ከፊል የስራ ማቆም አድማውን ተከትሎ የታሰሩ የጤና ባለሞያዎች ብዛት 78 መድረሱ ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ዛሬ አራተኛ ቀኑን የያዘውን የጤና ባለሞያዎች ከፊል የስራ ማቆም አድማን ተከትሎ የታሰሩ ባለሞያዎች ብዛት 78 መድረሱ እንዲሁም በባለሞያዎቹ ላይ እየደረሰ ያለው እስር እና እንግልት ተጠናክሮ መቀጠሉን ታውቋል።
መሠረት ሚድያ ዛሬ በደረሰው መረጃ በተለይም ትላንት ለሊት በጎንደር ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል የጸጥታ ሃይሎች ወደሃኪሞች መኖሪያ በመግባት የህጻናትና የካንሰር ስፔሻሊስትን ጨምሮ 25 ሬዝደንትና ስፔሻሊስት ሃኪሞችን አፍነው መውሰዳቸው ታውቋል፣ እስካሁንም የደረሱበት አልታወቀም።
ይህንና ተመሳሳይ አፈናና እንግልትን ተከትሎ የኢትዮጵያ ጤና ባለሞያዎች ንቅናቄ አባላት ሙሉ ለሙሉ ስራ ለማቆም በመወሰናቸው አሁን ላይ በህክምና ላይ ያሉ ታካሚዎች በማይንገላቱበት መንገድ እስከ ነገ ቅዳሜ ድረስ ሙሉ ለሙሉ ስራ የማቆም አድማውን ተፈጻሚ የሚያረግ ፕሮግራም አውጥተው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ታውቋል።
ሆኖም እስካሁን አፈናና እንግልት በደረሰባቸው እንደ ጥቁር አንበሳና ዘውዲቱ የመሳሰሉ ሆስፒታሎች ውስጥ የሚሰሩ ባለሞያዎች ሙሉ ለሙሉ ሰራ ማቆማቸው ተሰምቷል።
በተመሳሳይ በሃዋሳ ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል በአስተዳደር ሃኪሞች ወደስራ ገበታቸው ካልተመለሱ ግቢውን ለቀው እንዲወጡ የተሰጠውን ማስታወቂያ ተከትሎ የሆስፒታሉ ሬዝደንትና ኢንተርን ሃኪሞች ከግቢው የተቀበሉትን ንብረት በማስረከብ ለቀው እየወጡ መሆናቸውን የደረሰን መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ ጤና ባለሞያዎች በዚህ ንቅናቄ ጊዜውን ያማከለ እና ለመኖር የሚያስችል የደመወዝ ጭማሪ፣ የሪስከና የመሳሰሉት ከፍያዎች መፈጸም፣ የትራንስፖርት እገዛ፣ ጊዜውን የጠበቀ እና ያልተቆራረጠ የduty ክፍያ፣ ባለሞያውን ለአደጋና እንግልት የማያጋልጥ የስራ ቦታ፣ የጤና መድህን፣ የመኖሪያ ቤት ወይም ቦታ እንዲሁም ለትምህርት የሚመችና በደንብ የተደራጀ የመማሪያ ስፍራ እና በአጠቃላይ 12 የሆኑ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱላቸው እየጠየቁ ይገኛሉ።
የጤና ሚኒስቴር በበኩሉ ትናንት ባወጣው መግለጫ ከሰሞኑ የስራ ገበታቸው ላይ ያልተገኙ የጤና ባለመያዎች 'በሐሰተኛ መረጃ የተወናበዱ' እና 'ጥፋትን ዓላማቸው ያደረጉ' ናቸው ማለቱ ይታዋሳል።
መረጃን ከመሠረት!



