በምስሉ ላይ የሚታዩት አባት በአክሱም ሆስፒታል ሀኪሞች ስራ በማቆማቸው ህይወታቸው አልፎ ነው በሚል የሚሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ መሆኑ ተጋልጧል
(መሠረት ሚድያ)- “በአክሱም ሆስፒታል ሀኪሞች ስራ በማቆማቸው ህይወታቸው ያለፈን አዛውንት” በሚል ማህበራዊ ሚድያ ላይ እየተሰራጨ የሚገኘው ይህ ምስል የተሳሳተ መሆኑ ታውቋል።
በርካታ የፌስቡክ ገጾችና አካውንቶች ምስላቸው የሚታየው አዛውንት በትላንትናው እለት በአክሱም ሆስፒታል ህይወታቸው እንዳለፈ መረጃ እያጋሩ ይገኛሉ፣ መረጃው “የህልፈታቸው ምክንያት ደግሞ ሀኪሞች የስራ ማቆም ሰልፍ በግቢ ውስጥ እያካሄዱ ስለነበር ነው” ይላል።
በተጨማሪም “በመጨረሻም የድንገተኛ ክፍል ተረኛ የነበረው ሀኪም ጋወኑን አውልቆ ጠቅልሎ በላያቸው ላይ ጥሎ ዳግም ወደ ህክምና ላይመለስ እያለቀሰ ግቢውን ለቆ ወጣ” የሚል መረጃም ተካቷል።
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ቼክ የመረጃ ማጣርያ ዴስክ በምስሉ ላይ ባደረገው ማጣራት ይህ ምስል በትላንትናው እለት በአክሱም ሆስፒታል ህይወታቸው ያለፈን አዛውንትን እንደማያሳይ አረጋግጧል።
"ምስልን በምልሰት መፈለጊያ መገልገያዎችን በመጠቀም ባደረግነው ማጣራት ምስሉ ከ6 ቀናት በፊት ፌስቡክ እና ኤክስ (X) ላይ ተጋርቶ እንደነበር ተመልክተናል" ያለው ኢትዮጵያ ቼክ ምስሉን ያጋሩ አካውንቶች በትግራይ ክልል ሕፃፅ ከተማ የሚገኙ ተፈናቃይን እንደሚያሳይ ጠቁሟል፣ በከተማው የሚገኙ ተፈናቃዮች አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙና ትኩረት እንዲሰጣቸው በዚህ በቀደመ ፖስት ጥሪ ማቅረባቸውንም አክሏል።
ይህን ከቀናት በፊት የተጋራ ምስልና መረጃም ቀጥሎ ያሉትን ማስፈንጠሪያዎች በመጫን መመልከት እንደሚቻል ጠቁሟል: https://www.facebook.com/share/p/1AafEVYpJC/ እና https://x.com/tigrwayti/status/1919738488661881344?s=46&t=dmcdufxK8i9nmLEWi2-yGQ
ዛሬን ጨምሮ ከሰሞኑ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች እና ከተሞች የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ላለፈው አንድ ወር ከመብት፣ ደሞዝና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች ጋር በተገናኘ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ዘመቻ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን ከዛሬ ግንቦት 5፣ 2017 ጀምሮ ደግሞ ስራ የማቆም አድማ መጀመራቸው ታውቋል።
በዚህ ጊዜ በርካታ መረጃዎች ከተለያዩ አቅጣጫዎች እየተጋሩ ስለሆነ ይህም ለሀሰተኛ እና አሳሳች መረጃዎች እንዳንጋለጥ ተገቢውን ጥንቃቄ ህዝቡ እንዲያደርግ ኢትዮጵያ ቼክ አሳስቧል።
Via ኢትዮጵያ ቼክ



