የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ዘንድሮ በአንድ ፐርሰንት ገደማ ወደኋላ ቢንሸራተትም ከአፍሪካ ሁለተኛ ፈጣን እድገት እንደሚያስመዘግብ ተጠቆመ
(መሠረት ሚድያ)- በአለም ዙርያ የሚመዘገቡ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን በመከታተል አመታዊ ስሌታዊ ግምት (forecast) የሚያስቀምጠው አለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) አዲስ መረጃ አውጥቷል።
የተቋሙ ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት የእድገት ምጣኔ ይፋ የሆነ ሲሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በያዝነው የፈረንጆቹ አመት (2025) ከአምናው በርካታ ነጥቦችን ቢጥልም ዘንድሮ ከአፍሪካ ሁለተኛ ፈጣን እድገት እንደሚያሳይ ጠቁሟል።
በዚህም መሰረት ደቡብ ሱዳን በያዝነው አመት አንደኛ ቦታን ይዛ የኢኮኖሚዋ ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት (GDP) 24.3 ፐርሰንት እንደሚያድግ የተተነበየ ሲሆን ኢትዮጵያ እና ጊኒ የ7.2 ፐርሰንት በማስመዝገብ ሁለተኛ ቦታን በጋራ ይዘዋል። በሶስተኝነት ደግሞ ከዚህ በፊት በእድገት ሌሎቹን ሀገራት ትበልጥ የነበረችው ርዋንዳ ተቀምጣለች።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ሁለተኛ ቦታን እንደያዘ ይፋ ቢደረግም አምና አስመዝግቦት ከነበረው 8.1 ፐርሰንት እድገት ወደ 7.2 ፐርሰንት አሽቆልቁሏል፣ ይህም የ0.9 ፐርሰንት መንሸራተትን ያሳያል።
አይ ኤም ኤፍ ከሰሀራ በታች ያሉ ሀገራት አማካኝ እድገት 4.1 ፐርሰንት መሆኑን ጠቅሶ የቀጠናው ሀገራት ኢኮኖሚ መሻሻል እያሳየ መሆኑ አስታውቋል።
ብድር የማግኘት እድል መጥበብ፣ ኤክስፖርት የሚደረጉ ምርቶች ዋጋ መዋዠቅ እና የአለም የንግድ ስርዐት መናጋት ሀገራቱ ላይ የተደቀኑ ችግሮች መሆናቸው ተጠቅሷል።
በአይ ኤም ኤፍ ግምት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በመጪው የፈረንጆች 2026 አመትም በአንድ ነጥብ ወደኋላ ተንሸራቶ 7.1 እንደሚሆን ያሳያል። እንደ ኢትዮጵያ እና ናይጄርያ ያሉ ሀገራት ባከናወኗቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሞች ምክንያት የአንዳንድ የኢኮኖሚ ዘርፎች መነቃቃታቸውን የጠቀሰው አዲሱ የአይ ኤም ኤፍ ሪፖርት ቤኒን፣ ኮትዲቯር፣ ኢትዮጵያ፣ ርዋንዳ እና ዩጋንዳ ከፍተኛ እድገት ማስመዝገብ መቀጠላቸውን አስፍሯል።
እንደ ቡና ያሉ ምርቶች አሁን ላይ ጥሩ ዋጋ እያስገኙ በመሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት እየተጠቀሙ ይገኛሉ።
ይሁንና ሪፖርቱ የኢትዮጵያ የውጪ እዳ በየአመቱ እየጨመረ መጥቶ አሁን ላይ የኢትዮጵያ ብድር ከአመታዊው GDP አንፃር 46.7 መድረሱን አይ ኤም ኤፍ ይፋ አርጓል።
በሀገሪቱ ባሉ ግጭቶች ምክንያትም የአይ ኤም ኤፍ ድልድል ላይ 'በግጭት ውስጥ ያሉ ሀገራት' በሚል ስር ተካቷል። ኢትዮጵያ ከአበዳሪ ተቋማት ጋር እያረገችው ያለው የብድር ሽግሽግ ብዙ ርቀት መጓዝ ባለመቻሉ አበዳሪዎች ጉዳዩን ወደ ህግ ሊወስዱት እያሰቡ መሆኑን ከሁለት ቀን በፊት መዘገባችን ይታወሳል።
አይ ኤም ኤፍ የዘንድሮው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በ7.2 ፐርሰንት እንደሚያድግ ቢተነብይም ባለሙያዎች ብዙ ግዜ ይህ የቁጥር ጨዋታ እንደሆነ ያነሳሉ።
የኢኮኖሚ ባለሙያው አቶ ክቡር ገና በቅርቡ ለህዝብ እንዳስነበቡት የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ኢትዮጵያ ባለፈው አመት 7.1 ወይን የበለጠ በመቶ የኢኮኖሚ እድገት አስመዝግባለች የሚለው ቁጥር ወረቀት ላይ ያስደንቃል ይላሉ።
"መንግስትም ሆነ አንዳንድ አለም አቀፍ ተቋማት ዜናውን ለማስተጋባት ይፈጥናሉ፡፡ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ አመርታ ላይ እንደሆነች ያውጃሉ፡፡ ነገር ግን ዘወትር አንደሚሆነው ሁሉ ዜናው ሌላ ታሪክ አለው፡፡ እንደሚታወቀው ቁጥሮች ይፈበረካሉ፡፡ በመሬት ላይ ያለው እውነታን አይቶ እንዳላየ በማለፍ ቁጥሮች ይፈበረካሉ፡፡ እናም እውነታው በጠራራ ጸሀይ እንዲደበቅ ይደረጋል" የሚሉት አቶ ክቡር በጦርንት፣ በመፈናቀልና በዋጋ ንረት ፍዳዋን እያየች ያለቸውን ኢትዮጵያን በአለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገበች ያለች ሀገር ነች መባሉ ሌላ ታሪክ እንዳለው ያነሳሉ።
"ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይህ እድገት እንደ ህልም አለም በርቀት የሚሰማና የሚታይ ቅዠት እንጂ በዜጋው የዕለት ተዕለት ህይወት ውስጥ የሚታይ አይደለም" የሚለው የአቶ ክቡርን ፅሁፍ ነው።
"የሀገር ውስጥ አመታዊ ጠቅላላ ምርት (GDP) የተስፋ ዳቦ ነው። በዘመናዊ ኢኮኖሚክስ የሀገር ውስጥ አመታዊ ጠቅላላ ምርት ከአስማት ጋር የሚመሳሰል ገጽታ አለው፡፡ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ምጣኔ ጉዳይ ይበል የሚያሰኝ ነው ቢሉንም ውስጣዊ ይዘቱ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡ ለምሳሌ አምና የፌዴራል መንግስቱ ለካፒታል ፕሮጀክቶች የመደበው ከበጀቱ 35.5 በመቶ ዘንድሮ ወደ 38.6 በመቶ ቢያድግም በጀቱ በጦርነቱ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን ጭምር መልሶ ለመገንባት የሚውል በመሆኑ ነገሩን ውሀ ቅዳ ውሀ መልስ ያደርገዋል" ብለው አቶ ክቡር ያስረዳሉ።
"ጉዳዩን ትንሽ ጠለቅ ብለን ስናየው ደግሞ ከዘንድሮው የፌዴራል በጀት ውስጥ 19 በመቶ ለዕዳ ክፍያ የተመደበ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እናም የዕዳ ክፍያ ሀገሪቱ ለሌሎች ወሰኝ ልማቶችና ለኢንቨስትመንት ልታውለው የሚገባትን ሀብት ለእዳ ክፍያ በማዋል የማይሞላ ጉድጋድ ለመሙላት ከሚደረግ ጥረት ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ለዕዳ የሚከፈል ወጪ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ እንዳይሆነኑ እንቅፋት በመሆን እውነትኛ የኢኮኖሚ ሽግግር አንዳይኖር ሳንካ ይሆናል፡፡ እናም የአለም አቀፉ የገንዘብ ድረጅት እያደነቀ ያለው እንዲህ አይነቱን የትላንቱን ቁስል በማከም የነገውን የልማትና የእድገት ትልም ተግባራዊ ለማያደርግ የማያስችልን ለንቋሳ ኢኮኖሚ ነው" በማለት መረጃ አጋርተዋል።
-መሠረት ሚድያ-





