የአዲስ ስታንዳርድ አታሚ በዋና አዘጋጁ ላይ እገታ፣ በስቱዲዮው ላይ ወረራ መፈፀሙን ጠቅሶ ከቢሮው እንዲለቅ ትእዛዝ መተላለፉን አስታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- የአዲስ ስታንዳርድ አታሚ የሆነው ጃኬን (JAKENN) ፐብሊሺንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በዋና አዘጋጁ ላይ እገታ፣ በቢሮው ላይ ደግሞ በተፈጸመ ድንገተኛ ፍተሻ እና በግዴታ ቦታ የመልቀቂያ ትእዛዝ ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።
ተቋሙ መግለጫውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ ለዲፕሎማቶች፣ ለሰብአዊ መብትና ለፕሬስ ነፃነት ተሟጋች ድርጅቶች እንዲሁም ለህዝብ ይፋ አድርጓል።
እንደ መግለጫው ከሆነ ቅዳሜ ሐምሌ 25 ቀን 2018 ዓ.ም የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ ዮናስ ከድር በፀጥታ አካላት ታግቶ፣ አካላዊ ጥቃት ተፈፅሞበት እና ለ24 ሰዓታት ያህል ጥብቅ ምርመራ ሲደረግበት ቆይቶ ተለቋል።
ዋና አዘጋጁ ከተለቀቀ በኋላ ለተቋሙ የህግ ቡድን ዝርዝር የቃል ምስክርነቱን የሰጠ መሆኑን የጠቀሰው ተቋሙ ይህም ለህጋዊ ሂደቱ መዝገብ አካል ሆኖ ተይዟል ብሏል።
በማግስቱ እሁድ ሐምሌ 26 ቀን የታጠቁ የፀጥታና የደህንነት አባላት ያለ ሕጋዊ አሰራር ወደ ቢሮው በመግባት ከመልቲሚዲያ ስቱዲዮ በርካታ ፕሮፌሽናል 4ኬ ካሜራዎችን፣ ማይክሮፎኖችን፣ የድምፅና የቪዲዮ ማቀናበሪያዎችን እና የቅንብር መሳሪያዎችን በቁጥጥር ስር አውለዋል ያለው ጃንኬን በተጨማሪም የስቱዲዮ መብራቶችና መለዋወጫዎች ላይ ሆን ተብሎ ውድመት መፈፀሙን የአስተዳደር ክፍሉና የሕንፃው አስተዳደር ባደረጉት ኦዲት አረጋግጠዋል ብሏል።
የሕግ ቡድኑ ይህ ውሳኔ የውል ስምምነትን የሚጥስና ሕጋዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ ውድቅ ለማድረግ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል
"ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን ደግሞ ተቋሙ ላለፉት 16 ዓመታት የተከራየበት ሕንፃ አከራይ በፖሊስ አካላት ተገዶ በሶስት ቀናት ውስጥ ቢሮውን እንዲለቅ የሚያስገድድ ማስታወቂያ ሰጥቶታል። የሕግ ቡድኑ ይህ ውሳኔ የውል ስምምነትን የሚጥስና ሕጋዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ ውድቅ ለማድረግ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል" በማለት ይፋ አድርጓል።
እነዚህ አጋጣሚዎች የተከሰቱት ተቋሙ የኢትዮጵያ ሚዲያ ባለስልጣን የአዲስ ስታንዳርድን የኦንላይን ሚዲያ ምዝገባ ሰርተፊኬት ለመሰረዝ ያሳለፈውን ውሳኔ በሕግ ለመቃወም በሚንቀሳቀስበት ወቅት መሆኑ የታወቀ ሲሆን ተቋሙ የባለስልጣኑ ውሳኔ ሕገ-ወጥ ነው ብሎ እንደሚያምን ገልጿል።
እነዚህ ክስተቶች የነጻ ሚዲያዎችን ደህንነትና የሕግ የበላይነትን አደጋ ላይ የሚጥሉ በመሆናቸው አሳሳቢ መሆናቸውን ድርጅቱ አስታውቋል።
በመሆኑም የፍትህ ሚኒስቴር፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የሚመለከታቸው አካላት ድርጊቱን በገለልተኝነት እንዲመረምሩ፣ ሕጋዊ መሰረቱን እንዲያብራሩና ጥፋተኞችን ለሕግ እንዲያቀርቡ ጠይቋል።
በመጨረሻም ጃኬን ፐብሊሽንግ እና አዲስ ስታንዳርድ የሚደርስባቸው ተፅዕኖ ቢኖርም ገለልተኛና ህዝባዊ ጥቅም ላይ ያተኮረ ጋዜጠኝነትን የማቅረብ ቁርጠኝነታቸው የማይወላወል መሆኑን በመግለጽ መብታቸውንና የሰራተኞቻቸውን ደህንነት ለማስጠበቅ ሕጋዊ መንገዶችን ሁሉ እንደሚከተሉ በመግለጫው ጠቅሰዋል።
| መሠረት ሚድያ |


