በካናዳ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የቀድሞ አምባሳደሮች መኖሪያ ቤትን ለማፍረስ ማመልከቱ በሀገሪቱ የቅርስ ተሟጋቾች ዘንድ ቁጣን ቀሰቀሰ
(መሠረት ሚድያ)- ካናዳ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኦታዋ ከተማ 'አይላንድ ፓርክ ድራይቭ' ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውንና ለበርካታ አስርት ዓመታት ለአምባሳደሮች መኖሪያነት ሲያገለግል የነበረውን ታሪካዊ ሕንፃ ለማፍረስ ያቀረበው ማመልከቻ በከተማዋ አስተዳደርና በአካባቢው የቅርስ ጥበቃ ተሟጋቾች መካከል ከፍተኛ አለመግባባት መፍጠሩን የሲቢሲ ኒውስ (CBC News) ዘገባ አመልክቷል።
የኦታዋ ከተማ አስተዳደር በቁጥር 575 አይላንድ ፓርክ ክሬሰንት (575 Island Park Cres.) ላይ የሚገኘውን ይህንን የአንድ መቶ ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረ ሕንፃ ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ ለማቆየትና በቅርስነት ለመመዝገብ ጥረት እያደረገ ቢሆንም የሕንፃው ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ሕንፃው ከአቅም በላይ በመጎዳቱና ለደህንነት አስጊ በመሆኑ ሊፈርስ ይገባል የሚል አቋም ይዟል።
ይህ እ.ኤ.አ. በ1927 የተገነባውና በአካባቢው ካሉት ጥንታዊ መኖሪያ ቤቶች አንዱ የሆነው ሕንፃ በኢትዮጵያ መንግሥት የተገዛው እ.ኤ.አ. በ1993 ነበር። ሆኖም ሕንፃው ለረጅም ዓመታት ሳይታደስና ጥገና ሳይደረግለት ባዶውን በመቀመጡ ምክንያት አወቃቀሩ ሙሉ በሙሉ መጎዳቱንና ለመኖሪያነት የማይበቃበት ደረጃ ላይ መድረሱን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለማፍረስ ባስገባው ማመልከቻ ላይ ገልጿል።
የካናዳ የቅርስ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ አምባሳደር ቴዎድሮስ ግርማ ኤምባሲው ሕንፃውን ለመጠገን ከከተማዋ የቅርስ ዕቅድ አውጪዎች ጋር ለ18 ወራት ያህል ሲመክር እንደቆየ አስታውሰዋል።
ሆኖም ሕንፃው የደረሰበት መበላሸት እጅግ ከፍተኛ በመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ እሱን መልሶ ለመጠገን የሚወጣው ወጪ ከኢኮኖሚ አንጻር አዋጭ እንዳልሆነ አስረድተዋል። አምባሳደሩ አክለውም ኤምባሲው በአሮጌው ሕንፃ ምትክ የቀድሞውን የስነ-ሕንጻ ውበት፣ ስፋትና ታሪካዊ ገጽታ በቅርበት የሚያንጸባርቅ አዲስ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት ለመገንባት ማቀዱን ገልጸዋል።
"የድሮው ሕንጻ ዋና ማንነቱና ይዘቱ ሙሉ በሙሉ ከጠፋ በኋላ ፍርስራሹን ብቻ ይዞ መቆየት ቅርስን መጠበቅ ሊባል አይችልም" ሲሉም አምባሳደር ቴዎድሮስ ተከራክረዋል።
በሌላ በኩል የአካባቢው የነዋሪዎች ማኅበር (Island Park Community Association) እና የቅርስ ጥበቃ ተሟጋቾች ሕንፃው እንዳይፈርስ አጥብቀው እየተቃወሙ ነው።
ማኅበሩ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ በታሪካዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ ለዓመታት ሲታገል የቆየ ሲሆን ይህ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሕንፃ ደግሞ የአካባቢው የታሪክ መገለጫና ዋነኛ ማሳያ መሆኑን ይገልጻሉ። የከተማው ምክር ቤት ባለፈው ሰኔ 10 ቀን ሕንፃው ጊዜያዊ የቅርስ ጥበቃ ከለላ እንዲያገኝ የወሰነ ቢሆንም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ግን በውሳኔው ላይ ይፋዊ ተቃውሞ አስገብቷል።
የአካባቢው የምክር ቤት አባል ጄፍ ሌይፐር ሕንፃውን ከኤምባሲው ባለሥልጣናት ጋር በቦታው ተገኝተው መጎብኘታቸውንና ሕንፃው በጣም አስከፊ ሁኔታ ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሌይፐር እንዳሉት የቅርስነት ስያሜው ሕንፃው ሙሉ በሙሉ እንዳይፈርስ በቀጥታ ባይከለክልም ከተማው አዲስ በሚገነባው ሕንፃ ላይ የቀድሞውን ታሪካዊ መልክና ውጫዊ ገጽታ አስገድዶ ለማስከበር እንደ ትልቅ ዲፕሎማሲያዊ መደራደሪያ መሣሪያ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ቤቱን የማፍረስ ማመልከቻው በከተማው ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።
| መሠረት ሚድያ |



