ከሚሰራበት ባንክ ውስጥ በፀጥታ አካላት የተወሰደው ወጣት ያለበት ሳይታወቅ አራት ወር እንደሞላው ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ጥር 9/2017 ዓ/ም ከሚሰራበት ባንክ ውስጥ በፀጥታ አካላት ታፍኖ ተወሰደው ወጣት ያለበት ቦታ ሳይታወቅ አራት ወር እንዳለፈው ታወቀ።
ይበልጣል አንዱአለም የተባለው የባንክ ባለሙያ በዕለቱ ይሰራበት ከነበረው የአማራ ባንክ ዋና መስሪያ ቤት ጠዋት ላይ ተይዞ እንደተወሰደ ለመሠረት ሚድያ ከጓደኞቹ እና ቤተሰቦቹ ያሰባሰብነው መረጃ ያሳያል።
"የተያዘው ወደ ዋና መስሪያ ቤቱ ጠዋት ላይ ሲገባ ነው፣ ከዛ ወዲህ ያለበትን ለማወቅ ያልተሄደበት የፖሊስ ጣብያ የለም ነገር ግን አድራሻውን ማወቅ አልቻልንም" ያሉ አንድ የወጣቱ ቤተሰብ ምስራቅ ጎጃም አካባቢ የሚኖሩት ደካማ ቤተሰቦቹ ቀን ተቀን ሲያለቅሱ እንደሚውሉ ተናግረዋል።
"ቤተሰቦቹ አርሶ አደሮች ናቸው፣ ልጁም ምንም አይነት የፖለቲካ ተሳትፎ የለውም" ያሉት ሌላኛው ታጋቹን የሚያውቁ ግለሰብ ከጥምቀት ዋዜማ ጀምሮ ያለበት አለመታወቁ ቤተሰቡን እጅጉን እንደጎዳ ገልፀዋል።
መሠረት ሚድያ በቅርቡ በሰራው ተመሳሳይ ዜና አማኑኤል የማነብርሃን የተባለ እና በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ልደታ ቅርንጫፍ ዛጉዌ በምክትል ስራ አስኪያጅነት ያገለግል የነበረ ግለሰብ ከስራ ቦታው ታግቶ መወሰዱን ዘግቦ ነበር።
የካቲት 10/2017 ዓ/ም ይሰራበት ከነበረው ከዚህ ቅርንጫፍ እስካሁን ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ተይዞ ተወስዶ እስካሁን ያለበት እንደማይታወቅ ዘመድ ጓደኞቹ በወቅቱ ለሚድያችን ተናግረው ነበር።
የአማኑኤል ቤተሰብ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለጠ/ሚር ፅ/ቤት፣ ለፍትህ ሚኒስቴር፣ ለሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን፣ ለፖሊስ እና ለደህንነት ቢሮው አቤት ቢሉም እስካሁን ምንም ምላሽ እንዳላገኙ ይናገራሉ።
"ማመልከቻውን በመፃፍ ይመለከተዋል የተባለ አካል ጋር ሁሉ መድረስም ብንሞክርም መድረስ አልተቻለም፣ የተቻልዉ ላይም መልስ የለም" የሚሉት ቤተሰቦቹ ሁሉት ልጆቹ በከባድ ሁኔታ ላይ ናቸው ብለዋል።
እንደ ሁለቱ ወጣቶች ሁሉ በርካታ ዜጎች ከቅርብ ወራት ወዲህ ተይዘው እንደሚሰወሩ፣ አንዳንዶቹ የዲያስፖራ ኮሚኒቲ አባላት እንደሆኑ እንዲሁም ከተያዙ በኋላ ከፀጥታ አካላት ጋር በገንዘብ ተደራድረው የሚለቀቁ እንዳሉ መሠረት ሚድያ ከዚህ በፊት ያቀረባቸው መረጃዎች ያሳያሉ።
አንዳንዶቹ ‘በወቅታዊ ሁኔታ' በሚል እና በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ካሉ ሁኔታዎች ጋር በማገናኘት እንደሚያዙ ታውቋል፣ ሌሎቹ ደግሞ ‘እስከሚጣራ' በሚል ካለምንም ክስ ለበርካታ ሳምንታት እና ወራት በእስር ቤት እንደሚማቅቁ ታውቋል።
መረጃን ከመሠረት!




Keep forward as a reliable source of the media and honest news