የባንክ ሰራተኞች በግዴታ ደንበኛ እንዲያመጡ የሚያስገድዱበትን አሰራር እንደሚመረምር ብሔራዊ ባንክ ለሚድያችን አስታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- በትናንትናው ዕለት ለንባብ ባበቃነው አንድ ዘገባችን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ከዘመን ባንክ ውጭ ያሉ በርካታ የግል ባንኮች ሰራተኞቻቸው ላይ ኮታ በመጣል በግዴታ አዲስ የባንክ አካውንት እንዲያስከፍቱ እያረጉ እንደሆነ ገልፀን ነበር።
በዚህ ሪፖርታችን ላይ አንዳንድ የባንኮች አመራሮች ሰራተኞቻቸው ላይ ከፍተኛ የስራ ጫና በማድረግ፣ አዲስ አካውንት የማስከፈት ግዴታ በመጣል እንዲሁም ከፍ ሲል ስድብ እና ከስራ መባረር እያስከተሉባቸው እንደሆነ አንስተናል።
ሚድያችን ይህን መረጃ ይዞ የብሔራዊ ባንክ ገዢ አቶ ማሞ ምህረቱን ምላሽ የጠየቀ ሲሆን የተባለውን አሰራር ብሔራዊ ባንክ እንደሚመለከተው አጭር ምላሽ ሰጥተዋል።
አንድ ስሜ እና የስራ ድርሻዬ ለግዜው አይጠቀስ ያሉ ሌላ የብሔራዊ ባንክ አመራር ደግሞ ድርጊቱን የመከታተል እና ስርዐት የማስያስ ሀላፊነት ብሔራዊ ባንክ እንዳለበት ጠቅሰው በሰራተኞች የተነሳውን ቅሬታ እና የመብት ጥሰት ጭምር በጥልቀት እንደሚያዩት ተናግረዋል።
"እውነት ለመናገር ጉዳዩን አናውቀውም ወይም አልሰማንም ማለት አልችልም፣ ነገር ግን በተባለው መጠን ሰራተኞች እየተንገላቱ እና ከስራቸው እስከመባረር ጭምር እየደረሱ ከሆነ እናየዋለን። ተጋኖ የቀረበ ከሆነው ውጤቱ ይነግረናል" ብለዋል።
ትናንት ያቀረብነውን ዘገባ ተከትሎ አንዳንድ ባንኮች 'እኛ ጋር ድርጊቱ አይፈፀምም' የሚል መልዕክት ለመሠረት ሚድያ አድርሰዋል።
ይሁንና የዜናውን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ በርካታ የቅሬታ መልዕክቶች እስካሁኑ ሰዐት ድረስ እየተላከልን ይገኛል። የተወሰኑትን ከዚህ በታች እናቀርባለን።
- "በባንክ ሰራተኞች ላይ ያነሳችሁት ነገር ገብርኤልን ምርር ነዉ ያለን፣ እኔ የሚደርሰኝ ደሞዝ 15ሺ ነዉ ከዚህ ላይ 2,000ሺ ብር አዲስ ሰዉ ለማስከፈቻ እጠቀማለሁ አሁንማ በቀን 4 ከአልተከፈተ የሰራተኝነታችን ነገር ያበቃል ህዝቡ ደግሞ ስልችት ነዉ ያለዉ የባንክ ሰራተኛ ባያዩ በጣም ደስታቸዉ ነዉ ይደበቃሉ አሁን አሁንማ እኔ የምሰራ አባይ ባንክ አስፈላጊ ከሆነ ደግሞ ቡዙ መረጃዎችን አሰጣለሁ።"
- "የአቢሲኒያ ባንክ ሠራተኛ ነኝ፣ የተባለው ሁሉ እኛ ጋርም አለ"
- "አንድ የግል ባንክ የሚሰራ ወንድሜ በየወሩ እንደ ቤት ኪራይ ለአዲስ ሂሳብ መክፈቻ ብሎ በየወሩ 3000ሽ ብር ያስቀምጣል"
- "አዋሽ ባንክ አካውንት አላስከፈታችሁም ቢለር አክቲቭ አላደረጋችሁም በማለት ሰራተኞቹን እያባረረ ነው። የሚገርመው አሁን እያባረራቸው ያሉትን ሰራተኞቹን ሲቀጥር እስከ 150,000 ብር ተቀብሎ ነው።"
- "ስለ ባንክ ያነሳችሁት ሀሳብ በጣም ለኛ ወሳኝ ሀሳብ ነው ግፉበት እኛ እኮ ተሳቀን ሞትን ሰው መሳይ በሸንጎ ነን ልብስ ለብሰን ስንሄድ ሰው እንመስላለን አንድ ቀን የሰላም እንቅልፍ እንኳ አንተኛም ገንዘባችንን ብቻ ሳይሆን ጤናችንን ነው እያጣን ያለነው ከንግድ ባንክ አመሰግናለሁ"
- "በባንክ ሠራተኞች ላይ የሠራችሁትን አንብበነዋል፣ እንደዚህ የሚያየን ሚድያ በማግኘታችን በጣም ነው ደስ ያለን። ይሄ ችግር በሁለት ባንኮች ብቻ ሳይሆን ከዘመን እና ንግድ ባንክ ውጪ በሁሉም ባንኮች ላይ ተግባራዊ እየሆነ ያለ ነገር ነዉ። በዚህ ኑሮ ልጆች አሳድገን ቤት ኪራይ ከፍለን በተጨማሪ ሳይፈልጉ ለምነን ከፍተን ለማይጠቀሙበት አካውንት ያለንን አሟጠን እሱም አይበቃን ተበድረን ገቢ እናደርጋለን በጣም ጭንቀት ላይ ነው ያለነው። ቢሮ ውስጥ ያለውን ጭቅጭቅና ማስፈራራቱን ተወዉ ሰው ባንከር ሲባል ተመችቶን የምንኖር ነው የሚመስለው ደመወዛችንን እነኳን መልሰን ለባንኩ ገቢ አድርገን ወር መድረስ እንኳን እንዳቃተን አያውቅም ከዚህም የከፋው ፀሀዩ በሽተኛ አድርጎናል”
- "በባንኮች ዙርያ ያወጣችሁት መረጃ ትክክል ነው።እኔ 12 አመት የባንክ የስራ ልምድ ሲኖረኝ በሁለት ባንኮች የአሁኑን ጨምሮ በስራ አስኪያጅ መደብ እያገለገልኩ ነው።ዋናው ጫና ከበላይ የሚመጣና በተለይ ስራ አስኪያጅ የተባለውን ተቀማጭ ካላመጣ የደሞዝ ቅጣት ጀምረዋል በዚህም አዋሽ ሲቀጥል እነ አባይም ጀምረዋል። እናም ታች ያለው ላይ ያለው ጫና የመጣው ከላይ እንጂ ስራ አስኪያጅ ወዶት አይደለም"
- "በአሁኑ ሰዓት ባንኮች አንዱ ሌለውን ለመብለጥ የምያደርጉት ምንም ፍሬ የማይሰጥ ፉክክር መሠረተኞች እንድሰቃዩና እንድማረሩ ማድረግ ከጀመረ ቆይቷል።ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ በግል ባንኮች በሁሉም ማለት ይቻላል የለ መከራ ነው።ደንበኞች አንድ ስምንት በ'X' ባንክ ብረቻውን አስቀምጠው በሁላተኛ ስምንትበ 'Y' እያስቀመጡ ሠረተኛ ስላስቸገረ ብቻ rotate ማድረግ ሌላኛው ችግር ነው ለብሔራዊ ባንክ እንደዚህ ብልሹ አሠሪራር እንድቆምና ባንኮች merge ሆነው ለአገሪቱ የምጠቅም ሥርዐት እድሰፍን ድምፅ ሁኑ"
- "የተሰቃየን ነው በተለይ የአዋሽ ባንክ ሰራተኞች እባክህ ድምፅ ሁነን በየቀኑ ከኪሳችን ለአዲስ አካውንት 200 ብር እናዋጣለን በmerchant activation ብለው ሲያስጨንቁንም በቋሚነት የደሞዝ ቀን 1500 እናዋጣለን !ደሞዛችንን ግማሽ እራሱ ባንኩ ነው የሚወስድብን"
- “በዚህ ዙሪያ ተከታታይ ዘገባዎችን እንደምትሰሩልን እናምናለን። ነገሩን ጠለቅ ብላችሁ ብታዩልን ምን አይነት የሰቆቃ ቀምበር ተጭኖብን እየኖርን እንደሆነና በየቀኑ የምናሳልፈው ህይወት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ቢያንስ ጭንቀታችን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንዲደርስልን ብታደርጉልን ምኞቴ ነው። እንደ ሀገር ችግራችን ሲበዛ ጊዜ እኛም ችግራችንን መናገር ፈራን፣ አሁን ኢትዮጽያ ውስጥ ካለው የከፋ ችግር አንፃር የባንክ ሰራተኞች ተቸገርኩ ቢል ማን ያምነዋል ብለን በየቀኑ የምሬት ህይወት እያሳለፍን እንገኛለን።"
- "ኦሮሚያ ባንክም ይገኝበታል በጣም ተቼግረናል፣ ደመወዛችንን ለማስከፈት ነው የምናውለው ። ኑሮወም ከብዶናል። አዲስ አካውንት ማስከፈት እቅድ የሚሰጠው ከአመት አመት በጣም እየጨመረ መጥቷል። በአንፃሩ ደግሞ የሰው አካውንት የመከፈት ፍላጎቱ በጣም እየቀነሰ መጥቷል። ግን በጣም የሚገረመኝ በእንድ ቅርንጫፍ ከ3 እስ 6 ሰው የመድቡና ለበጀት አመቱ አዲስ አካውንት 4300 ታርጌት ይሰጥሃል ለአንድ ሰራተኛ እስከ 1100 አካባቢ በአማካይ ማለት ነው። ... ሰዎች በአንድ አመት ውስጥ ተወልደው በዛኑ አመት የባንክ አካውንት ለመክፈት እድሚያቸው አይደርስም። እና ከየት አምጥተን ይሄን ሁሉ አካውንት የምናስከፍተው!⁉"
- "እኔ በስራ አስኪያጅ የስራ ድርሻ ላይ የምሰራ የባንክ ሰራተኛ ነኝ ...ነገር ግን የባንክ የስራ ሁኔታ ከጊዜ ጊዜ በጣም እየተቀየረ መጣ ...ልክ አንተም እነደዘገብከው አካውንት ለማስከፈት ከኪሳችን በየእለቱ ብር እናወጣለን, ድጂታል ላይ ደግሞ በአዋሽ ባንክ በኩል "Biller Activation" የሚባል ነገር አለ አክቲቭ ለማድረግ ልክ እንደ አካውንት ከፈታው 100 ብር እናወጣለን ...ይህ ደግሞ በጣም የሚያስጠላው ነገር በየወሩ ግዴታ Active መደረግ አለበት እውነት ነው የምልህ አንድ በቅርብ የምታገኘው የአዋሽ ባንክ ሰራተኛ ስለ "Biller Activation" ብትጠይቀው ከአካውንት ከፈታው በላይ በጣም ወጭ እያሶጣን ያለው ይህ ነው...ቢያንስ እኔ ያለማጋነን በዚህ ምክንያት በትንሹ በየወሩ ከ3,000 ብር በላይ አወጣለሁ"
- "የዘገባችሁት በጣም ልክ ነው፣ የባንክ ስራ ልመና ሆኖብናል ደግሞ ግን ሁሉም ባንክ ነው ዳሽን ባንክም የሚሰጠን Target የማይደረስ ነው ላለመባረር ስንል ከኪሳችን እናወጣለን። ባለፈው አመት ከ 5000ብር በላይ አውጥቻለሁ በግሌ እድገት እንዳይከለክሉኝ እና tareget ለማሟላት። የባንክ ስራ ውርደት ነው አሁን። የሰውን ስድብ እና ምሬት ብትሰማ ደግሞ መፈጠርህን ትጠላለህ። pls ታግላቹህ አስቀሩልን"
- "እኔ አንድ የግል ባንክ ውስጥ መስራት ከጀመርኩ 3 አመት ሆኖኛል። እጅግ በጣም አስጠሊታ 3 አመታት። ወላሂ ከኖርኳቸዉ 25 አመታት ዉስጥ የተረገሙ 3 አመታትን አሳለፍኩ።አንድ ነገር ልንገርህ ዛሬን በሠላም ማደር አልችልም ምክንያቱም ነገ የት እንደምሔድ ሀሣብ ይሆንብኛል። እንዴት እንቅልፍ ይወስደኛል።በየ ቀኑ ደብዳቤ ይላካል። ቢሮ ውስጥ ጭቅጭቅ ነዉ። አንዷ የስራ ባልደረባየ ከ 3 ወር በፊት ለቃ ወደ ቤተሰቦቿ ሔደች። ወላሒ ነው ብዙ የአዕምሮ ችግር ሁሉ እየተፈታተነን ነው። የድሮ ባርነት የዚህን ያህል ይከፋ ይሆን ? አላውቅም ። ከደሴ"
-መሠረት ሚድያ-


