በሃዋሳ ከተማ የሀይቅ ዳር ልማት እና የነዋሪዎች የህልውና አደጋ: የፍትህ ያለህ የሚሉ ዜጎች አቤቱታ
(መሠረት ሚድያ)- በሃዋሳ ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ፊላደልፊያ ቀበሌ ውስጥ በተለምዶ የወንዝ ዳር የታጋይ መንደር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ ዜጎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግስት እየተካሄደ ካለው የሀይቅ ዳር የኮሪደር ልማት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የህልውና አደጋ እንደተጋረጠባቸው በማሳወቅ ላይ ይገኛሉ።
እነዚህ ነዋሪዎች በአካባቢው ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ማለትም ከሀምሳ ሁለት ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ማህበራዊ ህይወታቸውን የመሰረቱ፣ ትውልድ ያፈሩ እና አካባቢውን በራሳቸው አቅም ያለሙ ዜጎች መሆናቸው ይነገራል።
ይሁን እንጂ አሁን ላይ መንግስት ልማትን በማስታከክ ያለምንም የካሳ ክፍያ እና የምትክ መሬት ዝግጅት መኖሪያ ቀያቸውን ጥለው እንዲወጡ እያስገደዳቸው መሆኑን በከፋ የሀዘን ስሜት እየገለጹ ይገኛሉ።
ነዋሪዎቹ እስከ ሁለት ሺህ ዓመተ ምህረት ድረስ ለመንግስት የሚጠበቅባቸውን የቦታ እና የእርሻ ግብር በህጋዊ መንገድ ሲከፍሉ የቆዩ ቢሆንም ከዛ ጊዜ በኋላ ግን መንግስት ያለምንም ግልጽ ምክንያት ግብር እንዳይከፍሉ ማገዱን ያስታውሳሉ።
"ይህ ብቻ ሳይሆን ማህበረሰቡ ከራሱ ጉሮሮ እየነጠቀ ባዋጣው ገንዘብ የመብራት መስመር፣ የውሃ አቅርቦት እና አልፎ ተርፎም የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ግንባታን ሙሉ በሙሉ በራሱ ወጪ አከናውነናል" ብለው ለመሠረት ሚድያ ቃላቸውን የሰጡት ነዋሪዎች ከተማዋ ስትሰፋ እና ለሌሎች አካባቢዎች የካርታ ፕላን ሲዘጋጅ ለእነርሱም መሰል ህጋዊ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ከአስተዳደሩ ሲሰጣቸው የነበረው ምላሽ ግን አርፋችሁ ተቀመጡ የሚል የንቀት እና የማግለል ምላሽ እንደነበር በምሬት ይናገራሉ።
"ችግሩ ይበልጥ የተባባሰው በቅርቡ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ነው። የልማቱ አካል የሆነውን የኮሪደር ስራ ምክንያት በማድረግ የአካባቢው አመራሮች ነዋሪዎቹ በአጭር ቀናት ውስጥ በተለይም በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ የቃል ትዕዛዝ አስተላልፈዋል" ብለው ሌላ ነዋሪ ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ከዚህም ባለፈ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አመራሮች "በመካከላችሁ አቅም ያላቸው ነዋሪዎች አሉና ገንዘብ በማዋጣት አቅም ለሌላቸው የሁለት ወር የቤት ኪራይ ክፈሉ" የሚል ኃላፊነት የጎደለው እና ህዝብን ያላገናዘበ አስተያየት መስጠታቸው ነዋሪዎቹን በእጅጉ አስቆጥቷል።
ይህ አካሄድ ዜጎችን ከመንግስት እና ከመሪዎቻቸው ጋር እምነት እንዲያጡ ያደረገ ትልቅ አስተዳደራዊ ስህተት መሆኑን ነዋሪዎቹ ያሰምሩበታል። የከተማው አስተዳደር መውሰድ የነበረበትን ኃላፊነት በህዝቡ ጫንቃ ላይ ለመጫን መሞከሩ እጅግ አሳዛኝ ክስተት ሆኖ አልፏል።
ነዋሪዎቹ የከተማዋን ልማትም ሆነ የሀይቅ ዳር ፕሮጀክቱን እንደማይቃወሙ እና እንዲያውም እንደሚደግፉ በግልጽ ያሳውቃሉ። ነገር ግን ማንኛውም የልማት ስራ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት፣ ክብር እና የንብረት ባለቤትነት ህግን በተከተለ መልኩ መከናወን እንዳለበት አጥብቀው ያምናሉ።
"የኢትዮጵያ ህገ መንግስት የዜጎችን የንብረት መብት በግልጽ ያረጋገጠ ሲሆን የህዝብ መሬት ለልማት ሲወሰድ በቅድሚያ ማሳወቅ፣ ፍትሃዊ ካሳ መክፈል እና ምቹ የመቀየሪያ ቦታ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን የመሬት ለልማት የመጠቀም አዋጅ በግልጽ ያስቀምጣል" በማለት ሚድያችን ያናገራቸው እና ስሜ አይጠቀስ ያሉ የህግ ባለሙያ ያሰምሩበታል።
"አሁን በሃዋሳ ከተማ እየተፈጸመ ያለው ድርጊት ግን እነዚህን ሁሉ ብሄራዊ ህጎች የጣሰ እና ቤተሰብን በትኖ የዜጎችን የመኖር ህልውና አደጋ ላይ የጣለ ተግባር ነው። ለሃዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጥራቱ በየነ እና ለሌሎችም አግባብነት ላላቸው አስተዳደራዊ ቢሮዎች በተለያዩ ወራት ተደጋጋሚ የቅሬታ ደብዳቤዎች ቢገቡም እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት ተገቢ፣ ግልጽ እና ህጋዊ ምላሽ አልተሰጠም" በማለት ጉዳዩን አስተድተዋል።
አክለውም "በከንቲባው ተቋቁሟል የተባለው የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴም ቢሆን በአካባቢው ተገኝቶ ህዝቡን በቀጥታ የማነጋገርም ሆነ የችግሩን ስፋት የመረዳት ስራ አልሰራም። በመሆኑም ማህበረሰቡ ይህ አስተዳደራዊ በደል በአስቸኳይ እንዲቆም፣ ከንቲባው በአካል ተገኝተው ህዝቡን በክብር እንዲያወያዩ እና በህጉ መሰረት የካሳ እና የምትክ ቦታ ዝግጅት እንዲደረግላቸው አጥብቀው እየጠየቁ ይገኛሉ" ብለዋል።
ይህ የህግ ጥሰት የማይታረም እና ፍትህ የማይሰጣቸው ከሆነ ጉዳዩን ወደ ኢፌድሪ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ወደ ህዝብ እንባ ጠባቂ እና ወደ ሌሎችም ከፍተኛ የህግ አካላት ይዘው ለማምራት እንደሚገደዱ ነዋሪዎቹ በአጽንኦት አሳስበዋል።
በዚህ ዙርያ የሐዋሳ ከተማ አስተዳደርን ለማነጋገር ያረግነው ሙከራ አልተሳካም።
| መሠረት ሚድያ |



