱን ተከትሎ በአንድ ቀን ይህንን ያህል ከሽብር ጋር የተገናኘ ተጠርጣሪ አንድ ስፍራ ላይ ተሰብስበው የተገኙ አስመስሎበታል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ለሚዲያችን ጠቁመዋል።
አክለውም መግለጫው አዲሱን የቴዎድሮስ ካሳሁንን ሙዚቃ ሲያዳምጡ ታሰሩ የሚለውን የመሠረት ሚዲያ ዜና ለማስተባበል የታለመ ይመስላል ሲሉም አክለዋል።
-መሠረት ሚድያ-


