8ኛው ግራንድ አፍሪካን ረን የታዋቂ አትሌቶች ተሳታፊነት እና የ2026 ቶዮታ ኮሮላ ሽልማትን ይዞ ሊካሄድ ነው
(መሠረት ሚድያ)- በዋሽንግተን ዲሲ፣ ሜሪላንድ እና ቨርጂኒያ አካባቢ የሚካሄደውና የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ለማቀራረብ የሚዘጋጀው 8ኛው ግራንድ አፍሪካን ረን በፈረንጆቹ አቆጣጠር በመጪው ኦክቶበር 10, 2026 (ጥቅምት 1, 2019 ዓ.ም.) እንደሚካሄድ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ተደረገ።
‘አብሮነት መሻል ነው’ በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ዝግጅት፤ የዲያስፖራውን ማህበረሰብ ማሰባሰብ፣ በውጭ ሀገር የሚያድጉ ህፃናትና ወጣቶች ከባህላቸው ጋር እንዲቀራረቡ ማድረግ እና ለተለያዩ ማህበራዊ በጎ ስራዎች ገቢ ማሰባሰብን ዋና ዓላማው ያደረገ ነው። ለዝግጅቱ የሚሆን የምዝገባ ሂደት በአዘጋጆቹ ኦፊሴላዊ ዌብሳይት (www.africanrun.com) ላይ መጀመሩም ተገልጿል።
የዝግጅቱ ቀዳሚ አጋር የሆነው አሌክሳንድሪያ ቶዮታ ለተሳታፊዎች የሚሆን የ2026 ቶዮታ ኮሮላ መኪና በሽልማት መልክ አዘጋጅቷል። “ሁሉም አሸናፊ ነው” በሚለው የዝግጅቱ መርህ መሠረት፣ በሩጫው የተሳተፈ ማንኛውም ሰው ርቀቱን ያጠናቀቀበት ሰዓት ሳይወሰነው በቀረበው የመኪና ሽልማት ዕጣ ውስጥ እኩል የመሳተፍና የማሸነፍ ዕድል ይኖረዋል። አሸናፊውም በውድድሩ ማጠቃለያ ላይ በሚወጣ የሎተሪ ዕጣ የሚለይ ይሆናል።
በዘንድሮው 8ኛ ዙር ዝግጅት ላይ ታዋቂዎቹ አትሌቶች ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ፣ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ እና አትሌት ስለሺ ስህን በክብር እንግድነት ተገኝተው ተሳታፊዎችን እንደሚያበረታቱ ታውቋል። አትሌት ደራርቱ ቱሉ ለዝግጅቱ ያላትን ድጋፍ ስትገልፅ “ሀገራችንን በዓለም መድረክ ያስጠራው የአትሌቲክስ ስፖርት በውጭ ለሚገኙ ወገኖቻችን የመሰባሰቢያ መድረክ መሆኑ ዝግጅቱን ልዩ ያደረገዋል” ብላለች።
በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ የተገኙት የአሌክሳንድሪያ ቶዮታ፣ የኢትዮ ቴሌኮም፣ የዳሽን ባንክ፣ የጊፍት ሪል እስቴት፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እና የሮሚንግ ሮስተር ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ያላቸው ተወካዮች በበኩላቸው፤ ከተቋሞቻቸው ማህበራዊ ኃላፊነት አንጻር ከግራንድ አፍሪካን ረን ጋር ያላቸውን አጋርነት በመግለፅ ለዝግጅቱ ስኬት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።
የውድድሩ ዋና አዘጋጅ ዶክተር ጋሻው አብዛ ዝግጅቱ ከአንድ ቀን የ5 ኪሎ ሜትር የቤተሰብ ሩጫ ባሻገር፣ የዲያስፖራውን ማህበረሰብ እርስ በእርስ በማቀራረብ ረገድ ከፍተኛ ድልድይ እየሆነ መምጣቱን ገልጸዋል።
ግራንድ አፍሪካን ረን በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በሁለተኛው ቅዳሜ የሚካሄድና ብዙሃኑን የሚያሳትፍ ዓመታዊ የጎዳና ላይ የመዝናኛ ሩጫ ሲሆን፣ ዘንድሮ ለ8ኛ ጊዜ ይካሄዳል።
ለበለጠ መረጃ እና ለምዝገባ የNova Connections ድረ-ገፅን መጎብኘት እንደሚቻል ተገልጿል: www.africanrun.com
| መሠረት ሚድያ |


