በአዲስ አበባ ከተማ ከትናንት ጀምሮ ተመልሶ የመጣው መጠነ-ሰፊ የወጣቶች አፈሳ
(መሠረት ሚድያ)- ከወራት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ እና በበርካታ የክልል ከተሞች የወጣቶች አፈሳ እንደነበር በተለያዩ ሚድያዎች ሲገለፅ ነበር።
በወቅቱ በመንግስት ምላሽ ሳይሰጥበት አፈሳው በብዛት ከተከናወነ በኋላ 'በፍቃደኝነት እንጂ በግዴታ አይደለም' የሚል ምላሽ ቆይቶ መሰጠቱ ይታወሳል።
ከትናንት ጀምሮ ይህ የወጣቶች አፈሳ እንደ አዲስ እንደተጀመረ የሚደርሱን ተከታታይ መረጃዎች የሚጠቁሙ ሲሆን አፈሳው ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው ተብሏል።
"ከትናንት ጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ የአማራ ተወላጆችን በጅምላ ማሰር ተጀምሯል። ለምሳሌ ወንድሜ አስኮ አካባቢ ከጓደኞቹ ጋር የእቁብ ስብሰባ እያደረገ በነበረበት ሰዓት ሁሉንም 6 ልጆችን አፍሰው ወስደዋቸዋል" ያለው አንድ የመረጃ ምንጭ ነው።
"እነዚህ ልጆች ህይወታቸውን ለመቀየር ላይ ታች የሚሉ እንጂ ምንም አይነት ፖለቲካ ውስጥ የሉበትም። ሁሉም የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ናቸው" በማለት ለሚድያችን ተናግሯል።
“አዲስ አበባ ውስጥ ከትናንት ሰባት ሰአት በሗላ ጀምሮ መንቀሳቀስ አልቻልንም፣ በተለይ አየር ጤናና ዘነበወርቅ ከፍተኛ አፈሳ አለ" ያሉት ሌላ የመረጃ ምንጫችን ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ በቦሌ አራብሳ አካባቢ ኤርትራዊያንን እና የትግራይ ተወላጆችን ከየመንገዱ በማፈስ እስከ 40 ሺህ ብር ድርድር ማድረግ መልቀቅ እንደተጀመረም ታውቋል።
"ሲቪል ፖሊስ በየመንገዱ እወስድሀለው እያለ ይደራደራል፣ ሌብነቱ ሀላል ወጥቷል። በየቀኑ ከመዝናኛ ቦታ እየወሰዷቸዉ በብር ይለቋቸዋል" ያሉት አንድ የፀጥታ አካል ባልደረባ ናቸው።
የአንድ ሬስቶራንት ባለቤት ደግሞ ከስራ ቦታው በርካቶች ታፍሰው እየተወሰዱ መሆኑን በመግለፅ "ምንም መስራት አልቻልንም። ወንጀለኛ ከሆኑ ይዘዉ ለምን ይለቃሉ? ቦሌ አራብሳ ወረዳ 4፣ ወረዳ 6 ጣቢያ የገባ ሁሉ ብር ሲከፍል ነዉ ሚወጣዉ። ብር አጥተዉ ከሶስት ሳምንት በላይ የታሰሩ ሰዎችን አውቃለሁ" በማለት ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
በዚህ አዲስ በተጀመረ አፈሳ ዙርያ እስካሁን በመንግስት የተሰጠ ማብራርያም ሆነ ማረጋገጫ የለም።
መረጃን ከመሠረት!



