'ጥያቄዎቻችን በአግባቡ ይመለሱ' ያሉ የጤና ባለሙያዎች በበርካታ ከተሞች ድምፃቸውን አሰሙ
'ጥያቄዎቻችንን በግዜ ካልተመለሱ የስራ ማቆም እናደርጋለን' ያሉ የጤና ባለሙያዎች በበርካታ ከተሞች ከስራ ቦታቸው በመውጣት ድምፃቸውን አሰምተዋል።
ከተለያዩ ከተሞች ለመሠረት ሚድያ የተላኩ ምስሎች እና መረጃዎች እንደሚያሳዩት የጤና ባለሙያዎቹ የጤና ሚኒስቴር በቅርቡ ምላሽ በሚል የሰጠው መግለጫ አላስደሰታቸውም።
በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል/ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ በጎንደር ሪፈራል ሆስፒታል፣ በዲላ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል፣ ሀሮማያ ህይወት ፋና ጠቅላላ ሆስፒታል፣ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ኮምፕርኸንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በደባርቅ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ በፊቂ፣ በዋቸሞ ንግስት እሌኒ ኮምፕርኸንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ በቡታጅራ፣ በጎሮ፣ በንፋስ መውጫ እንዲሁም በሌሎች በርካታ የጤና ተቋማት የጤና ባለሙያዎች ተቃውሟቸውን ማሰማታቸው ታውቋል።
የጤና ባለሙያች ለበርካታ አመታት ተምረው ህብረተሰባቸው ሲያገለግሉ ለዝቅተኛ ኑሮ እንኳን የማይሆን ደሞዝ እየተከፈላቸው በድህነት እንደሚኖሩ በመግለፅ ለመንግስት የ30 ቀን ምላሽ መስጫ እንደሰጡ ይታወሳል።
የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ለጤና ባለሙያዎች ጥያቄዎች መፍትሔ ለመስጠት ሒደት እንደጀመረ አስታውቆ በአዲስ አበባ በማኅበር ተደራጅተው ቤት እንዲሠሩ ውሳኔ ተሰጥቶ አፈጻጸም እንደሚገኝ፣ የመኖሪያ ቤት መሥሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው የሚደረጉ ውይይቶች መቀጠላቸውን፣ ከደመወዝ ጭማሪ ጋር በቀጥታ የማይገናኝ የማበረታቻ ፓኬጅ እየተዘጋጀ መሆኑን፣ ከፍተኛ ባልሆነ ወለድ ብድር የሚያገኙበትን አማራጭ ለማመቻቸት ሚኒስቴሩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ውይይት መጀመሩን እንዱሁም በቅርቡ በመንግስት የተደረገው የደሞዝ ጭማሪ በቂ ካልሆነ ታይቶ ሊጨመርበት የሚችልበት እድል እንዳለ መግለፁ ይታወሳል።
በርካታ የጤና ባለሙያዎች ግን ይህ አካሄድ ድምፃቸውን ለመጥለፍ የታቀደ እንዲሁም እነሱ እየጠየቁ ካሉት የዳቦ እና እንጀራ ጥያቄ ውጭ የሆነ በመሆኑ በቀጥታ ጥያቄዎቻቸውም መንግስት እንዲመልስ እየጠየቁ ይገኛሉ።
መረጃን ከመሠረት!






