አሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማደፍረስ እና ግጭት ለመቀስቀስ እየሰሩ ነው ባሏቸው የሕወሓት አባላት ላይ የቪዛ እገዳ ጣሉ
(መሠረት ሚድያ)- የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ቶማስ ፒጎት ዛሬ ሰኔ 17 ቀን 2026 በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እና ለመሠረት ሚድያ አዲስ አበባ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በኩል የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው እርምጃው የተወሰደው በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ረገድ ቀጥተኛ ተሳትፎ ባላቸው ወይም ተባባሪ በሆኑ ግለሰቦች ላይ ነው።
የቃል አቀባዩ መግለጫ እንዳመለከተው በሕወሓት አመራሮች እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በቅርቡ እያገረሸ የመጣው ውጥረት በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ደም አፋሳሽ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል። በዘንድሮው ዓመት መጀመሪያ ላይ የትግራይ ደኅንነት ኃይሎች ከኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጋር መጋጨታቸውን ያስታወሰው መግለጫው ይህም የ600 ሺህ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው የ2020-2022ቱ ጦርነት ካበቃ ወዲህ በሁለቱ አካላት መካከል የተደረገ የመጀመሪያው ቀጥተኛ ወታደራዊ ፍልሚያ መሆኑን ገልጿል።
ይህን ተከትሎም በሰሜን ኢትዮጵያ የሚገኙ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎች ዳግም ወደ ጦርነት አዙሪት እንዳይመለሱ በመስጋት መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው እየተሰደዱ መሆኑ ተመላክቷል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በሀገሪቱ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አዋጅ አንቀጽ 212(a)(3)(C) በተሰጣቸው ሕጋዊ ሥልጣን መሠረት እርምጃውን መውሰድ መጀመራቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
"ይህ የቪዛ ገደብ ፖሊሲ በትግራይ ክልል ያለውን ቀውስ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ረገድ ተጠያቂ የሆኑ ወይም እጃቸው ያለበትን የሕወሓት አክራሪ አቋም አራማጅ (hardline) አባላትን እና የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ለይቶ የሚመለከት ነው" በማለት ቶማስ ፒጎት ተናግረዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ በሰላምና በክብር መኖር ከሚፈልገው የትግራይ ሕዝብን ጨምሮ ከጠቅላላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጎን መቆሟን እንደምትቀጥል መግለጫው ያረጋገጠ ሲሆን በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን አደጋ ላይ የሚጥሉ የሕወሓት ባለሥልጣናት እና ሌሎች ግለሰቦችን ተጠያቂነት ለማረጋገጥና ድርጊታቸውን ይፋ ለማድረግ ዋሽንግተን ያሏትን ዲፕሎማሲያዊ መሣሪያዎች ሁሉ መጠቀም እንደምትቀጥል አስታውቃለች።
| መሠረት ሚድያ |


