ማን እንደሆነ እና የት እንዳለ ያልታወቀ ግለሰብ በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው የክስ መዝገብ ዛሬ የዓቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ ድምፁ ከርቀት በማይክራፎን ችሎት ላይ ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው የክስ መዝገብ የፌደራሉ ዓቃቤ ሕግ አንድ ምስክር ከመጋረጃ ጀርባ ሆኖ ቃሉ እንዲሰማልኝ በሚል ለፍርድ ቤቱ ባቀረበው አቤቱታ መሰረት ፍርድ ቤቱ ምስክሩን ከመጋረጃ ጀርባ ለመስማት በይኖ ነበር።
ተከሳሾቹ በበኩላቸው ብይኑን ተቃውመው ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቢሉም ጠቅላይ ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤቱን ብይን አፅንቶ ዛሬ ይሄው የዓቃቤ ሕግ ምስክር ተሰምቷል።
ቀደም ሲል በነበረው የፍርድ ቤቶች አሰራር ከመጋረጃ ጀርባ የሚመሰክረው ግለሰብ እንዳይታይ ችሎቹ ውስጥ ጊዚያዊ መጋረጃ ይዘረጋል፣ ሁለቱ ተከራካሪ ወገኖችም በቀጥታ ጥያቄ እንዲጠይቁ ይደረጋል።
ይህ አሰራር በአዲስ አበባ ሁከትና እና ብጥብጥ አስነስታችኋል በሚል እነ አቶ እስክንደር ነጋ በተከሰሱበት ወቅት በግልፅ ተግባራዊ ተደርጎ እንደ ነበር ይታወሳል።
በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ግን ከመጋረጃ ጀርባ ይመሰክራል የተባለው የዓቃቤ ሕግ ምስክር እንደዚህ ቀደሙ በችሎት መጋረጃ ተዘጋጅቶ ሳይሆን ምስክሩ የት እንዳለ ሳይታወቅ ድምፁ ችሎት ውስጥ በማይክሮፎን እንዲሰማ ብቻ ተደርጓል።
ተከሳሾቹ በበኩላቸው ድምፁ የተፈጥሮ ሰው ሳይሆን የሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) ሊሆን ይችላል በሚል የተቃወሙት ሲሆን ተከሳሾቹ አክለውም "ምስክሩ ሰው ነው ቢባል እንኳን የት እና ከማን ጋር ሆኖ የምስክርነት ቃሉን እየሰጠ እንደሆነ አይታወቅም፣ ቃለ መሀላስ ፈፅሟል ወይ? ሌላ ቦታ ሆኖ የሚሰጥ ከሆነ ከችሎቱ ቁጥጥር ውጭ ሆነ ማለት አይደለም ወይ?" ሲሉ ለችሎቱ አመልክተዋል።
የችሎቱ ዳኞች የተከሳሾችን አቤቱታ በመስማት አንዱ የችሎት ዳኛ ተነስተው የዓቃቤ ሕግ ምስክር ቃሉን ከሚሰጥበት ስፍራ ሆነው ምስክሩ ብቻውን እና የሚነበብ ወረቀት አለመያዙን አረጋግጠው በአንድ ላይ እንዲቀመጡ ተደርጎ ሁለቱ ዳኞች በችሎት ተሰይመው ምስክሩ ቃሉን እንዲሰጥ ተደርጓል።
መሠረት ሚዲያ ዓቃቤ ሕግ በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና ክርስቲያን ታደለ ላይ ያሰማው ምስክር በዓቃቤ ሕግ ቢሮ ውስጥ ተቀመጦ ቃል መስጠቱን አረጋግጧል።
ዓቃቤ ሕግ ከአስራ ሰባት በላይ ምስክሮችን ያሰማ ሲሆን ሁሉም ምስክሮች የመከላከያ ሰራዊት እና የፌደራል ፖሊስ አባላት ናቸው። በዛሬው ዕለት የቀረበው ምስክር የመከላከያ ሰራዊት ወይም የፌደራል ፖሊስ አባል ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር የለም።
በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ የሕገ- መንግስት እና ፀረ-ሽብር አንደኛ ወንጀል ችሎት ጉዳያቸው እየታየ በሚገኘው በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና በአቶ ክርስቲያን ታደለ የክስ መዝገብ አስራ ስድስት ተከሳሾች ውስጥ የቀድሞው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ሊቀመንበር ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል እና የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ መምህር ካሳ ተሻገር (ዶ/ር) እና መሪጌታ በላይ አዳሙ ይገኙበታል።
-መሠረት ሚድያ-



