የአማራ ማህበር በአሜሪካ የመንግስት ሀይሎች ከትናንት ጀምሮ በተኮሷቸው ከባድ መሳርያዎች እና በአየር ድብደባ በንፁሀን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማስከተላቸውን አስታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ባለፉት ጥቂት ቀናት የመንግስት ሀይሎች በአማራ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ከበርካታ አካባቢዎች ለቀው መውጣታቸውን ተከትሎ የፋኖ ሀይሎች የያዟቸውን ቦታዎች ማስፋታቸው እየተሰማ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግስት መጠነ ሰፊ የድሮን ጥቃት እየፈፀመ እንደሚገኝ ለሚድያችን የደረሱ ጥቆማዎች ያሳያሉ።
የአማራ ማህበር በአሜሪካ ዛሬ ለመሠረት ሚድያ የላከው መግለጫ እንደሚያሳየው መንግስት በአማራ ክልል እና በአጎራባች አካባቢው ህዝብ በሚበዛባቸው ከተሞች ንፁሀን ላይ 'ያልተመጣጠ' ሀይል ተጠቅሟል።
ከየካቲት 4 ቀን ጠዋት ጀምሮ የደቡብ ጎንደር ዞን የአስተዳደር ማዕከል በሆነችው በደብረ ታቦር ከተማ መሐል እና በመኖሪያ ሰፈሮች ላይ የመንግስት ኃይሎች የአየር ድብደባ እና ከባድ መሣሪያ መተኮሳቸውን የአማራ ማህበር በአሜሪካ አስታውቋል።
"በአሁኑ ወቅት ባለው መረጃ መሠረት በወባባ (ጤና ሳይንስ ኮሌጅ አቅራቢያ)፣ በወይበላ ማርያም፣ በአየር ማረፊያ፣ በርብ ወንዝ፣ በቄራ ኡራኤል ቤተክርስቲያን እና በወርቅን ቀበሌ አቅራቢያ የአየር ድብደባዎች እንደደረሱ መረጃዎቻዎች ገልጸዋል" ያለው ማህበሩ በተጨማሪም እነዚህ ጥቃቶች በንፁሀን ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳትን አስከትለዋል ብሏል።
"በመኖሪያ ቤቶች እና በሕዝብ ትምህርት ቤቶች ላይ ከፍተኛ ውድመት አስከትለዋል። ነገር ግን በቀጠለው የበየነ መረብ መገናኛ መስተጓጎል ምክንያት የደረሰው ሞትና የንብረት ኪሳራ ትክክለኛ መጠን ሊረጋገጥ አልቻለም። በተጨማሪም የፋኖ ደጋፊዎች ናችሁ በሚል ሰበብ በአካባቢው ነዋሪዎች ላይ ሰፊ እስር እየተፈጸመ እንዳለ የአማራ ማህበር በአሜሪካ መረጃዎች ደርሰውታል" ብሏል።
ማህበሩ ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች መንግስት እየተጠቀመ ያለውን የንፁሀንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል ያልተመጣጠነ ኃይል እንዲያወግዙ፤ መንግስት እያደረሰ ያለውን ጥቃት እንዲያቆም፣ የሰብአዊ መብቶች እንዲያከብር፣ ያለአግባብ የታሰሩ ግለሰቦች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና የበየነ መረብ መገናኛ ወደ ነበረበት እንዲመልስ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል።
-መሠረት ሚድያ-



