'ሐራ መሬት' በሚል ስም የተደራጁ የትግራይ ኃይሎች አፋር ክልል ውስጥ ዛሬ ከሕዝብ ጋር መጋጨታቸው ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ የፌደራል መንግስት እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው የታጠቁ የትግራይ ኃይሎች በአፋር ክልል ክልበቲ ረሱ፣ በረሀሌ ወረዳ 'ቡሬ' ተብላ በምትጠራ ቀበሌ ለመስፈር በዝግጅት ላይ እንዳሉ ከአካባቢው ህዝብ ጋር በዛሬው ዕለት ግጭት ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ለመሠረት ሚድያ እንደተናገሩት "ሐራ መሬት በሚል ወረዳችንን የግጭት ቀጠና ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ በመሆኑ ሕዝቡ በተቃውሞ እንዲመለሱ አድርጓቸዋል" ብለዋል።
በታጣቂዎቹ እና በቀበሌው ሕዝብ መካከል በተነሳ ግጭት ሁለት ሰዎች በፅኑ መቁሰላቸውንም ለሚዲያችን ተናግረዋል።
በፌደራል መንግስት ድጋፍ የሚንቀሳቀሱት እነዚሁ የታጠቁ የትግራይ ኃይሎች 'ሐራ መሬት' በሚል በአፋር ክልል ክለበቲ ረሱ (ሰሜናዊ ዞን) በአብዓላ እና በመጋሌ ወረዳዎች ሰፍረው እንደሚገኙ የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።
ቀደም ሲል በዚሁ ሰሜናዊ ዞን ኩነባ ወረዳ 'ሐራ መሬት' በሚል ለመስፈር በዝግጅት ላይ እንዳሉ በተነሳ ሕዝባዊ ተቃውሞ አካባቢውን ለቀው መመለሳቸውንም ጨምረው ለሚዲያችን ተናግረዋል።
ከህወሓት የተገነጠለው እና ራሱን 'ሐራ መሬት' ብሎ የሚጠራው ኃይል በህወሓት ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለመክፈት መዘጋጀቱን ሲገልፅ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፣ ቡድኑ በዚህ ዓመት መጨረሻ ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠር እቅድ መንደፉንም በይፋ አስታውቋል።
የትግራይ ክልል ግዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ በይፋ ‘በፌደራሉ መንግሥት ይደገፋል' ብለው የጠሩት ይህ ታጣቂ ኃይል በህወሓት ላይ የተቀናጀ ጥቃት ለመክፈት መዘጋጀቱን የፈረንሳይ ሚድያዎች ዘግበው ነበር።
ከመቀሌ በስተምስራቅ 110 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ላኮራ አቅራቢያ ከሚገኙት ግንባሮች የአንዱ አዛዥ የሆኑት ሸዊት ቢተው "በዓመቱ መጨረሻ ትግራይን እንቆጣጠራለን" ሲሉ ለዜና ምንጮች ተናግረዋል፡፡
ጀነራል ታደሰ ግን "ይህ ታጣቂ ኃይል ጥቃት ከከፈተብን ትንኮሳው ከፌዴራሉ መንግሥት ወይም ከአፋር ክልላዊ መንግሥት እንደተደረገ እንቆጥረዋለን" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የ 'ሐራ መሬት' አመራሮች ከፌዴራሉ መንግሥት ምንም አይነት ድጋፍና እገዛ እንደማያገኙ በተደጋጋሚ የሚናገሩ ቢሆንም አፍሪካን ኢንተለጀንስ ከወራት በፊት ባወጣው አንድ ዘገባው ቡድኑ በፌዴራል መንግሥት እንደሚደገፍ ጠቁሟል።
-መሠረት ሚድያ-




