ሰራተኞቹ ላይ ድብደባ በመፈፀም እና ግቢ ውስጥ በማሰር ውንጀላ የቀረበበት ሱፐር ደብል ቲ ጄነራል ትሬዲንግ ጋዜጣዊ መግለጫ ጠራ
(መሠረት ሚድያ)- ባሳለፍነው ሳምንት ሚድያችን በምርመራ ዘገባው ያስነበበው በሱፐር ደብል ቲ ጄኔራል ትሬዲንግ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚፈፀመው የሰራተኞች መብት ጥሰት እና ወንጀል በርካቶችን አነጋግሯል።
ሮዳስ ቀለም እና ሱፑር ፋይበር በሚል ምርቶቹ የሚታወቀው ሱፐር ደብል ቲ ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግል ማህበር በሸገር ከተማ፣ አለም ገና ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ላይ ድብደባ፣ እስር፣ ማዋከብ፣ ደሞዝ መከልከል እና መቁረጥ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የሰብዓዊ ጥሰቶች እንደገፀመባቸው ቁጥራቸው በርከት ያሉ ሰራተኞች ለሚድያችን ተናግረዋል።
ይህ መረጃ መውጣቱን ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ እና የአሁን ሰራተኞች እንዲሁም ተቋሙን በቅርበት የሚያውቁ ግለሰቦች መሠረት ሚድያ ላይ የወጣው መረጃ እንደውም አንሶ መቅረቡን በመግለፅ ሌሎች ዝርዝር በደሎችን ማህበራዊ ሚድያ ላይ አጋርተዋል።
ይህን ተከትሎ ተቋሙ ለድርጅቱ ለሰራተኞቹ የደሞዝ እና ቦነስ ጭማሪ ከዚህ ሳምንት ጀምሮ እንደሚሰጥ ቃል መግባቱን ከውስጥ ምንጮቻችን ሰምተናል።
ባሳለፍነው ሳምንት በርካታ የስራ ቦታ ሁኔታዎች መሻሻላቸውን የገለፁት ሰራተኞች ይህም ድርጊቱ ሲፈፀም እንደነበር ለማድበስበስ የተደረገ መሆኑን ያስረዳሉ።
ሚድያችን አሁን የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው ደግሞ ሱፐር ደብል ቲ ጄነራል ትሬዲንግ በመጪው ቅዳሜ ጋዜጠኞችን አዲስ አበባ ከሚገኘው ማሪዮት ኢንተርናሽናል ሆቴል ሰብስቦ አለም ገና ወደሚገኘው ፋብሪካው በመውሰድ ለዚህ የተዘጋጁ ከ100 በላይ ሰራተኞችን እንዲያነጋግሩ ለማድረግ ማቀዱ ታውቋል።
በተቋሙ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ በዳዳ ደጋጋ የተፈረመና ለሚድያዎች እየተሰራጨ የሚገኝ ደብዳቤ እንደሚገልፀው ሱፐር ደብል ቲ ጄነራል ትሬዲንግ በበጎ አድራጎት እና ሀገራዊ ተልዕኮዎች ላይ እየተሰማራ ይገኛል። ፕሮግራሙ ላይ ለሚገኙ ጋዜጠኞች 'ጥሩ አበል' መዘጋጀቱን አንድ ምንጫችን ጠቁመዋል።
ደብዳቤው አክሎም "ተቋማችንን ለማፍረስ አንዳንድ የሶሻል ሚድያ ተጠቃሚዎች ከእኛ ጋር ሳይነጋገሩ ሰሞኑን ያልተገባ ስም የማጥፋት ዘመቻ እያካሄዱብን እንደሚገኙ ተመልክተናል" ይላል።
ይሁንና ድርጅቱ በሚድያዎች ላይ የገዘፈ ስም እንዳለው የሚጠቅሱት የድርጅቱ ሰራተኞች ለእነሱ ግን 'ሲኦል' እንደሆነባቸው በስፋት አንስተዋል።
በተለይ የድርጅቱ ባለቤት የፈለጉትን ሰው ግቢው ውስጥ ባለ አንድ ክፍል ውስጥ እንደሚያሳስሩ፣ ያሻቸውን ደግሞ ሸገር ከተማ በሚገኙ የፀጥታ አካላት እንደሚያስወስዱ፣ ሌሎች ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ድብደባ እንደተፈፀመባቸው እና አካለ ጎዶሎ የሆኑ ጭምር እንዳሉ ያስረዳሉ።
ሌሎች ሰራተኞች ለሚድያችን ያነሷቸው ነጥቦች:
- ህገወጥ በሆነ መልኩ ስራ በግዴታ ከጠዋት 12 ሰአት እስከ ምሽቱ 12 ሰአት፣ አንዳንዴም እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ካለ ተጨማሪ ክፍያ እንደሚሰሩ
-የንግድ ህግ ጥሰት በሚል ሽፋን የድርጅቱ የንግድ ተወዳዳሪ የሆኑ እና ፋይበር ግላስ የሚያመርቱ ሰዎች አሁን ድረስ ታስረው እንደሚገኙ
- ደሞዝ ከፍ ተደርጎ ሰው እንደሚቀጠር፣ ይሁንና በበርካታ ቅጣቶች እስከ አንድ አራተኛ የሚሆነው ተቆራርጦ የሚወስድ ሰራተኛ ብዙ መሆኑ፣ ካለ ቅጣት ደሞዝ የማይወስድ እንደሌለ
- ሰራተኞች በቅጥር ወቅት የስራ ውል እንደማይሰጣቸው፣ ሲለቁም ምንም አይነት የስራ ልምድ ደብዳቤ እንደማያገኙ
- ከስራ አንድ ደቂቃ ያረፈደ 700 ብር፣ ማስቲካ ያኘከ 1 ሺህ ብር እንደሚቀጣ
- ስራ መልቀቅ እፈልጋለሁ ያለ ሊደበደብ ወይ ሊታሰር እንደሚችል፣ በተለይ ልምድ ያላቸው ሰራተኞች መልቀቅ ማለት ድብደባ፣ እስር ወይም ብር ሰርቋል የሚል ክስ እንደሚቀርብባቸው
- በርካታ ቁጥር ያላቸው የቀድሞ ሰራተኞች በድርጅቱ ጠቋሚነት ኦሮሚያ ክልል ዳለቲ ከተማ እንደታሰሩ፣ አሁንም ታስረው እንደሚገኙ
- ለሰራተኞች ዋስ የሆኑ በርካታ ግለሰቦች ዋስ ማንሳት እንዳልቻሉ፣ ይህን ሲጠይቁ ከድርጅቱ ቅጥር ግቢ አካባቢ በፀጥታ አካላት እንደሚባረሩ
- ከዚህም በተጨማሪ ድርጅቱ በራሱ ስም አንድም ሰራተኛ እንደማይቀጥር፣ ማስታወቂያ ሲያስነገር ራሱን የቻይና ድርጅት አርጎ እንደሚያስተዋውቅ፣ ይህንንም ከግብር ጋር በተገናኘ እንደሆነ ምርመራ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
ሚድያችን በዚህ ዙርያ የድርጅቱን መግለጫ ተከትሎ ያሰባሰባቸውን መረጃዎች ለአንባቢዎች ያቀርባል።
-መሠረት ሚድያ-





