የፌደራል መንግስታዊ ተቋም ሆኖ ለሀላፊዎቹ ከፍተኛ መጠን ያለው አበል እና ጥቅማ ጥቅም በዶላር የሚከፍለው መስሪያ ቤት ሲዳሰስ
(መሠረት ሚድያ)- ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በርካታ መንግስታዊ ተቋማት ውስጥ ያሉ እነጋጋሪ አሰራሮችን እንዲሁም አንዳንድ የሙስና ድርጊቶች ላይ አተኩረን መረጃ ስናቀርብ መቆየታችን ይታወሳል።
ዛሬ ደግሞ ከአንድ የመረጃ ምንጫችን በደረሰን ጥቆማ መሰረት ያገኘነውን የምርመራ ውጤት ለተከታታዮቻችን በሚከተለው መልኩ እናቀርባለን።
ጉዳዩ እንደዚህ ነው፣
የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት የፌደራል መንግስት ተቋም ሲሆን ዋና ተግባሩ በኢትዮጵያ ተጠልለዉ የሚገኙ የጎረቤት ሃገራት ስደተኞች ከማስተዳደር ጋር በተያያዘ የሚሠራ ነዉ፡፡ የ
በጀት ምንጩ የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ነዉ፤ ተቋሙ ተጠሪነቱ ለብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እንደሆነ፣ ተቋሙን የሚመሩ አካላት እንደማንኛዉም የፌደራል ተቋም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሿሚዎች እንደሆኑ ይታወቃል።
በዚህም መሰረት የተቋሙ የበጀት ምንጭ መንግስት ስላልሆነ የፌደራል ዋና ኦዲተር ኦዲት አድርጎት የማያዉቅ ተቋም መሆኑን፤ በራሱ መመሪያ አውጥቶ እንደሚተገብር እና አሁን አሁን ጠያቂ አልባ ተቋም መሆኑን ምንጮች ያስረዳሉ።
መሠረት ሚድያ የተመለከተው “የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞች አፈጻፀም መመሪያ ቁጥር 16/2017” የጸደቀዉ ታህሳስ 2017 ዓ.ም ነበር። ታድያ ይህ ሰነድ ኢትዮጵያ ዉስጥ የፌደራል መንግስት ተቋም ሆኖ በዶላር ጥቅማ ጥቅም በመመሪያ አጽድቆ ክፍያ እንደሚፈፅም ያሳያል።
ከተቋማት የዉስጥ መመሪያ አወጣጥ ጋር በተያያዘ የህግ እዉቀት ያላቸዉን ሰዎች ለማነጋገር በተደረገው ጥረት አንድ ተቋም የራሱን የጥቅማ ጥቅም መመሪያ እራሱ አዘጋጅቶ እራሱ መተግበር ይችላል ወይ? በሚል ለቀረበው ጥያቄ ሲመልሱ የጥቅማ ጥቅም መመሪያን በተመለከተ የጥቅም ግጭት ስለሚያመጣ በሚመለከተዉ አካል ተዘጋጅቶ ተፈጻሚ እንደሚሆን፣ በሌሎች መመሪያዎች ማንኛዉም በተቋማት የሚዘጋጁ የዉስጥ መመሪያዎች በፍትህ ሚኒስትር መጽደቅ እንዳለበት ያስረዳሉ።
"የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞች አፈጻፀም መመሪያ ቁጥር 16/2017 ላይ ችግሩ ያለዉ ወደ መመሪያዉ የዉሰጥ ይዘት ሲገባ ነዉ፤ ክፍያው በዶላር መሆኑ ብቻ ሳይሆን አመራሩ ይህን መመሪያ ሲያዘጋጅና አጽድቆ ወደ ስራ ሲያስገባ የአመራሩ ጥቅማ ጥቅሙን በመመሪያ አስደግፎ ለመጠቀም ቆርጦ የተነሳ ለመሆኑ ማሳያ ነው። ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ የሚለዉን አባባል አጉልቶ የሚያሳይ ሆኖ አግኝቸዋለሁ" የሚሉት አንድ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የመንግስት ሰራተኛ ያስረዳሉ።
ተቋሙ አሁን ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙ አንድ ዋና ዳይሬክተር እና ሶስት ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች አሉት፣ እስከ ቅርብ አመታት አንድ ምክትል ዳይሬክተር እንደነበረውም ታዝበናል።
ወደ መመሪያዉ የዉስጥ ክፍሎች ስናመራ:
• በአንቀጽ 4 'ልዩ ልዩ አበሎች' በሚለዉ ስር ለዋና ዳይሬክተር የሃላፊነት አበል በየወሩ 59 ዶላር፣ ለምክትል ዋና ዳይሬክተሮች 53 ዶላር ይላል። ይህ በአሁኑ የባንክ ምንዛሬ ሲመነዘር ለዋና ዳይሬክተር 59 X 150 ብር= 8,850 ብር ሲሆን ለሶስት ምክትሎች ለእያንዳንዳቸዉ 53 X 150 ብር= 7,950 ብር ይሆናል፡፡
• በአንቀጽ 6 'የቤት ኪራይ አበል' ለዋና ዳይሬክተር 354 ዶላር ለሶስት ምክትሎች ለእያንዳንዳቸዉ 295 ዶላር ይላል ይህም በአሁኑ ምንዛሬ ሲመነዘር ለዋና ዳይሬክተር 354 X 134 ብር = 53,100ብር ሲሆን ለሶስት ምክትሎች ለእያንዳንዳቸዉ 295 X 150 ብር = 44,250 ብር ይሆናል፡፡ ለእነዚህ ተሿሚዎች እንደማንኛዉም ተሿሚ መንግስት የመኖሪያ ቤት እያቀረበ የሚገኝ ሲሆን ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት በተቋሙ የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ያዕቆብ ያላ ከላይ የተጠቀሰዉን 44,250 ብር የቤት አበል እየተከፈላቸዉ በአዲስ አበባ ከተማ ሳርቤት ገብርኤል ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ሰፊ ግቢ ያለዉ የመኖሪያ ቤት ከመንግስት ተሰጥቷቸዉ እንደሚኖሩ ለማወቅ ተችሏል።
• በአንቀጽ 7 'ለተሽከርካሪ ነዳጅ' በሚለዉ ስር ለዋና ዳይሬክተርና ለሶስት ምክትሎች ለእያንዳቸዉ 260 ሊትር ቤንዚንና 300 ሊትር ናፍጣ በየወሩ ለእያንዳንዳቸዉ የሚሰጣቸዉ ሲሆን ይህ ነዳጅ ለአዲስ አበባ ከተማ ላይ ብቻ ለመንቀሳስ ነው። በጠቅላላ 560 ሊትር የነዳጅ ገንዘብ በወቅቱ የነዳጅ ዋጋ ተባዝቶ በየወሩ ይወስዳሉ፤ አሁን ባለዉ አንድ ሊትር በ120 ብር ቢሰላ ለእያንዳንዳቸዉ 67,200 ብር በየወሩ ከደምወዛቸዉ ጋር ይወስዳሉ ማለት ነዉ። ይሁንና በአዲስ አበባ ከተማ ከመኖሪያ ቤት ወደ ሥራና ከሥራ ቦታ ወደ መኖሪያ ቤት ለመሄድ ለሁለት ተሽከርካሪ 560 ሊትር ነዳጅ በአንድ ወር ዉስጥ ይጨርሳል ወይ? የሌሎች ተቋማት አሠራራርስ ? የሚለው ጥያቄ መሆኑን ብዙዎች ይስማማሉ።
• ሌላዉ በአንቀጽ 12 'የሻይ ቡና አገልግሎት አበል' በሚል የተያዘዉ ለዋና ዳይሬክተር በየወሩ 114 ዶላር፣ ለምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ለእያንዳንዳቸዉ 76 ዶላር ይላል፤ ይህም በአሁኑ ምንዛሬ ሲመነዘር ለዋና ዳይሬክተር 114 X 150 ብር = 17,100 ብር ሲሆን ለሶስት ምክትሎች ለእያንዳንዳቸዉ 76 X 150 ብር = 11,400 ብር ይሆናል።
• ከላይ ከተጠቀሱት ዉጭ አንደ አጠቃላይ ለመግስት ተሿሚዎች የሚሰጠዉ ተመላሽ የማይሆን ተንቀሳሰቃሽ ስልክና ላፕቶፕ ኮምፒዉተር እንዲሁም ጥቅል ወርሃዊ ያልተገደበ ስልክና ኢንተርኔት እንደሚያገኙ በመመሪያዉ አንቀጽ 15 ተመላክቶዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሰዉ የጥቅማ ጥቅም መመሪያ በየደረጃዉ ለሚገኙ ሃላፊዎችና ሠራተኞች እንደ ተሿሚዎቹ ከፍተኛ ባይሆንም እንደ ደረጃቸዉ እንደተቀመጠ መረጃዎች ያሳያሉ።
በዚህም መሰረት የጥቅማ ጥቅም መመሪያዉ ለዋና ዳይሬክተር በየወሩ ለጥቅማ ጥቅም ብቻ 146,250 ብር፤ ለሶስት ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ለእያንዳንዳቸዉ 130,800 ብር በየወሩ ክፍያ ይፈጸማል፡፡
"ከዚህ በላይ መመሪያን ተገን አድርጎ ራስን መጥቀም ሌላ መገለጫ ያለዉ አይመስለኝም። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በምክር ቤት ለሚነሳላቸዉ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ የምንሰማዉ መንግስታዊ ሙስና የለም የሚሉት ይሄን ያካትት አያካትት ለአንባቢ ፍርድ ልተወዉ" የሚሉት ሌላ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ የተቋሙ ሰራተኛ ናቸው።
አክለውም "በጣም የሚያሳዝነዉ በዚሁ ተቋም የሚሠራ አንድ ጥበቃ ከፔይሮል ላይ እንደሚታየዉ ወርሃዊ የተጣራ ክፍያ 7,327.44 ብር ነው። ይህም በአንድ ተቋም ዉስጥ ያለዉ የደምወዝ ልዩነት ስናቀናንሰዉ ጥቅማጥቅምን ሳይጨምር የ 115,867.31 ብር ነዉ" ብለዋል።
"የአመራሩን ጥቅማጥቅም ስንደምረዉ ለዋና ዳይሬክተር 269,444.75 ብር ለምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ለእያንዳንዳቸዉ 245,125.51 ብር ይህ ከጥበቃ ሠራተኛዉ ምንም አይነት ጥቅማ ጥቅም ከሚያገኘዉ ጋር ያለዉ ልዩነት 262,117.31 ብር ነዉ። ይህ እንግዲህ በአንድ ተቋም በሚሠሩ ሠራተኞች ያለ ወርሃዊ የገቢ ልዩነት ነዉ" በማለት አስረድተዋል።
ለዚህ ዘገባ የተቋሙን ዋና ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ ጠይባ ሀሰን፣ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ብሩህተስፋ ሙሉጌታ እና የአስተዳደር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር የሆኑትን አቶ ያቆብ ያላ መረጃ ጠይቆ የነበረ ሲሆን ይህ ዘገባ ለህዝብ እስከቀረበበት ሰዓት ድረስ ምላሽ አላገኘም። በቀጣይ ምላሽ ከደረሰን ይዘን የምንመለስ ይሆናል።
-መሠረት ሚድያ-








የዝች አገር ጉድ የሚደንቅ ነው