የኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት መገታቱን እና የትምህርት ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን አንድ አዲስ የዓለም ባንክ ሪፖርት ጠቆመ
(መሠረት ሚድያ)- የዓለም ባንክ "የሰው ሀብትን ተገቢ በሆነ ቦታ መገንባት" (Building Human Capital Where It Matters) በሚል ያወጣው አዲስ ሪፖርት በኢትዮጵያ ላለፉት 15 ዓመታት የታየው የሰው ሀብት ልማት ሂደት መገታቱንና እንዲያውም በአንዳንድ ዘርፎች ወደ ኋላ እየተመለሰ መሆኑን ይፋ አድርጓል።
በሪፖርቱ የቀረቡት መረጃዎችና ግራፎች እንደሚያሳዩት ሀገሪቱ ጥራት ያለው ትውልድ ከመገንባት አኳያ የከፋ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ይህም የወደፊት የኢኮኖሚ ዕድገቷንና የዜጎቿን የነፍስ ወከፍ ገቢ በእጅጉ የሚገድብ ሆኖ ተገኝቷል።
በሪፖርቱ በዋነኝነት የተመለከተውና ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ ሀገራት የታየው አስደንጋጭ እውነታ የትምህርት ጥራትና ውጤት (Harmonized Learning Outcomes - HLO) ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ምንም ዓይነት መሻሻል አለማሳየቱ ተብራርቷል።
እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ኢትዮጵያ በትምህርት ተደራሽነት ላይ ጥረት ብታደርግም ተማሪዎች በትምህርት ቤት የሚያገኙት ዕውቀትና ክህሎት ግን እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ቀጥሏል።
በሪፖርቱ ላይ የቀረበው የሀገራት የንፅፅር ግራፍ እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ በነጥብ ደረጃ ከዜሮ በታች ወይም እጅግ ዝቅተኛ ዕድገት በሚታይባቸው ሀገራት ተርታ ተሰልፋለች። ይህ የትምህርት ጥራት መውደቅ የዜጎችን ምርታማነት ከመቀነሱም በላይ ሀገሪቱ ለትምህርት ዘርፍ የምታውለው ሀብት ያለ አግባብ እየባከነ መሆኑን የሚያሳይ ማሳያ ተደርጎ ቀርቧል።
ሪፖርቱ በኢትዮጵያ ያለውን የሰው ሀብት ቀውስ ይበልጥ አጉልቶ ያሳየው በቤተሰብ የኢኮኖሚና የትምህርት ደረጃ ምክንያት በህፃናት መካከል የሚፈጠረውን ሰፊ የክህሎት ልዩነት በመተንተን ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን የቃላት ዕውቀት እና የሂሳብ ችሎታን መሠረት በማድረግ የቀረበው መረጃ እንደሚያመለክተው የተማሩ እና ያልተማሩ እናቶች በሚወልዷቸው ህፃናት መካከል ያለው የውጤት ልዩነት እጅግ ሰፊና የማይቀራረብ ሆኖ ተገኝቷል።
በግራፉ መሠረት የአንደኛ ደረጃ ወይም ከዚያ በታች የትምህርት ደረጃ ያላቸው እናቶች ልጆች የሁለተኛ ደረጃና ከዚያ በላይ ከተማሩ እናቶች ልጆች ጋር ሲነፃፀሩ ያላቸው ውጤት በጣም ዝቅተኛ ነው።
ይህ ልዩነት ይበልጥ አሳሳቢ የሚሆነው ህፃናቱ ዕድሜያቸው እየጨመረና ትምህርት ቤት እየገቡ በሚሄዱበት ወቅት ልዩነቱ ከመጥበብ ይልቅ በተመሳሳይ ርቀት ፀንቶ መቀጠሉ ነው። ሪፖርቱ እንደሚያሳየው በ5 ዓመት ዕድሜያቸው የተመዘገበው የክህሎት ልዩነት ህፃናቱ 8፣ 12 እና 15 ዓመት ሲሞላቸውም ሳይቀንስ ይቀጥላል።
ይህ የሚያሳየው የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ከቤት ይዘውት የሚመጡትን የክህሎት ክፍተት መሙላት አለመቻሉንና ድህነት ውስጥ ያደጉ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸውም ቢሆን ከበለፀጉት ጋር እኩል ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ የሚያደርግ ደካማ መዋቅር መኖሩን የሚያሳይ መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል።
የዓለም ባንክ ግኝት ጨምሮ እንደሚያመለክተው ይህ ዓይነቱ የትምህርትና የክህሎት ውድቀት የረጅም ጊዜ ማህበራዊ ኪሳራ ያስከትላል። ደካማ የትምህርት ውጤቶች የሰራተኛውን ኃይል ምርታማነት በመቀነስ የዜጎችን የዕድሜ ልክ ገቢ ከማሳነሱም በላይ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን እንደሚያሰናክል በሪፖርቱ ተገልጿል።
ሪፖርቱ በግልጽ እንደሰፈረው በቤት ውስጥ የሚገኙ ግብዓቶች (እንደ መጽሐፍትና የትምህርት ክፍያ) ብቻቸውን ለሰው ሀብት ልማት በቂ አይደሉም። ይልቁንም በኢትዮጵያ ያሉ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው የሚሰጡት እንክብካቤ፣ አመጋገብና ቀድሞ የመማር ዕድል እጅግ ዝቅተኛ መሆን ለዚህ ውድቀት ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ተጠቅሷል።
በመጨረሻም፣ ሪፖርቱ የኢትዮጵያን ፖሊሲ አውጭዎች የሚሞግት ጠንካራ ነጥብ አስፍሯል። እስካሁን የነበረው ትኩረት በትምህርት ቤቶችና በጤና ጣቢያዎች ግንባታ ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑንና ይህም የሰው ሀብት ልማትን ለመታደግ እንዳልቻለ ይገልጻል።
"አሁን ባለው ሁኔታ በኢትዮጵያ የሚታየው የትምህርት ጥራት መውደቅና የክህሎት ክፍተት ሀገሪቱ ለወደፊት በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆን የሰው ኃይል እንዳይኖራት እያደረገው ነው። ይህ መገታትና ወደ ኋላ መመለስ በአስቸኳይ በመዋቅራዊ ለውጥ ካልታገዘ የኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማት ከከፋ ድህነትና ከማያቋርጥ የኢኮኖሚ መቀንጨጭ ሊወጣ አይችልም" ሲል ሪፖርቱ ያስጠነቅቃል።
| መሠረት ሚድያ |


