የጤና ሚኒስቴር ለጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎች መፍትሔ ለመስጠት ሒደት እንደጀመረ አስታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ሰሞንኛውን የጤና ባለሙያዎችና ሰራተኞች ጥያቄዎችን በተመለከተ የጤና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነትና ጤና ኮሚኒኬሽን ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ተገኔ ረጋሳ በሰጡት ማብራርያ የአጭር፣ የመካከለኛ የረጅም ጊዜ ዕቅድ ይዞ ለችግሮች መፍትሔ ለመስጠት በሒደት ላይ እንደሚገኝ ተናገሩ።
"በጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች የሚነሱ ጥያቄዎች ተገቢና ዕውቅና የምንሰጣቸው ናቸው" ብለው ለሪፖርተር የተናገሩት ዶ/ር ተገኔ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር በቀጥታ የማይገናኝ ማበረታቻ ወይም (Non Salary Incentives) ለጤና ባለሙያውና ለሠራተኛው ጠቀሜታው የጎላ ነው ተብሎ ተለይቶ እየተሠራበት ያለ አንዱ ፓኬጅ ነው ብለዋል።
የደመወዝ ጭማሪ የጤና ባለሙያውንና ሠራተኛውን ጥያቄ ብቻውን ይመልሳል ብለው እንደማያምኑ ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል። የመኖሪያ ቤት ጉዳይ ዋነኛ ከሆኑ ጥያቄዎች አንዱ ነው ያሉት ዶ/ር ተገኔ ፣ የጤና ባለሙያውና ሠራተኛው አገልግሎት እየሰጡ ባሉበት አካባቢ መኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው የሚደረጉ ውይይቶች አሁንም ቀጥለዋል ብለዋል።
ለአብነት ያህል የኦሮሚያ ክልልና አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለዚህ ጥያቄ ምላሽ ከሰጡት መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልጸዋል። ይኼ ጥያቄ በኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ለኦሮሚያ ሥራና ከተማ ልማት ቢሮ የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች በያሉበት የቤት መሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ለአፈጻጸም ውሳኔ መተላለፉን አክለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በተመሳሳይ የጤና ባለሙያዎችና ሠራተኞች በማኅበር ተደራጅተው ቤት እንዲሠሩ ውሳኔ ሰጥቶ፣ አፈጻጸም ላይ ይገኛል ብለዋል።
ሌሎች ክልሎችና የከተማ አስተዳድሮችም ይኼንን ጥያቄ በቶሎ እንዲመልሱ ጥሪ አቅርበው፣ ሚኒስቴሩም የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።
የቤት መሥሪያ ቦታ ከተገኘ ቤቱ በምን ይሠራል የሚለው አብሮ መነሳት ያለበት ጉዳይ መሆኑን የጠቀሱት ሥራ አስፈጻሚው፣ የጤና ባለሙያውና ሠራተኛው ከፍተኛ ባልሆነ ወለድ ብድር የሚያገኝበትን አማራጫ ለማመቻቸት ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ውይይት መጀመሩን አስረድተዋል። ሒደቱ ከሌሎች ባንኮች ጋር እንደሚቀጥልም አክለዋል።
የብድር ወለድ መጠኑና ምን ያህል ገንዘብ ድረስ መበደር እንደሚቻል ውሳኔ ተላልፎ እንደሆነ ጥያቄ የቀረበላቸው ዶ/ር ተገኔ እስካሁን እንዳልተወሰነና ስምምነት ላይ ሲደረስ ወደፊት እንደሚገለጽ ጠቁመዋል።
ለአገርና ለኅብረተሰብ ጠቃሚ ሥራ የሚሠሩ የጤና ባለሙያዎች ዝውውርና የትምህርት ዕድል የሚያገኙበት አማራጭ ሌላው እየተሠራበት የሚገኝ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀውና የአተገባበር ደንብና መመርያዎች እየወጡለት የሚገኘው የጤና አገልግሎት አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1362/2017 ብዙ ችግሮችን እንደሚፈታም አክለዋል።
ለአብነት ያህል የጤና ባለሙያውና ሠራተኛው ሥራውን እየሠራ በሚገኝበት ጊዜ ለሚያጋጥሙት በሽታዎች ቤተሰቦቹን ጨምሮ ሕክምና እንዲያገኝ፣ ለዚህም መንግሥት ሙሉ በሙሉ የጤና መድን ክፍያ እንደሚሸፍን መደንገጉን አውስተዋል። ይህም ትልቅ ዕርምጃ ነው ሲሉ ገልጸውታል። ከዚህ በፊት ብዙም ያልነበረው የሕግ ከለላ ጉዳይ በአዋጁ ምላሽ ማግኘቱንም አብራርተዋል።
የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ ቀን ተቆርጦ የተላለፈ ውሳኔ አለ ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሥራ አስፈጻሚው፣ በቅርቡ የጤና ባለሙያውና ሠራተኛውን ያካተተ ጭማሪ እንደ አገር መደረጉን ገልጸዋል። "በቂ ላይሆን ይችላል፣ ያለውን ጫና ታይቶ የማይጨመርበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ሆኖም በአጭር ጊዜ ይመለሳል ማለት አንችልም፣ በመካከለኛ አልያም በረጅም ጊዜ የሚታይ ጥያቄ ነው" ብለዋል።
የትርፍ ሰዓት ክፍያ አቤቱታዎችን በሚመለከት ዶ/ር ተገኔ ሲመልሱ፣ መንግሥት ባወጣው መመርያ መሠረት መከፈል እንዳለበት ገልጸዋል። በበጀትና በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ ክልሎች ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ማስተካከያ መደረጉን ተናግረዋል።
"በዚሁ ሒደት ያልተከፈላቸው የጤና ባለሙያዎች እንዲከፈላቸው እናደርጋለን" ሲሉ አስረድተዋል። ዘርፉ ከሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር እንዲወጣ የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ እያቀረቡ ስለሆነ ሚኒስቴሩ ይኼን እንዴት ይመለከተዋል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ሥራ አስፈጻሚው "ጥያቄው ተገቢ ነው፣ ሆኖም ዝም ተብሎ ተነስቶ ሳይሆን በጥናት ነው የሚመለሰው" ብለዋል።
የጤና ባለሙያዎች ሥራ ያቆማሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው የገለጹት ዶ/ር ተገኔ እሱን አደረጉ ማለት የገቡትን የሕክምና ቃል ኪዳን አፍርሰው አባት፣ እናት፣ ወንድምና እህት እንዲሞቱ ማድረግ ይሆናል ብለዋል።
ሆኖም የጤና ባለሙያዎች ሥራቸውን እየሠሩ በተገቢው መንገድ አይጠይቁ ማለት አይደለም ያሉት ሥራ አስፈጻሚው፣ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ከጤና ባለሙያዎች ማኅበራት ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆናቸውንና ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
“ከዚያ ውጪ ግን ይኼንን አጋጣሚ ጠልፎ ለሌላ ዓላማ ለማዋል በማኅበራዊ ሚዲያው ዘመቻ የጀመረ ጤና ባለሙያ ያልሆነ አካል አለ፡፡ እሱን አስረግጠን መናገር እንችላለን፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የጤና ባለሙያዎቹም መለየትና ማጋለጥ አለባቸው፤›› ሲሉ መናገራቸው ታውቋል።
Via ሪፖርተር




Comment section of MoH is closed. Why? ምናል ብንተነፍስ
ደግ ደጉን ያሰማን እንጂ ኑሮ ለሁላችንም እሳት ሆኖብናል ... ይሄ ጦርነት ካልቆመ መተላለቃችን ነው