በዛሬው ዕለት የሰባት አመት እስራት የተፈረደባቸው አቶ ታዬ ደንደዓ ባልተለመደ አሰራር ዛሬውኑ እቃቸው ተይዞ ወደ አባ ሳሙኤል እስር ቤት ተወሰዱ
(መሠረት ሚድያ)- የቀድሞው የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ ተገኘባቸው ከተባለ የጦር መሳርያ ጋር በተያያዘ በሰባት አመት ከሁለት ወር እስራት እና በአምስት ሺህ ብር መቅጣታቸው ይታወቃል።
አቶ ታዬ ለምስክርነት የጠሯቸው የመንግስት ከፍተኛ ሀላፊዎች ሳይቀርቡ ፍርዱ እንደተላለፈ የታወቀ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ውሳኔው ባሳለፈበት በዛሬው ዕለት ባልተለመደ መልኩ በፍጥነት ወደ አባ ሳሙኤል ማረሚያ ቤት መወሰዳቸውን ሚድያችን አረጋግጧል።
"አቶ ታዬ ዛሬውኑ እቃውን ሰብስበው ይዘውት ወደ አባ ሳሙኤል ተወስዷል፣ ብዙ ግዜ እንዲህ በፍጥነት ወደ ወህኒ ቤት ሰው የሚወሰደው በሰውየው ላይ ጥርጣሬ ሲኖር ነው" በማለት አንድ ጉዳዩን የሚያውቁ የመንግስት ሀላፊ ለሚድያችን ተናግረዋል።
ሚድያችን ከሌሎች የማረሚያ ቤት ሰራተኞች እንዳረጋገጠው ሌሎች ብዙ አመት የተፈረደባቸው ሰዎች ሶስት እና እና አራት አመት ድረስ ሳይቀር በቂሊንጦ እንደሚቆዩ ተናግረዋል።
"ቂሊንጦ ለቤተሰብ ቅርብ ስለሆነ ከማረሚያ ቤቱ ጋር ተነጋግረው እዚሁ ይቀራሉ። የአቶ ታዬ ሞራልን ለመንካት በሚመስል መልኩ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እያሉም የወጣቶች እና ህፃናት ማቆያ ውስጥ እንዲቀመጡ ተደርገው ነበር" በማለት እኚህ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ምንጭ ተናግረዋል።
እድሜያቸው ከአስራ ሰባት አመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች እና ሕፃናት 'ዞን አንድ' ውስጥ ለብቻቸው አንድ ቤት ተሰጥቷቸው እንደሚኖሩ የታወቀ ሲሆን አቶ ታዬም ከእነሱ ጋር ታስረው መቆየታቸው ታውቋል።
ሚድያችን ያሰባሰበው መረጃ እንደሚያሳየው አቶ ታዬ መጀመሪያ ሲታሰሩ የገቡት 'ዞን አምስት' የሚባለው ቦታ ነበር። ይሁንና ዞን አምስት ውስጥ የፋኖ አመራሮች ናቸው ተብለው ከተጠረጠሩ ግለሰቦች ጋር 'ጥሩ ግንኙነት አለው' በሚል ወደ ዞን አንድ መወሰዳቸው ታውቋል።
ዞን አምስት ውስጥ በተለይ ከዶ/ር ወንደሰን አሰፋ እና ከአቶ ዮሐንስ ቧያለው ጋር ጥሩ ግንኙነት ፈጥሯል የሚል ጥርጣሬ እንደነበር መረጃዎቻችን ያሳያሉ።
"ዞን አንድ የተባለ የአጥፊ የሕፃናት እና የታዳጊ ወጣቶች ማቆያ ውስጥ አስገብተውት ተረብሾ ነበር። በሽምግልና እባካችሁ ተብሎ የማረሚያ ቤቱ ሀላፊ ተጠይቆ ወደ ዞን ሁለት እድሜያቸው ከገፉ ሰዎች ማቆያ ቤት አቆይተውት ዛሬ ተፈርዶበት ሲመለስ ወዲያውኑ አስወጥተው ወደ አባ ሳሙኤል አቻኩለው ወስደውታል" በማለት ምንጫችን አስረድተዋል።
-መሠረት ሚድያ-



