በድሬዳዋ በአንድ የግል እጩ ተወዳዳሪ ላይ በመንግስት አካላት እየተፈፀመ የሚገኝ መጠነ ሰፊ የማጥላላት፣ የማስፈራራት ዘመቻና የፍትህ መጓደል አነጋጋሪ ሆኗል
(መሠረት ሚድያ)- በመጪው ሀገራዊ ምርጫ በድሬዳዋ የምርጫ ክልል የግል እጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ዶክተር ሀብታሙ አለሙ በከተማዋ ከሚስተዋለው ብልሹ አሰራርና ሙስና ጋር በተያያዘ ስር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ቢነሱም ከፍተኛ የመብት ረገጣና የማጥላላት ዘመቻ እየደረሰባቸው መሆኑን ገለጹ።
ዶክተር ሀብታሙ በሙያቸው በድልጮራ ሆስፒታል የሚያገለግሉ ጠቅላላ ሀኪም ሲሆኑ በምርጫው ወቅት ከገዥው ፓርቲ እጩና ከከተማዋ ከንቲባ አቶ ከዲር ጁሀር ጋር ለፉክክር መቅረባቸውን ተከትሎ በማህበራዊ ሚዲያ የስም ማጥፋትና የዛቻ ድርጊቶች እየተፈጸሙባቸው ይገኛል።
በተለይም የሌሊት ታክሲ ሹፌሮች ሊቀመንበር የሆነው 'ቃልኪዳን ፀሀይ' የተባለ ግለሰብ ከተለያዩ ግብረ አበሮቹ ጋር በመሆን በፌስቡክ ገጹ የዶክተር ሀብታሙን ምስል ከእንስሳት ጋር በማቀናጀትና የሀሰት መረጃዎችን በማሰራጨት የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ ቁጥር 1162/2011 አንቀጽ 134 እና 135ን የጣሰ ተግባር እየፈጸመ መሆኑን አያይዘው ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ተጎጂው እጩ ጉዳዩን ለድሬዳዋ ፖሊስ፣ ለፌደራል ፖሊስ፣ ለአቃቤ ህግና ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ ቢያሳውቁም እስካሁን ድረስ ተገቢው የህግ እርምጃ አለመወሰዱን ተናግረዋል።
ግለሰቡ ከፖሊስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው ካድሬ በመሆኑ በድሬዳዋ ፖሊስ ሀላፊዎች ከለላ እየተደረገለት እንደሚገኝና የፌደራል ፖሊስም መጀመሪያ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ቃል ቢገባም በኋላ ላይ ግን ጉዳዩን ችላ በማለት ተጠርጣሪውን ለይቶ ከመያዝ ይልቅ ለእጩው የሰጡት ምላሽ አጥጋቢ እንዳልሆነ አመልክተዋል።
ዶክተር ሀብታሙ ለፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባስገቡት ደብዳቤ ላይ እንደገለጹት "Naimaa Guyoo"፣ "Aymen Salah" እና "Gero Bire" የተባሉ የሀሰት የፌስቡክ አካውንቶች ስማቸውን ለማጠልሸትና ህዝብ በእሳቸው ላይ ያለውን አመኔታ እንዲያጣ ለማድረግ ሌት ተቀን እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በድሬዳዋ የማህበራዊ አንቂና የዶክተር ሀብታሙ የቅርብ ጓደኛ የሆነው ወጣት በቃሉ ምስጋናው በማህበራዊ ሚዲያ መረጃ በመስጠቱ ብቻ ከሁለት ወር በላይ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ሌላኛው የፍትህ መጓደል ማሳያ ሆኖ ቀርቧል።
ፖሊስ በማስረጃ የተደገፈ የወንጀል አቤቱታ የቀረበበትን ግለሰብ በነጻነት ሲያዘዋውር በበጎ አድራጎት ስራዎች የሚታወቀውን ወጣት በቃሉን ያለበቂ ምክንያት ማሰሩ በከተማዋ ወጣቶች ላይ ፍርሃት ለመልቀቅና ደጋፊዎችን ለማሸሽ የታለመ ስልት መሆኑን እጩ ተወዳዳሪው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ለፌደራል ፖሊስ ጉዳዩ እንዲታይ ደብዳቤ ቢጽፍም በተግባር የታየ ለውጥ ባለመኖሩ ጉዳዩ ወደ ሚዲያ እንዲወጣና ህዝቡ የእኩልነትና የፍትህ ጥያቄው እንዲመለስ ድምጽ እንዲሆንላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
ዶክተር ሀብታሙ አለሙ በማስረጃነት ባቀረቧቸው የፌስቡክ ምስሎች ላይ እንደሚታየው ቃልኪዳን ፀሀይ የተባለው ግለሰብ "በበግ ጠባቂነት እንኳን አደራ ለማይሰጥ ሰው የድሬዳዋ ተወካይ በማድረግ ስህተት አንሰራም" የሚሉና እጩውን የሚያጥላሉ ጽሁፎችን ሲያጋራ ቆይቷል።
በተጨማሪም በህክምና ልብሳቸው ላይ የጭንብል ምስል በመለጠፍ "የፊርማ ንግድ አጭበርባሪው" በሚል ስም በማጥፋት ላይ እንደሚገኝ ከ screenshots ለመረዳት ተችሏል።
ይህ አይነቱ ድርጊት በነጻና ፍትሀዊ ምርጫ ላይ ጥቁር ነጥብ የሚጥል በመሆኑ የሚመለከታቸው የፍትህ አካላትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ጉዳዩን በአንክሮ ሊመለከቱት እንደሚገባና የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ እጩ ተወዳዳሪው በጽኑ አሳስበዋል።
| መሠረት ሚድያ |






