በጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ብ/ጄነራል ገዛኢ አበራ ግድያ ዙርያ ያልተሰሙ መረጃዎችን የሚዳስስ የምርመራ መፅሀፍ ገበያ ላይ መዋሉ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- 'ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ብ/ጄነራል ገዛኢ አበራን ማን ገደላቸው? ጥቃቱስ እንዴት ተፈፀመ?' የሚል ጥልቅ ምርመራን ያካተተ መጽሐፍ አማዞን ላይ ለገበያ መዋሉ ተሰምቷል።
ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም በጄነራል ሰዓረ እና በ/ብጄነራል ገዛኢ ላይ የተፈፀመውን ጥቃት አስመልክቶ በጥልቀት የሚዳስሰው ይሄው የምርመራ መፅሀፍ የችሎቱን ሂደት እና የፎረንሲክ ምርመራ ውጤትን ጨምሮ የዓይን ምስክሮችን ቃል ያካተተ መጽሐፍ መሆኑ ታውቋል።
መጽሐፉ ወንጀሉን ፈፅሟል ተብሎ በፍርድ ቤት የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት የተበየነበትን የአስር አለቃ መሳፍንት ጥጋቡን ቃልም ይዟል። አስር አለቃ መሳፍንት “እኔ አልገደልኳቸውም፣ ጄነራሎቹ የተገደሉት በግቢው አጥር ዘለው በገቡ የሰለጠኑ ተኳሾች ነው” ሲል ይናገራል።
መፅሀፉ ውስጥ “ከብ/ጄነራል አሳምነው ፅጌ ጋር የነበረህ ግንኙነትስ ምን ይመስላል?” ተብሎ ተጠይቆም የሰጠው ምላሽ በመጽሐፉ ተካቷል።
ጄነራሎቹ ተገደሉበት የተባለው ሽጉጥ ባለቤቱ ማነው? ለምን የጣት አሻራ ሳይገኝ ቀረ? በዕለቱ የጥበቃ ካሜራዎቹን ማን አጠፋቸው? የዕለቱ የጥበቃ ተረኛ ለምን ከጥርጣሬ ውጭ ሆነ? የሚሉ እስካሁን ያልተሰሙ መረጃዎችን እንደሚዳስስ ሚድያችን ተመልክቷል።
“ብዙ አከራካሪ ጉዳዮችን በማስረጃ እየነቀሰ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው” የተባለለት ይህ የምርመራ ዘገባ በመጽሐፍ ሰንዶ ለአንባቢያን ለማድረስ ሁለት ዓመት ያህል እንደወሰደበት ታውቋል።
መጽሐፉን ለየት የሚያደርገው በአገራችን የምርመራ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ መሆኑ ነው የተባለለት ሲሆን ፀሀፊው አሁን ላይ ሀገር ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ለደህንነቱ ሲባል “ከጋዜጠኛው” በሚል የብዕር ስም እንዲታተም ሆኗል። መጽሐፉ አሁን አማዞን ላይ እየተሸጠ ይገኛል።
መጽሐፉን የሚገኝበት ሊንክን ለምትፈልጉ: https://a.co/d/jkk5fH0
-መሠረት ሚድያ-




