ለበርካታ አስርት አመታት መርካቶ 'መደብ' የሚባል ሱቅ ይዘው ሲሰሩ የነበሩ ነጋዴዎች ንብረታቸውን በአስቸኳይ ይዘው እንዲነሱ ተነገራቸው
(መሠረት ሚድያ)- ከደረሰኝ መቁረጥ/አለመቁረጥ ጋር በተያያዘ የገቢዎች ቢሮ እና እንደ መርካቶ ባሉ ገበያዎች የሚሰሩ ነጋዴዎች አልፎ አልፎ ውዝግብ ውስጥ ሲገቡ ይታያል፣ ይህ ውዝግብ አንዳንዴም ወደ ሱቅ መዝጋት አድማ ሲሸጋገር በቅርብ ወራት ታይቷል።
በተመሳሳይ ከሰሞኑ የገቢዎች ቢሮ በመርካቶ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር እያረገ ይገኛል።
መሠረት ሚድያ ከስፍራው የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው በተለይ ሸቀጦችን፣ እቃዎችን እና ምርቶችን ጭነው ወደተለያዩ ክፍለ ሀገራት የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች ላይ ከባድ ፍተሻ እየተደረገ ነው።
ይሁንና በርካታ በመርካቶ የሚካሄዱ ጉብኝቶች ደረሰኝ የሌላቸው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ 'መደብ' ተብለው የሚጠሩት እና ከመርካቶ ሱቆች ስር የሚሰሩ ነጋዴዎች ችግር ላይ እንዳሉ ለሚድያችን ጠቁመዋል።
"በአዳራሽ ዙሪያ ያለን 15 አመት በላይ የቆየን ነጋዴዎችን መነሳት አለባችሁ ተብለናል። ከባለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ተነሱ የሚል መረጃ ይዘው መጡ፣ የሚገርመው ይህ የሆነው ከሰሞኑ ግብር ከፍለን ከጨረስን በኋላ ነው" የሚሉት አንድ የመደብ ሱቅ ባለቤት ናቸው።
"በዛሬው እለት ደግሞ ስማችንን እየፃፉ ማስፈራሪያ ሲሰጡን ውለዋል። ቦታ ሳይዘጋጅ እንዲህ ማለት ተገቢ አይደለም፣ እቃዎቻችንን እያነሱ ውለዋል። ነገ አዲስ ሀይል ይመጣል የሚል ማስፈራሪያ ስጥተውን ሄደዋል" በማለት አክለዋል።
ሌላኛው የመርካቶ ነጋዴ ደግሞ "መርካቶ ለረጅም አመታት ስንሰራ የነበርን ነጋዴዎች ንግድ ፍቃድ ያለን እና ለመንግሥት ግብር ስንከፍል የቆየን ነን። እኛ በዚህ ስራ ስንት ቤተሰብ እንደምናስተዳደር አያውቁ ይሆን? ቦታ ሳይዘጋጅ ተነስ ማለት ምን ማለት ነው? ግብር ከፍለን ከጨረስን በኋላ አጠቃላይ መርካቶ መደብ ተነሱ የሚል ትዕዛዝ መጥቷል፣ ለምን" ብለው ጥያቄ ሰንዝረዋል።
የዛሬ አመት ገደማ በመርካቶ ገበያ የተጀመረው ሱቅ የመዝጋት አድማ መነጋገርያ ሆኖ ነበር። መንግሥት እያካሄደ በነበረው የደረሰኝ ቁጥጥርና ቅጣት ምክንያት ነጋዴዎች መደብሮቻቸውን በመዝጋት አድማ ላይ ነበሩ።
በወቅቱ ከአድማው በተጨማሪ ከመጋዘን እቃ የማሸሽ ተግባርም መኖሩን የገለፁት ነጋዴዎቹ በዚህም ምክንያት ገበያ መቀዛቀዙን ገልፀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ በበኩላቸው፣ “ቁጥጥሩ የተጀመረው በርካታ ሕገ ወጥ አሠራሮች ስላሉ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
-መሠረት ሚድያ-



