በጅማ ከተማ አዲሱ አስገዳጅ መዋጮ- ለትራፊክ ፖሊሶች ሞተር ሳይክል መግዛት
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን ከዚህ በፊት አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ የሀገሪቱ ክፍሎች ዜጎች በግዴታ እየተጠየቋቸው ያሉ መዋጮዎችን በተመለከተ መረጃ ሲያቀርብ ቆይቷል። ከሰሞኑ ደግሞ ከወደ ጅማ በተደጋጋሚ ሲደርሰን የነበረ መረጃን እናቀርባለን።
በጅማ ከተማ ከ5 ሺህ በላይ የባጃጅ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ይገመታል፣ እነዚህ ባጃጆች ደግሞ በ10 ገደማ ማህበራት ስር ተደራጅተው ይገኛሉ።
እነዚህ ማህበራትን የሚመሩት ግን የባጃጅ እና የታክሲ ባለቤቶች ወይም አሽከርካሪዎች ሳይሆኑ የከተማው መንገድ ትራንስፖርት የሚሰሩ ካድሬዎች እና ባለስልጣናት መሆናቸውን የባጃጅ ሹፌሮች ይናገራሉ።
ታድያ ማህበራቱ ላለፉት ጥቂት ወራት አሽከርካሪዎች በየወሩ ከሚከፍሉት 400 ብር በተጨማሪ በየወሩ 120 ብር ለልማት እንዲሁም 500 ብር ለመከላከያ እየተባሉ ሲከፍሉ መቆየታቸውን ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
"አሁን ደግሞ በቅርቡ ይህም አልበቃ ብሎ የሚያስቅም፣ የሚያናድድም ነገር ይዘውብን መጥተዋል። እሱም ለትራፊክ ፖሊሶች ሞተር ሳይክል መግዣ ብር አምጡ ብለው ትእዛዝ ሰጥተዋል" በማለት አስረድተዋል።
"እነዚህ የካድሬዎች የግል ንብረት የሆኑ ማህበራት በዚህ ቢፋቱን ጥሩ ነበር። አሁንም ሌላ መዋጮ ብለው እንደሚመጡ እየሰማን ነው። ነዳጅ እንኳን ገዝቶ መስራት ባልተቻለበት ሁኔታ ብር ከየት አምጥተን እናዋጣ? የትራፊክ ፖሊስ ሞተር መግዛትስ የመንግስት ድርሻ አይደለም?" ብለው ጥያቄ አቅርበዋል።
እነዚህን መዋጮዎች ካልሰጠን መስራት አንችልም የሚሉት አሽከርካሪዎቹ አብዛኞቹ ወታደር የነበሩ፣ ስራ አጥ የነበሩ እና ከተለያየ መጥፎ ሱስ ነፃ ወጥተው ራሳቸውን ለማሸነፍ የሚሰሩ ሆነው ሳለ ይህ 'አስጨናቂ' ያሉት አስገዳጅ መዋጮ ትልቅ ችግር እንደሆነባቸው ተናገረዋል።
ለትራፊክ ፖሊስ ሞተር መግዣ ገንዘብ ያላዋጣ የ1 ሺህ ብር ተጨማሪ ቅጣት ይጠብቀዋል መባሉን ሰምተናል።
ከጅማ በተጨማሪ በሌሎች በርካታ ከተሞች ለኮሪደር ልማት፣ ለጎፋ ቦንሳ፣ ለቀይ መስቀል፣ ለሚሊሺያ ደሞዝ፣ ለስታዲየም ግንባታ ወዘተ በሚል በርካቶች ገንዘብ በግዴታ እየተጠየቁ መሆናቸው ይታወቃል።
ለምሳሌ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሉሜ ወረዳ ባሉ ትናንሽ ከተሞች ያሉ ነዋሪዎች ከቅርብ ግዜ ወዲህ በአካባቢው የመንግስት ሀላፊዎች 'ደጃፋችሁን በኮሪደር ልማት ልክ አልሰራችሁም' በማለት ማሰር እና ማንገላታት በመብዛቱ ነዋሪው ተገዶ ያለውን ወርቁን እና ከብቱን እየሸጠ እንደሆነ የታወቀ ሲሆን ነጋዴው ደግሞ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ነው ተብሏል።
"ከዚህም በተጨማሪ የገቢዎች ሰራተኞች እያስፈራሩ በወር ከ5,000 ብር በላይ ከእያንዳንዱ ነጋዴ እና ብር አለው ብለው ያሰቡት ነዋሪ ይቀበላሉ" የሚሉት ነዋሪዎቹ በተለይ ባለሬስቶራንቶች እና ስጋ ቤቶች ላይ አተኩረዋል ብለዋል።
መረጃን ከመሠረት



