"የአክቲቪስት ስዩም እና የፓስተር ትዝታው ጉዳዮች ተለያይተው የሚታዩ አይደሉም፣ የአንድ ጥልቅ በሽታ ምልክቶች ናቸው"
በጉዱ ካሳ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- ገዢው ፓርቲ አጋሮቹን ለመጠበቅና ተቺዎቹን ለመቅጣት ፖሊስን እንደ መሳሪያ እየተጠቀመ ይገኛል የሚሉ አስተያየቶች በብዛት እየተሰሙ ይገኛሉ፣ የሀገሪቷ የፍትህ ስርአትም የመጨረሻ ተስፋ አስቆራጭ ደረጃ ላይ የደረሰ ይመስላል የሚሉም አሉ::
አሁን አሁን አስገዳጅ የፍርድ ቤት ትእዛዞች ተግባራዊ የማይደረጉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፣ ፖሊስ የህግ የበላይነትን ሳይሆን የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ፍላጎትን አስፈፃሚ እየሆነ መጥቷል::
የአክቲቪስት ስዩም ተሾመ እና የፓስተር ትዝታው ሳሙኤል የፍርድ ቤት ጉዳይ ለዚህ ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ::
ስዩም ተሾመ የአቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና የአቶ ክርስቲያን ታደለን የክስ ሂደትን አስመልክቶ በችሎቱ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው በሚል ፍርድ ቤቱ ግለሰቡን ሥነ-ሥርዓት እንዲያስይዘው ጠይቀው ነበር::
አክቲቪስት ስዩም ተሾመ
የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የሽብር ወንጀል ችሎት አክቲቪስቱ ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ለፌደራል ፖሊስ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ይሁንና ፖሊስ ግለሰቡን "ላገኘው አልቻልኩም" በሚል የስላቅ ምክንያት ፍ/ቤት ሊያቀርበው እንዳቻለ ሲዝገብ ቆይቷል::
ፖሊስ "ላገኘው አልቻልኩም" ሲል ፍርድ ቤት ላይ እየተሳለቀ ባለበት ሰአት አክቲቪስቱ ለገዢው ፓርቲ የፕሮፓጋንዳ ስራውን ዩትዩብ ላይ ሲሰራ እና በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ በነፃነት ሲንጎማለል ነበር::
ስዩም ፍትህን እያመለጠ ያለ ተራ ግለሰብ አይደለም:: በፕሮፓጋንዳው መስክ የገዥው ፓርቲ አገልጋይ ሲሆን በምላሹም ዳጎስ ያለ ገንዘብ ከከለላ ጋር የተሰጠው ነው:: ፖሊስ ሊይዘው ሳይሆን ሊጠብቀው የተቀጠረ::
ፓስተር ትዝታው ሳሙኤል ለውዝግብ እንግዳ አይደለም።
ግለሰቡ ለዘመናት በዘለቀው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የማያቋርጥ ዘለፋ ሲያካሂድ የቆየ ነው:: ግለሰቡ የቤተክርስቲያኗን እሴቶች ፣ ሃይማኖቱን እና የተቀደሱ ነገሮችን በንቀት ሲሳደብ ቆይቷል::
ፓስተር ትዝታው ሳሙኤል
የቤተክርስቲያኗ የህግ ክፍል ኃላፊ አፈ መምህር አባ ገብረሥላሴ ጌትነት ከማኅበረ ቅዱሳን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፣ ቤተክርስቲያኗ በአቶ ትዝታው ሳሙኤል ላይ ክስ መመስረቷን አስታውቀው ነበር::
ፍርድ ቤት ግለሰቡ በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውል እንዲሁም ከሀገር እንዳይወጣ እግድ እንደጣለበት አፈ መምህሩ ገልፀዋል።
የፌደራል ፖሊስ "ግለሰቡን ለመያዝ እየፈለገው እንደሆነና በዚህ የፍለጋ ተግባር ላይ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ጥቆማ እንዲያደርግለት ጥሪ አቅርቧል" ብለዋል አፈ መምህሩ።
ፖሊስ ግለሰቡን ፈልጎ እንዳጣው ህዝብ በፍለጋው ላይ ተባባሪ እንዲሆን ቢናገርም ፓስተሩ ሐምሌ 26 ቀን 2017 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ሺዎች በታደሙት ፕሮግራም ላይ ተገኝቷል::
እነዚህ ጉዳዮች የፖሊስን ደካማ የማስፈፀም አቅም የሚያሳዩ አይደሉም:: ሁኔታው እጅግ አደገኛ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑን የሚያመልክቱ ናቸው:: ፖሊስ የገዥው ፓርቲ መሳሪያ ሆኗል::
ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚዛመድ የፖለቲካ እና የሃይማኖት አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦች እና ቡድኖች ከለላ የሚያገኙበት ፣ የፍርድ ቤት ተእዛዛት እና ውሳኔዎች ዋጋ እያጡ የመጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል::
ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ግለሰቦች ለመጠበቅ የፍርድ ቤት ትዕዛዞችን ችላ ማለት የህግ የበላይነት እና ፍትህ ከባድ አደጋ ላይ መውደቃቸውን ያሳያል:: ተጎጂዎች እና ቅሬታ አቅራቢዎች አቅም አጥተዋል፣ ዳኞች ተዋርደዋል።
የአክቲቪስት ስዩም እና የፓስተር ትዝታው ጉዳዮች ተለያይተው የተከሰቱ ክስተቶች አይደሉም። እነሱ የጥልቅ በሽታ ምልክቶች ናቸው::
በፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ተዳክሞ የተቦረቦረ የፍትህ ሥርዓት እያየለ መምጣቱን፣ ፖሊስ ፍርድ ቤቶችን ሳይሆን የገዢው ፓርቲ አገልጋይ መሆኑን ህዝብ ለመታዘብ ተችሏል።
****መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
መረጃን ከመሠረት!





