ጆሮ ዳባ ልበስ የተባለው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ውስጥ ዜጎች ላይ የሚደርሰው እንግልት
(መሠረት ሚድያ)- ከዚህ በፊት በዚህ ሚድያም ሆነ በሌሎች ሰዎች በኩል ስለ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምንዛሬ ቢሮ የተለያዩ ቅሬታዎችና ጥቆማዎችን ስንሰማ እንደነበር የሚታወቅ ነገር ነው።
ታድያ መንግስት እንደጥቆማ የሚጠቀምበት መሠረት ሚድያ ያደረሰውን ዘገባ ማስተካከያ ተደረገበት ወይስ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ባንኩ ጉዳዩን ከምንም አልቆጠረውም? የሚለውን ለማየት ያደረገኝ ጉዳይ ከሰሞኑ የተቋሙን የምንዛሬ ቢሮ ለመጎብኘት እድሉ ገጥሞኝ ስለነበረ በሚድያ የሰማሁትና መሬት ላይ የገጠመኝ ምንድነው የሚለውን ለመግለፅ ነው።
በአሁኑ ወቅት ተደጋጋሚ ጥቆማዎችና ብልሹ አሰራርን እየተከታተለ የሚያሰማው መሠረት ሚድያ የብዙ ሰዎችን እንባ እያበሰ ያለና በመንግስት በኩልም ማስተካከያና ክትትል ለማድረግ እንደሚጠቀምበት ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ላይ የተደረገውን የምታውቁት ጉዳይ ነው።
ምነው ታድያ ግዙፉና ትልቁ መንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ስለ ምንዛሬ ቢሮው ከአንድም ሁለት ጊዜ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲሰማ ማስተካከያ ለማድረግ ምን አገደው የሚለው በጣም ስላስገረመኝ ነው።
እንኳን የፋይናንስ ተቋም ይቅርና ሌሎች ተቋማትም ቢሆኑም የተነሳባቸውን ቅሬታ ለማረም ነገ ዛሬ እንደማይሉ መታወቅ አለበት።
ሌላው መንግስት አዲስ የኢኮኖሚ ሪፎርም አደረኩ ካለ በኋላ ብሔራዊ ባንክን ጨምሮ ከተለያዩ ባንኮች እና ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚወጣው መረጃ እንደሚያሳየው የዶላር አቅርቦት በፊት ከነበረው የተሻለ እንደሆነ እና ደንበኞች ለውጭ ንግድ ጨምሮ ለጉዞ የሚፈልጉትን የዶላር መጠን መውሰድ እንደሚችሉ እንሰማለን።
ነገር ግን አሁን ላይ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ቢሮ ለደንበኞች የሚሰጠው እጅግ ዝቅተኛ እና ለዛውም አሰራርና ግልፅነት የጎደለው መሆኑን እኔም እንዳረጋገጥኩትና የተለያዩ ደንበኞችም በተለያዬ ጊዜ ሲናገሩ ይሰማሉ።
ባንኩ ውጭ ላይ ደንበኞች የሚቀመጡበት ቦታ ያስቀመጠውን ያረጀና የተቀዳደደ የደንበኞች አስተያዬት መስጫ ምንም እንኳን ለራሱ አገልግሎት የሚጠቀምበት ቢሆንም የተወሰነውን ለማዬት እንደሞከርኩት ተቋሙ ማስተካከያ የማያደርግበት ከሆነ አስተያዬት መስጫውን ማስቀመጥ ለምን እንዳስፈለገው ሊገባኝ ግን አልቻለም።
ምክንያቱም በተለያዩ ደንበኞች የተፃፉት አስተያየቶች የሚያሳዩት እጅግ እንግልትና ብሎም በተቋሙ የስራ ኃላፊዎች ዘለፋና ማንቋሸሽ እንደሚደርስባቸው ነው።
አስተያዬት መስጫ ብቻውን መፍትሔ የሚሰጥ ይመስል ድሪቶ አስተያዬት መስጫ መጎለት ጥቅሙ ምን ይሆን?ምን አልባት ተቋሙ ቀልጣፋ አገልግሎትና ተመጣጣኝ ምንዛሬ ለደንበኞቹ መስጠት የከበደው ምንድነው ስል እንደ አንድ የባንኩ የረጅም ጊዜ ደንበኛ በመቆርቆር ስሜትና የተቋሙን ሐገራዊ ሚና በማሰብ አንድ የተቋሙን ሰራተኛ ለማናገር ሞክሬ ነበር።
እሱም ከእኔ በበለጠ የመቆርቆር ስሜት ውስጥ ሆኖ ተቋሙ ትልቅና ሐገራዊ ሚናው የጎላ ግዙፍ ባንክ ነው ግን ምን እንደተፈጠረ ባይታወቅም ማለቴ ለእኔ ባይገባኝም ባንኩ እጁን ከቅርንጫፉ ላይ ያነሳ ነው የሚመስለው።
በመቀጠል አለኝ የቅርንጫፉ አደረጃጀት በዲስትሪክት ደረጃ ቢሆንም ነገር ግን ቅርንጫፉ ስለሚሰራው ስራ የዲስትሪክት የስራ ኃላፊዎች መረጃ የላቸውም፣ ማዘዝም አይችሉም፣ የተሰጠውን ፕላን ብቻ ቅርንጫፍ ካሳካ ዲስትሪክቱ ደንታ የለውም።
ባንኩ ግን እንደ ባንክ ቅርንጫፉን የማስተካከልና የማረም ፋላጎት የለውም ምክንያቱም ለየትኛው ደንበኛ ስንት ይሰጠው፣ ስንት ለሚፈልገው ምን ያህል የውጭ ምንዛሬ ይፈቀድለት የሚለው የተፃፈም ሆነ ሌላ ባንኩ ያስቀመጠው አሰራር የለም።
ከፈለጉ እና ከነሱ ጋር ከተዋወክ የተሻለ የውጭ ምንዛሬ ይሰጡሀል፣ ካልፈለጉ ደግሞ 200 እና 300 ዶላር ይሰጡሀል። አብዛኛው 90 በመቶ የሚሆነው ደንበኛ 200እና 300 ዶላር ነው ይዞ የሚሔደው። ስለዚህ ምንም አሰራር ባልተቀመጠበት ነው ደንበኞች ቅሬታና ወቀሳ እያቀረቡ ያሉት። ይህ የባንኩ የበላይ አካል ሊያየው የሚገባ ጉዳይ ነው ብሎ ተሰናበተኝ።
በመጨረሻም ግን ማለት የምፈልገው ብሔራዊ ባንክ ምን ይላል?
1ኛ. ተጠያቂነት ስለሌለበት አሰራር
2ኛ. ደንበኞችን ስለማጉላላትና ተገቢውን መስተንግዶ አለመስጠት
3ኛ.ለደንበኞች በቂና ተመጣጣኝ የውጭ ምንዛሬ አለማቅረብ
4ኛ.የውጭ ምንዛሬ ቢሮ እንዴት መመራት እንዳለበት
በተጨማሪም ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመሪያ /FXD/01/2024 የውጭ ጉዞ ያላቸው የግለሰብ ደንበኞች እስከ 10,000 ዶላር፣ ለድርጅት ደንበኞች ደግሞ 15,000 ዶላር መውሰድ ይችላሉ ይላል።
ቅሬታ የሚነገራቸው የቅርንጫፉ ሀላፊዎች ሲጠየቁ 'ዋናው ኃላፊ ጋር ሒድ፣ እኔ ልሰጥህ የምችለው ይህን ነው?' ይላሉ። ነገር ግን ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሰጠኝ የጠየኩት ጥያቄ እሱ ሳይሆን ሌሎች ሰራተኞች መረጃ ይነግሩሐል ብሎ ዘጋብኝ። ዋና የተባለው ሰው ጋር ስሔድ ልሰጥህም፣ ልነሳህም ስልጣን ያለኝ እኔ ነኝ በሚመስል ሁናቴ እና ካልፈለክ ተወው በማለት 300 ዶላር የነበረውን 500 ዶላር አደረገው።
ነገር ግን እኔን እዚህ ያመጣኝ ደንበኝነቴ ነው፣ እንዴት እንደዚህ ይሆናል? ሰው መማፀን ይኖርብኛል? በማለት ለማስረዳት ያደረኩት ሙከራ ባይሳካም ከነበረኝ ጊዜ አንፃር አማራጭ ስላልነበረኝ ሰውየው የቸሩኝን ዶላር ለመውሰድ ተገደድኩኝ።
ባንኩ ላይ ያለው ሁኔታ እንዲህ በእኔ ብዕር የሚገለፅ ሳይሆን መሠረት ሚድያን ጨምሮ ሌሎች አካላትም ተጨማሪ የምርመራ ዘገባ ሊሰሩበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን። -መሠረት ሚድያ-




