ከካዛንችስ እና ፒያሳ በኮሪደር ልማት ተፈናቅለው ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ ሰፍረው የሚገኙ ዜጎች ካሉበት ቦታ በሶስት ቀን ውስጥ ልቀቁ ተባሉ
(መሠረት ሚድያ)- በኮሪደር ልማት ምክንያት የመኖርያ ቦታቸው የፈረሰባቸው እና ወደ ፈረንሳይ ለጋሲዮን አካባቢ በመሄድ ሰፍረው የነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አሁን ካሉበት ቦታም በአስቸኳይ እንዲነሱ ተነገራቸው።
እነዚህ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ጉራራ ኪዳነምህረትን አልፎ 'አንቁርጫ' የሚባል ሰፈር ኑሯቸውን ያደረጉ የከተማ ውስጥ ተፈናቃዮች ለመሠረት ሚድያ በሰጡት ቃል አሁን የት እንደሚሄዱ ግራ እንደገባቸው ተናግረዋል።
"ትላንት ምንም ሳያሳውቁን መጥተው ቀለም ቀቡ፣ እዚህ ደግሞ ህዝቡ ከፒያሳ፣ ከቤላ፣ ከሽሮሜዳ፣ ከተክለሀይማኖት፣ ከካሳንችስ እና ከዜሮ አምስት ተፈናቅሎ እየኖረ ነው" የሚሉት አንድ ተፈናቃይ አሁን ተነሱ መባሉ ብዙ ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
"ይሄ ሁሉ ህዝብ ተፈናቅሎ ሲመጣ የተከራየው እዚሁ አንቁርጫ ነው፣ እጅግ በጣም ብዙ ህዝብ ነው የሚኖረው። አሁን ግን ማስጠንቀቂያ እንኳን ሳይነግሩን ሊያፈርሱት ነው። ወዴት እንሂድ? ብዙ ነብሰጡር ሴቶች በድንጋጤ ታመዋል። ሰፈሩ በጣም ብዙ ህዝብ ነው ያለው፣ ግራ ገብቶናል" በማለት ፎቶ እንኳን እንዳያነሱ በፖሊስ ሰፈሩ ታጥሮ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
ሚድያችን ያናገራቸው ሌላኛው ተፈናቃይ ደግሞ ትላንት 5 ሰአት ላይ የመንግስት ሰዎች ቀለም ቀብተው ሄደው ለዛሬ ስብሰባ እንደጠሩ ይገልፃሉ።
"በዚህ 3 ቀን ውስጥ ለቃችው ውጡ፣ ያላችሁ ቀን እስከ እሮብ ነው" ተብለናል የሚሉት ግለሰቡ እቃቸውን ሰብስበው በፍጥነት እንዲወጡ መታዘዛቸውን እና ሀሙስ ተመልሰው ሲመጡ አንድም ነገር ማውጣት እንደማይችሉ መነገሩን አስረድተዋል።
"ቢያንስ ትንሽ ቀን ስጡን ብለን ብንለምን ፖሊስ ደብድቦ አባረረን። የእውነት በጣም ብዙ ሰው በጭንቀት ታሟል፣ የካ ክፍለ ከተማ መልስ ቢሰጡን ብለን ሄድን፣ እዛም በቃ ይፈርሳል ከተባለ ምንም ማድረግ አይቻልም ሁሉም የልማት ተነሽ ነው ብለው አባረሩን። አንዱ እንደውም እባካችው ብሎ ሲለምን ድብደባ ተፈፅሞበታል" በማለት አስረድተዋል።
በዚህ ዙርያ የየካ ክፍለ ከተማ ሀላፊዎችን በስልክ ለማናገር ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም፣ ምላሽ ካገኘን እንመለስበታለን።
ፎቶ: ፋይል
መረጃን ከመሠረት!



