በቅርቡ ለመንግስት እጃቸውን የሰጡት ኮ/ል ፈንታው ሙሀቤ በዛሬው ዕለት በሽብር ወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈባቸው
(መሠረት ሚድያ)- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ አንደኛ የሕገ-መንግሥት እና የፀረ-ሽብር ወንጀል ችሎት ዛሬ በዋለው ችሎት በቅርቡ ለመንግስት እጃቸውን የሰጡት ኮ/ል ፈንታው ሙሀቤ ላይ በሽብር ወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላለፈ።
የመሠረት ሚድያ ምንጮች እንዳረጋገጡት ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሞት በሚያስቀጣው ክስ ዛሬ ጥፋተኛ የተባሉት ኮ/ል ፈንታው ችሎት ላይ አልተገኙም ነበር።
የክሱ መዝገብ እንደሚያስረዳው ከሦስት ዓመት በፊት በአማራ ክልል የተከሰተውን የፖለቲካ አለመረጋጋት ተከትሎ ሕገ- መንግሥቱን በኃይል ለመናድ የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርገው ተንቀሳቅሰዋል በሚል ኮ/ል ፈንታው በሽብር ወንጀል ተከሰው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲፈለጉ ቆይተዋል።
ግለሰቡ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በጋዜጣ ጥሪ ቢያደርግላቸውም ሊገኙ ባለመቻላቸው የቀረበባቸውን ክስ መከላከል አልቻሉም በሚል በዛሬው ዕለት ከአስራ አምስት ዓመት እስከ ሞት በሚደርስ የወንጀል ቅጣት ጥፋተኛ ሆነዋል ሲል ፍርድ ቤቱ በይኗል።
የአፋህድ ምክትል ሊቀመንበር እና ወታደራዊ ዋና አዛዥ እንደነበሩ የሚነገርላቸው ኮ/ል ፈንታው ሙሀቤ የሰላም አማራጭን ተቀብለው ለመንግስት እጅ መስጠታቸው የዛሬ ወር ገደማ ይፋ መደረጉ ይታወቃል።
ኮሎኔል ፋንታሁን ጥፋተኛ የተባሉት በእነ ዶክተር ወንደሰን አሰፋ፣ መስከረም አበራ፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ እና ጋዜጠኛ ዳዊት በጋሻው በሚጠራው መዝገብ ስር ተከሰው ነው።
በዚሁ የክስ መዝገብ ጋዜጠኛ ገነት አስማማው፣ ዶ/ር ሲሳይ አውግቸው፣ የሕግ ጠበቃ አለልኝ ምሕረቱ፣ መዓረጉ ቢያበይን እና ዶ/ር ግብረዓብ አለሙ በተመሳሳይ የሽብር ወንጀል የቀረበባቸውን የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን ሰጥቷል።
51 ተከሳሾችን በያዘው በዚህ መዝገብ ስድስት ተከሳሾች ዓቃቤ ሕግ ያቀረበባቸውን ማስረጃ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነፃ መሰናበታቸውን የመሠረት ሚዲያ ምንጮች ተናግረዋል። እነዚህ ተከሳሾች ከሦስት ዓመት በላይ በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ ይገኛል።
ከአማራ ክልል የፀጥታ መደፍረስ ጋር ተያይዞ በተመሳሳይ ሦስት መቶ የሚሆኑ ተጠርጣሪዎች ጉዳያቸው በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየታየ ነው።
-መሠረት ሚድያ-





ሽብር ተኛው እንዴት ሽብርተኛ ብሎ መክሰስ ይችላል እንዴ