ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ውስጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፀሙ የተባሉ አመራር ላይ ክስ ሊመሰረት ነው
(መሠረት ሚድያ)- በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያሌው እና በአቶ ክርስቲያን ታደለ መዝገብ ስር በሚገኙ ተከሳሾች ላይ የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አመራር ኢንስፔክተር ድሪባ ሰንበታ ፈፅመውታል በተባለ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት የፌዴራል ፖሊስ በምርመራ አጣርቶ ለዓቃቤ ሕግ ማስረከቡን ለፍርድ ቤት አስታውቋል።
የማረሚያ ቤቱ ጥበቃና ደህንነት ኃላፊ ኢንስፔክተር ድሪባ ሰንበታ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በማረሚያ ቤት የሚገኙትን ተከሳሾችን ደብድበዋል፣ ጠያቂ ቤተሰቦቻቸውን አዋርደዋል፣ የአማራን ሕዝብን በጅምላ ተሳድበዋል ሲሉ የሕሊናና የፖለቲካ እስረኞች ለፍርድ ቤት ማመልከታቸውን ተከትሎ ምርመራ መጀመሩን የመሠረት ሚድያ ምንጮች ተናግረዋል።
ሚያዚያ 22 ቀን 2028 ዓ.ም በዋለው ችሎትም ፍርድ ቤቱ ኢንስፔክር ድሪባ ፈጽመውታል የተባለውን የወንጀል ፍሬ ነገር በተመለከተ የፌዴራል ፖሊስን የደረሰበትን ሂደት ጠይቋል።
የፌዴራል ፖሊስም ከረጅም ጊዜ መጓተት በኋላ ጉዳዩን አጣርቶ ክስ እንዲመሰረት መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ መላኩን ለፍርድ ቤቱ አረጋግጧል።
ዐቃቤ ሕግም ከፖሊስ የቀረበለትን የምርመራ መዝገብ መሰረት አድርጎ በኢንስፔክተር ድሪባ ሰንበታ ላይ በቅርቡ ክስ ይመሰርታል ተብሎ ይጠበቃል።
| መሠረት ሚድያ |



2018