"ችግኝ መትከል ለፖለቲካ ዓላማ መሳርያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ግን ለፖለቲካ ዓላማ ስለሚውል ብቻ የግዴታ መቃወም አለብን ማለት አይደለም"
በዞራን አባይ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- መንግስት ላለፉት ዓመታት እያካሄደ ያለው ሰፊ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ትልቅ ተቃውሞ ይቀርብበታል። አንደኛውና ዋነኛው የመቃወሚያ ምክንያት ደግሞ "ችግኝ ተከላው የፖለቲካ ዓላማን አንግቦ የተነሳ ፕሮግራም እንጅ ለሕዝብ የታሰብ ፕሮጀክት አይደለም!" ሚለው ነው።
በሌላ በኩል "ከችግኝ ተከላ በፊት ሌሎች ችግሮች ቅድሚያ ይሰጣቸው!" ሚሉም አሉ።
በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ተቃውሞ በአገራችን ሲሰማ የመጀመርያ አይደለም። ከዓመታት በፊት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ድንጋይ ሲቀመጥ በተመሳሳይ ተቃውሞ አስተናግዶ ነበር።
እንደውም የሕዳሴ ግድቡ በውጭ አገር በጠንካራ ሰልፎች የታገዘ ተቃውሞ ነበር ያስተናገደው። የተቃውሞ መነሻው ደግሞ "ግድቡ ከሕዝብ ድጋፍ ለማግኘትና ለፖለቲካዊ ትርፍ ታቅዶ ሚሰራ እንጅ ሕዝቡን ለመጥቀም አይደለም" ሚል ነበር። "ግዙፍ ግድብ ከመስራታችን በፊት ለፖለቲካዊ ችግሮቻችን ቀድመን መፍትሔ እንስጥ!" ሚሉም ነበሩ።
መንግስታት ይሄዳሉ ይመጣሉ። የትኛውም መንግስት ግን ምሉዕ በሚባል መልኩ ለዜጎች ምቹ አይሆንም። በተለይ አገራችንን ጨምሮ ወደ አብዛኛው የአፍሪካ አገራት ስንመጣ ደግሞ የተደራረቡና የተወሳሰቡ ችግሮች ሳጠራ እንደመሆናችን ምሉዕ ቀርቶ ግማሽ ምቹነት ማምጣት ከባድ ነው።
ግን በዚህ መሐል መንግስታት ሚሰሯቸው የተለያዩ ፕሮግራሞች ይኖራሉ።
ከእነዚህ ፕሮግራሞች ውስጥ ዓላማቸው ለምንም ጉዳይ ይሁን ካለንበት ሁኔታ አኳያ ሲገመገሙ ልንቃወማቸው ማይገቡ ዘመን ተሻጋሪ ሐሳቦች ይገኛሉ።
ለምሳሌ የንጉሡ መንግስት ትምህርት ላይ፣ የደርግ መንግሥት ትላልቅ እርሻ ማስፋፋት ላይ፣ እንዲሁም መሠረት ትምህርትና ችግኝ ተከላ ላይ ኢህአዴግ ደግሞ መሠረተ ልማትና የሕዳሴ ግድቡን በድፍረት ማስጀር ላይ የሰሩት ስራ ያለቅድመ ሁኔታ ድጋፍ ይገባቸዋል።
ከዚህ አንፃር ስንመለከተውም ችግኝ መትከል ለፖለቲካ ዓላማ ሊውል ይችላል። ፖለቲካን አደገኛ ከሚያደርገው ባህሪዎች አንዱም አንድ ፖለቲከኛ የትኛውንም አጀንዳ ለፖለቲካ ዓላማው ጠምዝዞ መጠቀም እንዲችል ስለሚያደርግ ነው። ስለዚህ ችግኝ መትከልም ለፖለቲካ ዓላማ መሳርያ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። ግን ለፖለቲካ ዓላማ ስለሚውል ብቻ የግዴታ መቃወም አለብን ማለት አይደለም።
አንድ ግዜ አንድ ትልቅ አባት ስለ መፅሐፍ ቅዱስ ሲናገሩ "አንዳንድ ሰዎች መፅሐፍ ቅዱስ የሐሰት መፅሐፍ ነው ሲሉ ይናገራሉ፤ በእርግጥ መፅሐፍ ቅዱስ የሐሰትት መፅሐፍ አይደለም! ነገር ግን መፅሐፍ ቅዱስ የሐሰት መፅሐፍ ቢሆን እንኳ የዓለማችን ምርጡ ሐሰት ነው ሚሆነው" ብለው ነበር።
በተመሳሳይ ችግኝ መትከልም ፖለቲካ ሊሆን ይችላል፤ ላይሆንም ይችላል። ነገር ግን ችግኝ መትከል ፖለቲካ ቢሆን እንኳ የዓለማችን ምርጡ ፖለቲካ ነው ሚሆነው።
****መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
መረጃን ከመሠረት!


