የኢትዮጵያ ኢንሳይደር መስራች ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ መታሰሩ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በኢትዮጵያ ካሉ የካበተ ልምድ ካላቸው ጋዜጠኞች አንዱ የሆነው ተስፋለም ወልደየስ 'ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት' በሚል ተጠርጥሮ መታሰሩ ታወቀ።
የጋዜጠኛውን መታሰር በተመለከተ የኢትዮጵያ ኢንሳይደር አታሚ ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጋዜጠኛው የታሰረው ሰኔ 1/2017 ዓ/ም ነበር።
በአዲስ አበባ ከሚገኘው ግዮን ሆቴል ቅጥር ግቢ ውስጥ ሲቪል በለበሱ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋለው ተስፋለም ሌሊቱን እስጢፋኖስ አካባቢ በሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ሕንፃ ውስጥ ወንበር ላይ እንዲያሳልፍ መደረጉን ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ገልጿል።
ተስፋለም የመጀመሪያውን ሌሊት ካሳለፈበት እስጢፋኖስ አካባቢ ከሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ትላንት ሰኞ ሰኔ 2 ቀን፤ 2017 ቄራ አካባቢ ወደሚገኝ የፖሊስ መምሪያ ተዘዋውሯል የተባለ ሲሆን ዛሬ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፣ ቂርቆስ ምድብ ችሎት ቀርቦ በ15,000 ብር ዋስትና እንዲፈታ ተወስኖ ነበር።
"ለዋስትና የተጠየቀው ገንዘብ ከተከፈለ በኋላ ተስፋለም የጠየቀውን መስፈርት የሚያሟላ በመሆኑ ከእስር እንዲለቀቅ በፍርድ ቤቱ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ትዕዛዝ ተሰጥቷል። ተስፋለም ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት እንደተጠረጠረ ፍርድ ቤቱ ከእስር እንዲፈታ ትዕዛዝ በሰጠበት ደብዳቤ ላይ ሠፍሯል። የተስፋለም የዋስትና መብት እንዲከበር ከተሰጠው ትዕዛዝ በኋላ መርማሪ ፖሊስ በቃል ይግባኝ እንደሚጠይቅ ገልጿል" በማለት መግለጫው አስታውቋል።
ይሁንና እስካሁን በይፋ ፍርድ ቤት ይግባኝ አለመጠየቁ ታውቋል።
"የተስፋለም ዋስትና እንዲከበር ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን አስፈላጊውን ክፍያ ፈጽሞ በፍርድ ቤቱ ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተጻፈው ደብዳቤ በሚመለከታቸው የፖሊስ መኮንን ሳይፈረምበት ቀርቷል። በዚህም ምክንያት ይህ መግለጫ ይፋ እስከሆነበት ሰዓት ድረስ ጋዜጠኛ ተስፋለም በፍርድ ቤት የተረጋገጠለት የዋስትና መብት አልተከበረም" በማለት ሐቅ ሚዲያና ኮሚኒኬሽን ይፋ አርጓል።
ተስፋለም ለሚድያ ስራ ባለው ክብር እና ፍቅር የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ አጋጣሚዎች ለእስር ተዳርጎ እንደነበር ይታወሳል።
መረጃን ከመሠረት!




“የካበተ ልምድ ያለው ⁉️⁉️:-