ሱፐር ደብል ቲ ያሰራቸው እና ያሳሰራቸው የቀድሞ ሰራተኞች በስም እና ምስል እየተለዩ ነው፣ ያሉበትን ያላወቀ ቤተሰብ ካለ እዚህ ነን እያሉ ነው፣ እነማን ናቸው?
(መሠረት ሚድያ)- ከሰሞኑ ሚድያችን ያወጣቸውን ዘገባዎች ተከትሎ ሱፐር ደብል ቲ ጄኔራል ትሬዲንግ ባሳለፍነው ሳምንት ሸገር ከተማ፣ አለም ገና በሚገኘው የፋብሪካው ቅጥር ግቢ ውስጥ ባለሀብቱ ራሳቸው ያደራጁትን 'አደጋ መከላከል' የሚባል ሀይል በማስገባት ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰራተኞችን ስልክ እየፈተሹ እንደነበር ታውቋል።
"ሁሉም ሰራተኛ ታግቶ ስልኩ እየተበረበረ ቆይቷል፣ በተለይ ለመሠረት ሚድያ መረጃ የሰጡ እና መሠረት ሚድያ ብለው ፍለጋ (search) የፈፀሙ እየተፈለጉ ነው" ያሉት አንድ ምንጫችን ናቸው።
"ፍተሻውን የሚያረገው የመንግስት አካል አይደለም፣ ባለሀብቱ አቶ ፀጋዬ ደበበ በግል ያደራጇቸው አደጋ መከላከል የሚባል ሀይል ነው" ያሉት ምንጮች ፍተሻው በየቀኑ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በደረሰበት ድብደባ ከፍተኛ የጀርባ አጥንት እና የነርቭ ጉዳት ያጋጠመው ወጣት መንክር የዛሬ ሳምንት ቅዳሜ በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ህክምና እየተከታተለ እንደሆነ እና ወጪውም በፋብሪካው ባለቤት እንደተሸፈነ ቢገልፅም ይህ ሀሰት መሆኑን ሰምተናል።
ምንጮቻችን እንዳሉት ወጣቱ ዜናው ከወጣ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ አዳማ ከሚገኝ የፀበል ቦታ በቀጥታ ተፈልጎ እና አዳዲስ ልብስ እና ጫማ ተደርጎለት እንዲሁም አዲስ ዊልቼር ቀርቦለት ጋዜጠኞች ፊት መቅረቡ ታውቋል።
ለዚህ አገልግሎት የሚውል ዊልቼር የፋብሪካው ንብረት በሆነው ሮዳስ ቀለም መኪና ሲጓጓዝ የሚያሳይ ምስል ደርሶናል።
በአሁን ሰዓት ወጣቱ ከህክምና ቦታ ወጥቶ ወደ መቄዶንያ መግባቱ ታውቋል።
በሌላ በኩል ዳለቲ ላይ 42፣ ፉሪ 17 እንዲሁም ገላን ጉዳ ካንተሪ 13 የቀድሞ የድርጅቱ ሰራተኞች ታስረው እንደሚገኙ ሚድያችን ከፀጥታ አካላት አረጋግጧል።
"እስር ቤት ሆነው ድረሱልን እያሉ ነው፣ እኛ ግን እጃችን ታስሯል ምንም ማረግ አንችልም" ያሉት የፀጥታ አንድ የመንግስት የፀጥታ አካል ሁኔታው ብዙዎችን እያሳዘነ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
ከዚህ በታች የታሳሪዎቹን ስም እና ፎቶ አያይዘናል።
1. ጉታታ አበበ
2. ፍራኦል ከበደ
3. ሀይማኖት ጌታቸው
4. መታፈሪያ ደስታ
5. ጥላሁን ማስረሻ
6. መዝገበ ተክለማርያም
7. ተመስገን ታከለ
8. አቤል ግርማ
9. ፍፁም የኋላ
10. ጁሀር ሀሰን
11. ማቲዎስ ጋምቴሳ
12. ደምስ ፈይሳ
13. ሀብታሙ አያሌው
14. አስናቀ ክንፉ
15. ናደው ሙሉጌታ
16. ኪሩቤል ጥጋቡ
17. ሀብተማርያም ወዜ
18. ሀይሌ ነጋሽ
19. መለሰ ሁሩማ
20. አስፋው ዋጋሪ
21. ገመቹ ደበላ
22. ተካልኝ ነጋሳ
23. ገነነ ፈቃዱ
24. አብርሀም ተፈሪ
25. መንሱር (የአባት ስም አልተገኘም)
26. ከበደ "
27. አቢቲ "
28. መሳይ "
29. ፍቅርተ "
ጅፋር “
ሰለሞን “
አብርሃም “
መሳፍንት “
ገብረመድህን ነጋሽ
አዲስ አለም ምህረት
ቴዎድሮስ ፀጋዬ
ከበደ ከተማ
ብዬ ገበየሁ
የወጣት ጉታታ አበበ ታሪክ፣
ወጣት ጉታታ አበበ የሮዳስ ቀለም እና የሱፐር ፋይበር ውሀ ማጠራቀሚያ አምራች በሆነው በሱፐር ደብል ቲ ድርጅት ውስጥ ከአመታት በፊት ይሰራ ነበር።
ይሁንና የድርጅቱ ባለቤት አቶ ፀጋዬ ደበበ ወጣት ጉታታ ከድርጅታቸው ከወጣ እና ሌላ ተመሳሳይ ምርት የሚያመርት ፋብሪካ መስራት ከጀመረ ከሁለት ዓመት በኋላ "1.3 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ቀለም ከለከለኝ" በሚል ከሰሱት።
የአይን እማኞች እንደሚሉት ወጣቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመኖርያ ቤቱ የተወሰደው በድርጅቱ የግል ተሽከርካሪ 'ዶልፊን' መኪና ነው። ለክሱ ምንም የጽሑፍ ማስረጃ አልቀረበም ነበር።
ፍርድ ቤት "በ10 ሺህ ብር ዋስ ይውጣ" ሲል፣ ፖሊስ "አይ፣ ሌላ ክስ አለበት" ብሎ መከልከሉን ጉዳዩን የሚያውቁ ይናገራሉ። በሌላ ክስ የ3 ዓመት ከ7 ወር ተፈርዶበት በይግባኝ ፍርድ ቤት ነጻ እንደለቀቀው ነገር ግን ጉታታ ከማረሚያ ቤት ሊወጣ ሲል የፉሪ ፖሊሶች ከማረሚያ ቤቱ በር ላይ "በሌላ ክስ ትፈለጋለህ" ብለው ማሰራቸው ታውቋል።
በድጋሚ በ4ኛ ክስ 11 ወር ተፈርዶበት ጊዜውን አጠናቆ ሊወጣ ሲል፣ "አይ፣ አሁንም ሌላ ክስ አለ" ተብሎ ዳግም ከእስር እንዳይወጣ ተደረገ። አሁንም 5ኛ ክስ ቦታ በመቀየር "ገላን" አካባቢ ተከፍቶበት እስር ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ባለቤቱም ታስራ እንደነበር፣ አሁን ላይ ለደህንነቷ በመስጋት ተሸሽጋ እንደምትገኝ ምንጮቻችን ያስረዳሉ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ወዳጅ ዘመድ የህግ አካላት ጋር እንዲሁም ኢቢሲ እና ፋናን ጨምሮ ወደ ሚድያዎች ቢሄዱም ምላሽ ሳያገኙ እንደቆዩ ታውቋል።
የወጣት መንክር ጥጋቡ ታሪክ፣
ወጣት መንክር በሱፐር ደብል ቲ ረዘም ያለ ግዜ ከሰራ በኋላ 500 ሺህ ብር ጎሎብሀል ይባላል። ከዛም የገንዘብ መጠኑ ተቀይሮ 2 ሚልዮን ብር ስለጎደለ ክፈል ተብሎ ይያዛል።
"ከተያዘ በኋላ ከባድ ድብደባ ሲደርስበት አምልጧቸው ባህር ዳር ሄዶ ተሸሽጎ ነበር። ይሁንና የድርጅቱ ባለቤት ሂርና የምትኖረውን ባለቤቱን በወታደር አስይዞ ወደ አዲስ አበባ አስመጣት። ይህን የሰማው መንክር ከባህር ዳር ተመልሶ ባለቤቴን ልቀቋት፣ እኔን የፈለጋችሁትን አድርጉኝ" በማለት እጅ መስጠቱን ጉዳዩን የሚያውቁ ይናገራሉ።
በዚህ ግዜ በደረሰበት ከፍተኛ ድብደባ የጀርባ አጥንቱ (spinal cord) ከፍተኛ የነርቭ ጉዳት እንደደረሰበት ታውቋል።
ሚድያችን ከዚህ በፊት እንደዘገበው ጉዳቱ ለመዳን ምናልባትም ከአስር አመት በላይ ሊፈጅ ይችላል።
የዛሬ አመት ገደማ ይህ ከፍተኛ ድብደባ የተፈፀመበት መንክር መጀመርያ ሆስፒታል ገብቶ የነበረ ሲሆን፣ ከዛ በመውጣት አዳማ ፀበል ሲጠመቅ መቆየቱ ታውቋል።
የመሠረት ሚድያ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ ግን የድርጅቱ ባለቤት አቶ ፀጋዬ ወጣቱ ያለበትን ቦታ በማፈላለግ "መሠረት ሚድያ ላይ ክስ ልንመሰርት ስለሆነ መመስከር አለብህ" በማለት እና በገንዘብ በማግባባት ሚድያ ፊት እንዲቀርብ መደረጉ ታውቋል።
ይሁንና ከጋዜጣ መግለጫው በኋላ ወጣት መንክር ከሆስፒታል ወጥቶ ወደ መቄዶንያ መወሰዱን ምንጮቻችን አረጋግጠዋል።
ድርጅቱ ውስጥ የሰሩ ሰራተኞች ሌላ ድርጅት ሄደው ከሰሩ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገቡ ሰራተኞቹ ደጋግመው ያነሳሉ።
"ክስ እንኳን ሲመሰረት እዛው ድርጅት ውስጥ ተመሳስሎ በሚሰራ ዶክመንቶች ነው፣ ምስክር ሆነው የሚቀርቡት ደግሞ የራሱ የድርጅቱ ሰራተኞች ናቸው፣ ለዚህም ከ3ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 20 ሺህ ብር ይከፈላቸዋል። በዚህ መልኩ ወጣቱ አበሳውን እያየ ይገኛል" በማለት የሚናገሩት አንድ የቀድሞ የተቋሙ ሰራተኛ ናቸው።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተገኝተው የነበሩ ጋዜጠኞች ሰኞ የአበል ገንዘብ ይገባላችኋል ተብለው የነበረ ቢሆንም "በሁለት ቢላ የሚበላ ከውስጣችሁ አለ" በማለት ክፍያውን መከልከላቸው ታውቋል።
በዚህ ዙርያ አንድ ተሳታፊ ጋዜጠኛ ያደረሰንን በዕለቱ የታዘበውን እናካፍላችሁ።
ማለዳ ነው፤ ዕለቱ ቅዳሜ።
እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ከሚገኘው ማሪዮት ሆቴል ጎን ሚኒባሶች ተደርድረዋል። መኪኖቹ ጋዜጠኞችን ሸክፈው ወደ ዓለምገና ለመክነፍ ቋምጠዋል። በሱፐር ደብል ቲ ጄኔራል ትሬዲንግ ስምሪት የተሰጣቸው አስተባባሪዎች ወደ ሚኒባሶች የሚገቡ ጋዜጠኞችን ይቆጣጠራሉ።
“አስተባባሪ" ተብለው ከተመደቡ ሰዎች ውስጥ ዋልተንጉሥ አብነህ አንደኛው ነው። በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ ጋዜጠኛ ሆኖ እየሰራ በመገኘቱ እና ለአቶ ጸጋዬ ደበበ የተወሰነ ቅርበት ስላለው የማስተባበር ሃላፊነቱ ተበርክቶለታል። ሌሎችም የድርጅቱ ሰራተኞች በዚሁ የማስተባበል ዘመቻ ውስጥ ሁነኛ ተሳታፊ ናቸው።
እኔ ከተመደብኩበት ሚዲያ ለዚህ ስራ እንድንቀሳቀስ መመሪያ ሲሰጠኝ፣ ሁለት ልብ ሆኜ ነበር። አንዱ ይህ ተቋም በሰራተኞቹ ላይ የሚፈጽመው ዕመቃ እና በደል አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ መሆኑን ግምት ውስጥ አስገብቼ ከዚሁ ጉዞ ለመቅረት ግማሽ ልቤ ወስኖ ነበር።
ሆኖም በዚሁ ጉዞ ሳቢያ የሚኖረው የውሎ አበል ሁኔታ ቀልቤን ስለሳበው ለመጓዝ ልቤ ተነሳሳ። ከዚያም ከምኖርበት ሰፈር ወደ ማሪዮት ሆቴል አካባቢ ሄድኩ። ከዋልተንጉሥ ጋር ሰላምታ ተለዋውጬ ወደ ተመደበልን አንደኛው ሚኒባስ አመራሁ። ሚኒባሱ በጋዜጠኞች ተጠቅጥቋል። ካሜራ የታጠቁ የአሻም እና አርትስ ቲቪ ሰራተኞች ከእነጋዜጠኞቻቸው ይታያሉ። የራዲዮ ጣቢያዎች ሪፖርተሮችም አሉ። በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ የሚጽፉ ግለሰቦችም አልጠፉም።
ይህ ሁሉ የሚዲያ ሰራዊት ነው እሳት ማጥፋት ስራ ላይ የተሰማራው።
ጉዞ ተጀመረ፤ ጉዞ ወደ ዓለምገና።
ዓለምገና ስንደርስ፣ ዓለም ሆቴል ጋ ሚኒባሱ ቆመ። እኛ ብቻ ሳንሆን ሁለቱ ሚኒባሶችም ቦታቸውን ያዙ። ከሚኒባሱ ወርደን ወደ ሆቴሉ የውስጥ ምግብ ቤት ዘለቅን። አረፍ ከማለታችን ጾመኛ መሆን አለመሆናችን ተጠየቅን። እንደማንጾም ስንነግራቸው፣ በደቂቃ ልዩነት ዱለት እና ዕንቁላል ፍርፍር መጣልን። ለስላሳ ተሰጠን። ምግቡን እያጣጣምን፣ ለስላሳውን እየጠጣን ሳለ፣ ከፊት ለፊታችን ታዋቂ ቲክቶከሮችን አየን።
አንደኛው ቲክቶከር "ያያ ዘልደታ" በመባል የሚታወቀው በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ጉዳይ ላይ ግንባር ቀደም ተሰላፊ የሆነው ግለሰብ ነው። "አሃ፣ ያያ ዘልደታ አለ። ጥሩ አበል አለ ማለት ነው" አልን። ከቁርስ በኋላ፣ ከሆቴሉ በስተጀርባ በብዙ ሜትሮች ርቀት ላይ ወደሚገኘው የሱፐር ደብል ቲ ፋብሪካ ቅጥር ግቢ አመራን። የፋብሪካው ግቢ በር ወለል ብሎ ሲከፈት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በየአቅጣጫው ተሰቅሎ ጠበቀን።
ከሚኒባሱ ወርደን በአስተባባሪዎቹ መሪነት ወደተዘጋጀው መድረክ አቅራቢያ ወሰዱን። መስታወት በመስታወት የሆነች ጠባብ ክፍል ውስጥ አስገብተውን ተቀምጠን ለትንሽ ደቂቃ እንድንጠባበቅ ተነገረን። በመጨረሻም የኩባንያው ባለቤት አቶ ጸጋዬ ደበበ በበርካታ ሰዎች ታጅበው መጡ።
ንግግራቸውን ጀመሩ፣ "ይህ ክፍል የኔ ቢሮ ነው። ማንም ይሁን ማን ከፍ ዝቅ አይልም። እዚህ ነው ስራዬን የምሰራው" በአንድ ጥግ የተቀመጡ ዋንጫዎች እና ሰርተፊኬቶችን ገርመም አደረጉና፣ "ከጋዜጣዊ መግለጫው በፊት ፋብሪካውን መጎብኘት አለባችሁ። ጊዜ ሳንፈጅ ወደ ጉብኝቱ እንሂድ" አሉና ፊት ፊት እየመሩን ማስጎብኘት ጀመሩ።
በየክፍሉ፣ በየማምረቻ ስፍራው ተመርጠው የተቀመጡ ሰራተኞች ነበሩ፤ "ንግግር ይችላሉ" የተባሉ። እነርሱ የተወሰነ ነገር ሲናገሩ፣ አቶ ጸጋዬ ጣልቃ ይገቡና ነገሩን ያሰፉታል። እንዲህ እያልን የተወሰነውን የፋብሪካው ክፍል ጎበኘን።
በዚህ ጉብኝታችን ላይ ሁለት ነገሮችን ታዘብኩ። አንደኛው አቶ ጸጋዬ በየንግግሮቻቸው ጣልቃ የሚያስገቡት "የእግዚአብሔር ስም የተመሰገነ ይሁን" የሚለው ቃል ነው። "እንደዛሬው ቀን የእግዚአብሔር ስም በባለሃብት ዘንድ አልተመሰገነም" አልኩ፣ በልቤ።
በተቋማቸው ውስጥ "ብልሹ አሰራር ወይም የስነ ምግባር ጥሰት" የፈጸሙ ሰራተኞችን ተቀጣሪዎቻቸው እንዲጠቁሙ እና እንደየጥፋቱ ደረጃ ታይቶ ለጠቋሚዎች ከ1 ሺሕ እስከ 6 ሺሕ ብር እንዲሸለሙ የሚያነሳሳ ጽሑፍ የለጠፉ ሰው፣ በዕውኑ የእግዚአብሔርን ቃል ተረድተውታልን? አይመስለኝም!
ሲቀጥልም፣ ማስቲካ ላላመጠ፤ ስልክ ላወራ እና ሌሎች "ስሕተቶችን" ለፈጸመ ሰው በሺሕ ብሮች የሚገመት ቅጣት ከደመወዙ ላይ በመቁረጥ መፈጸምም አግባብነቱ ምን ያህል አዋጪ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፤ የሕግ ባለሞያዎችም በጉዳዩ ላይ አስተያየት ቢሰጡበት መልካም ነው።
እንደእኔ አመለካከት ግን፣ አክሳሪ አሰራር ነው፤ ሰራተኞች በትጋት እንዳይሰሩ የሚያደርግ! የደህንነት ካሜራዎችን የሚቆጣጠረው ክፍል ጋ ደረስን። አንዲት ሰራተኛ እንድትናገር አቶ ጸጋዬ ዕድል ሰጧት። በሃይል ትናገር ጀመር።
"ከ400 በላይ የደህንነት ካሜራዎች በግቢው ውስጥ ይገኛሉ። የትኛውንም ዕንቅስቃሴ በካሜራዎቹ እንቆጣጠራለን" እያለች ቀጠለችና፣ "መሰረት ሚዲያ ለምን የድርጅታችንን ስም እንዳጠፋ አውቃለሁ። የፕሮሞሽን ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት ስላላገኘ ነው። በንዴት የውሸት ዜና ሰራ" አለች።
አቶ ጸጋዬ ከእርሷ ተቀብለው የራሳቸውን ሃሳብ ከጨመሩ በኋላ፣ ወደ ሌሎች የስራ ክፍሎች ለጉብኝት ተጓዝን። ለሰዓታት ከአቶ ጸጋዬ ጋር ስንኳትን ቆየን።
በመጨረሻ መባዘኑ አበቃና ወደ ጋዜጣዊ መግለጫው አመራን። ስለጋዜጣዊ መግለጫው ይዘት የምናገረው ተጨማሪ ዕሴት ያለው መረጃ የለም። ነገር ግን የመድረክ አስተዋዋቂው ለሁለት ጋዜጠኞች ብቻ የጥያቄ ዕድል እንደሚሰጥ ቢናገርም፣ የትኛውም ጋዜጠኛ ለጥያቄ እጁን አላነሳም። በጥቅሉ፣ የነበረው ጉብኝትም ሆነ የአቶ ጸጋዬ ገለጻ የሚያሳብቀው ነገር ቢኖር፣ በመሰረት ሚዲያ በኩል የተሰራጨው መረጃ ትክክለኛ መሆኑን ነው።
ከንግግራቸው እና ከእጅ አወናጫጨፋቸው አንጻር፣ አቶ ጸጋዬ ስሜታዊነት ይንጸባረቅባቸው ስለነበር፣ ምናልባት "ለምን ተጋለጥኩ?" የሚል ቁጣ በውስጣቸው ይንተከተክ እንደነበር ገምቼአለሁ። በሌላ በኩል፣ "ምስክርነት" የሰጡት ሰራተኞች ገጽታ ላይ የሚስተዋለው የመገደድ እና የፍርሃት ስሜት ጥርጣሬያችንን የጨመረ እንጂ የቀነሰ አይደለም።
ዥጉርጉር የወታደር መለዮ የለበሱ የፋብሪካው ዋርድያዎች እኛን እየተከተሉ እግር በእግር የምናወራውን ነገር ሁሉ ለማዳመጥ የነበራቸው ጉጉት በጣም አሰቃቂ ነበር።
ሁሉም ነገር ተጠናቅቆ ዓለም ሆቴል ገብተን ምሳችንን እየበላን ሳለ፣ አስተባባሪው ዋልተንጉሥ አብነህ መጣና ወደ አንድ መነጽር ያደረገ፤ ጸጉሩን እንደአቤሴሎም የሚያዘናፍል ባለሃብት ሰው ጣቱን ቀስሮ፣ "ክፍያውን እርሱ ይጨርሳል። እናንተ አታስቡ፤ ሰኞ ይከፈላችኋል" አለን። ውስጣችን በተስፋ እና ስጋት ተሞላ።
ተስፋው ሰኞ ብሩን ወደ አካውንታችን ለማስገባት ሰዎቹ ይተጉ "ይሆናል" የሚል ሲሆን፣ ስጋቱ "አጠቃላይ ለክፍያ የተመደበው ብር ዋልተንጉስ አፍኖ ይዞ በኋላ ላይ ለጓደኞቹ ብቻ ከፍሎ፤ እኛን ቢተወንስ?" የሚል ነበር።
ለቲክቶከሮቹ ያያ ዘልደታ እና ለጓደኛው በነፍስ ወከፍ 100 ሺሕ ብር እንደተከፈላቸው ስለሰማን፣ ተስፋችንን ሙሉ በሙሉ አልቆረጥንም፤ "ለእኛም ይዘንማል" በሚለው ፈሊጥ! በዚህ የስሜት ሁኔታ ውስጥ ነበር ወደ አዲስ አበባ የተመለስነው። የሆነው ሆኖ የአንድ ቀን ልፋታችን እንዳልሰመረ እንኳን እኛ፤ እናንተ አንባቢዎቻችን ጭምር የታዘባችሁት ነው።
ዕውነት ጉልበቷ የማይበገር፤ ጥልቀቷ የማይመተር መሆኗን ያሳየ ክስተት ነው። በርግጥም፣ "ማስተባበያው ማስተባበል አልቻለም"!
-መሠረት ሚድያ-















