ኢትዮጵያ በዓዋጅ የተቋቋመ ብሔራዊ ሙዚየም እንዳይኖራት ለምን ተፈለገ?
(መሠረት ሚድያ)- በመጀመሪያ ደረጃ ይሄን መረጃ ለመሠረት ሚዲያ ለመላክ ስወስን ተቋማችሁ በታማኝነት የሕዝብን ድምፅ ያሰማል ብዬ የማምን ኢትዮጵያዊ ዜጋ መሆኔን እንድታውቁልኝ እፈልጋለሁ። ለሕዝብ የሚታመን መረጃን በማቅረባችሁ ትልቅ አክብሮት እና ምስጋና አለኝ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በ1936 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ-መጻሕፍት አካል በመሆን የተቋቋመና በቀደምትነት የሚጠቀስ አንጋፋ የባህል ተቋም ነው፡፡
ይሁንና ብሔራዊ ሙዚየሙ ከምስረታው ጀምሮ በተለያዩ የመንግስት ዘመን ሕጋዊ እውቅና ሳይኖረው ዘርፉ የሚጠይቀውን አግባብነት ያለው የሙዚየም አደረጃጀትና አሰራር እንዲከተል ሳይደረግ በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ሥር ተጠሪ ሆኖ መቆየቱ የሚታወቅ ነው፡፡
ዛሬም ላይ በመዋቅር ደረጃ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ሥር እንደ አንድ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ተዋቅሮ የሚገኝው ብሔራዊ ሙዚየም ከስያሜው ጀምሮ የኢትዮጵያን ህልውና የካደና መሰል የዓለም አቀፍ ተቋማት ከሚያከናውኑት ተግባርና አሰራር የተቃረነ ሆኖ መቀጠሉና ዘርፉ አሁን ላይ ዓለም ከደረሰበት ደረጃ አንጻር ተወዳዳሪነት እንዳይኖረው ተደርጎ ይገኛል፡፡
በዚህም ምክንያት የሙዚየሙን ጉዳይ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በተለያዩ ጊዜያት ቀርቦና ችግሩ ታምኖበት እልባት እንደሚሰጠው ቃል የተገባ ቢሆንም፣ በጥቂት አላዋቂና ግብዝ ግለሰቦች ፍላጎት ምክንያት ሀገራዊና ትክክለኛ ተቋማዊ አደረጃጀት እንዳይፈጠር፣ በተለይም የፌደራል አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር እንዲሁም ትክክለኛ አደረጃጀትን ለመፍጠር በወጣው አዲሱ አዋጅ ቁጥር 1263/2014 ጊዜ ችግሩ ተደባብሶና ተወሳስቦ የቀጠለ መሆኑ ጉዳዩን በጣም አሳዛኝና ታሪክ ይቅር የማይለው ነው፡፡
ሙዚዬሞች ከሚያከናውኗቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ ቅርሶችን መሰብሰብ፣ መሰነድ፣ ማጥናት፣ ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ፣ እንዲሁም ቅርሶችን ለትምህርት፣ ለምርምር፣ ለመዝናኛነት እና ለልማት እንዲውሉ ማስቻል ወዘተ የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ነገር ግን በ2015 ዓ.ም በአስፈጻሚነት ደረጃ እንደ አዲስ በተዋቀረው የብሔራዊ ሙዚየም መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሥር አራት ዴስኮች ያሉ ሲሆን፤ እነሱም፡- የሙዚየም ኤግዚቢሽን፤ የሙዚየም ትምህርት፤ የሙዚየም ማርኬቲንግና ፕሮሞሽን እና የሙዚየም ደህንነት ዴስኮች ናቸው፡፡
ይሁንና በ2015 ዓ.ም በአዲስ የተዋቀረው የብሔራዊ ሙዚየም መሪ ሥራ አስፈጻሚ፣ ከላይ የተዘረዘሩትን መሠረታዊ የሙዚየም ተግባራትንና ሀላፊነቶችን በአጠቃላይ በሚባል ደረጃ ያልያዘ መሆኑ በዘርፉ እንደ ተቋምም ሆነ እንደ አገር ወደኋላ እንደቀረን ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ከስሙ እንደምንረዳው አስፈጻሚ ባለስልጣን ቢሆን በተመሳሳይ የሙዚየሞችን ተግባርና ሀላፊነት በመያዝ በሀገራችን ኢትዮጵያ ሙዚየሞች እንዳይስፋፉና እንዳይለሙ ትልቅ ማነቆና እንቅፋት ሆኖ ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ በ2018 ዓ.ም መንግስት በአገር አቀፍ ደረጃ እያደረገ ያለውን የተቋማት የሪፎርም ሥራ ምክንያት በማድረግ የሙዚየሙን ስያሜ በህግ የብሔራዊ ሙዚየም መሪ ስራ አስፈጻሚ ማድረጉ ሳያንሰው፣ በታፔላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የሚል ስም ለጥፎ ሕዝብን በማሳሰትና በማታለል፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከሚያከናውኑት ተግባርና አሰራር የተቃረነ ሆኖ እና ተባብሶ መቀጠሉ ያሳዝናል፡፡
በይበልጥ የባለስልጣኑ የበላይ አካል የሆነው የቱሪዝም ሚኒስቴር ችግሩን በተመለከተ በተደጋጋሚ ቢነገረውም፣ ሰምቶ እንዳልሰማ፣ አይቶ እንዳላየ ሲያልፍ መመልከት በጣም ያስቆጫል፡፡
ስለሆነም የብሔራዊ ሙዚየም መሪ ሥራ አስፈጻሚ ከስያሜው ጀምሮ የተሳሳተ፣ መሰል የዓለም አቀፍ ተቋማት ከሚያከናውኑት ተግባርና አሰራር የተቃረነ ሆኖ መቀጠሉ አግባብነት የለውም፡፡
በተያያዘም ኢትዮጵያ እስከ ዛሬ ድረስ የዓለም አቀፉ የሙዚየሞች ካውንስል አባል አገር ሳትሆን መቆየቷ እንደ አገር በዘርፉ ብዙ ጥቅሞችን ሳታገኝ ቆይታለች፡፡
በመሆኑም ለባህልና ታሪክ ጥበቃ፣ ለአለም አቀፍ ትብብር እንዲሁም ለሙያ እድገትና ልማት የሙዚየሞች አስተዳደርና አደረጃጀት የጎላ ሚና ስለሚጫወት ጉዳዩን ለሚመለከተው የመንግስት አካል እና እንዲሁም ሕዝብ እንዲያውቀው ፍተሻ እንድታደርጉ መልዕክት እያስተላለፍኩ በህግ እውቅና ያልሰጠውን ተቋም ባለስልጣኑ ሕዝብንና መንግሰትን በታፔላ ያታለለበትን ምስል እንደሚከተለው አያይዤ አቅርቢያለሁ፡፡
ያስተውሉ የብሔራዊ ሙዚየም መሪ ሥራ አስፈጻሚ የሚለው በህግ እውቅና የተሰጠው ሲሆን፣የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም የሚለው ህጋዊ እውቅና የለውም።
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
-መሠረት ሚድያ-


