አማራ ባንክ ያፀደቀው አዲሱ የሰራተኞች የደመወዝ ጭማሪ አተገባበር ተቃውሞ ገጠመው
(መሠረት ሚድያ)- ሚድያችን ከዚህ በፊት ለአንባቢዎቹ ያቀረበው ተከታታይ መረጃ እንደሚጠቁመው በአማራ ባንክ ውስጥ ያሉ ሰራተኞች የደሞዝ እርከን ጭማሪ ሲጠይቁ ቆይተዋል።
በቅርብ አመታት ወደ ስራ ከገቡ ባንኮች አንዱ የሆነው አማራ ባንክ ከሰራተኞቹ ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ እንደቆየ የተለያዩ ጥቆማዎች ያሳያሉ፣ በርካታ የባንኩ ሰራተኞችም ለመሠረት ሚድያ እየላኩት የነበረው መረጃ ይህንኑ ያሳያል።
ጉዳዩ በዋነኝነት 'ቃል የተገባልን የደመወዝ ጭማሪ አልተፈፀመልንም' የሚል ሲሆን ከዚህ ጋር ተያይዞም ሰራተኞቹ በባንኩ አመራሮች ላይ ቅሬታቸውን እያሰሙ ቆይተዋል።
"እኛ የአማራ ባንክ ሰራተኞች ባንኩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ በደስታና በከፍተኛ ፍላጎት ባንኩን ተቀላቅለን እየሰራን እንገኛለን። አብዛኛው ሰራተኛ ከሌሎች ባንኮች ደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅሞችን በመቀነስ እንዲሁም የተሻለ የስራ ቦታ ትቶ የመጣ ነው" የሚሉት አንዱ የባንኩ ሰራተኛ ናቸው።
ሌላ የባንኩ ሰራተኛ ደግሞ "ከሞቀ ቤታችን ለምሳሌ ከንግድ ባንክ፣ ከአቢሲኒያ ባንክ፣ ከአዋሽ ባንክ እና ከተለያዩ ግዙፍ ባንኮች ወጥተን አማራ ባንክ የገባን ሲኒየር የባንክ ሰራተኞች ይሄው ፍዳችንን እየበላን ነው" በማለት ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።
ሚድያችን አሁን የደረሰው መረጃ እንደሚያሳየው አማራ ባንክ ከየካቲት 22/2018 ዓ.ም ጀምሮ አዲስ የደሞዝ ማስተካከያ አድርጓል።
ይሁንና ጭማሪው ከላይ ላሉት (Chiefs, Directors, Managers) ከፍ ብሎ በጣም ብዙ ወደታች እየወረደ ሲመጣ ደግሞ ያሽቆለቆለ ነው የሚል ትችት ቀርቦበታል።
"እሱም ሆኖ ሰራተኛው በደስታ ተቀብሎታል፣ የኢንዱስትሪው አቬሬጅ ደሞዝ ነው በሚል። ይሁን እንጂ አሁንም የሰራተኛ የአደጋ ጊዜ የደመወዝ ብድር (Employee Salary Advance) ዘግቷል። ባንኩ ለሰራተኞች ጥቅማ ጥቅም ብሎ ከያዛቸው ብድሮች አንዱ የሆነው ይሄ የብድር አይነት አማራ ባንክ ላይ ከቆመ ከሁለት አመት በላይ የሆነው ሲሆን አንድም ሌላ ባንክ ይሄንን ብድር የከለከለ የለም" የሚሉት አንድ የባንኩ ሰራተኛ ናቸው።
አክለውም "አማራ ባንክ ውስጥም ቢሆን ቺፎች፣ ዳይሬክተሮች፣ እንዲሁም የዲቪዝን ማናጀሮች ከክልከላው በኋላ የተቀጠሩ ቢሆንም ለእነሱ ያለምንም ክልከላ እየተሰጣቸው የሚገኝ ሲሆን ከታች ያለው ሰራተኝ ግን ከተከለከለ ሁለት አመት አልፏል" በማለት አስረድተዋል።
ሌላ የባንኩ ሰራተኛ ደግሞ "ዋና ስራ አስፈፃሚው እና ከፍተኛ አመራሮች የቤትና የመኪና ብድር ከወለድ ነጻ ይወስዳሉ። ባንኩ ከተመሰረተ ጀምሮ ለሰራተኞች የሚሰጠው የቤትና የመኪና ብድር ለስራ አስፈጻሚው እና ለአመራሮቹ ብድሩን የሚሰጠው ባንኩ ኪሳራ ውስጥ ገብቶ ነው፣ ይህም በዜሮ ፐርሰንት ወለድ ማለት ነው። አንድም ባንክ ኢትዮጵያ ውስት እንደዚህ የሚያደርግ የለም፣ በትንሹ ሰባት ፐርሰንት ወለድ ያስከፍላል" በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።
በዚህም አሰራር መሰረት ለምሳሌ አንድ የባንኩ ዳይሬክተር በ8 ሚሊዮን ብር መኪና ቢገዛ የሚከፍለው 8 ሚሊዮን ብሩን ብቻ ነው፣ ባንኩ ግን በየወሩ ለደንበኛው የ8 ሚሊዮኑን ዝቅተኛ ወለድ 7 ፐርሰንት ለደንበኛው ወለድ ይከፍላል።
ከዚህም በተጨማሪ ደሞዝ ከተጨመረ በኋላ ሰራተኞች ላይ ጫና መብዛቱን ሰራተኞቹ የላኳቸው ተደጋጋሚ ጥቆማዎች ያሳያሉ።
"ሰራተኛው ሞያው ባልሆነው እና በማይመለከተው ዲፖዚት ማሰባሰብ በሚል የባንኩ ስትራቴጂ ነው በሚል ሁሉንም ሰራተኛ አስር አስር ሰው አካውንት እንዲያስከፍት እንዲሁም አንድ ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ አለባችሁ በሚል እያስገደደን ይገኛል" በማለት ይከሳሉ።
የታችኛውን ሰራተኛን ያገለለ፣ በተቃራኒው ደግሞ ለላይኛዉ አመራር 90 ፐርሰንት እና ከዚያ በላይ ደሞዝ በመጨመር ተሰርቷል የተባለውን ማስተካከያ ሰራተኞቹ እየተቃወሙት ይገኛሉ።
የታችኛው ወለል ላይ ያሉ ሰራተኞች የደመወዝ ድልድሉ ፍትሃዊነት የጎደለው ነው በማለት አቤቱታ ወደ ዋናው መስሪያ ቤት ለማቅረብ በሚሄዱበት ወቅት ዛቻና ማስፈራሪያ እየደረሰብን ይገኛል በማለት ይናገራሉ።
ባንኩ ለሁሉም ሰራተኞች መጋቢት 4/2018 ዓ.ም ይፋ ባደረገው አንድ የውስጥ ማስታወሻ አንዳንድ የባንኩ ሰራተኞች በግል እና በቡድን በመሆን አቤቱታ ለባንኩ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ አስታውቋል፣ ይህ ደግሞ 'አላስፈላጊ' የስራ ግዜ መባከን እንዳስከተለ ይጠቅሳል።
በተቀዳሚ ስራ አስፈፃሞው የተፃፈው ደብዳቤው አክሎም "ይህ የውስጥ ማስታወሻ ከተፃፈበት ቀን ጀምሮ በግልም ይሁን በቡድን የሚቀርቡ አቤቱታዎች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው እያሳሰብኩ ይህንን መመርያ በማተላለፍ አቤቱታ በሚያቀርብ ማንኛውም ሰራተኛ ላይ ባንኩ አስተዳደራዊ እርምጃ የሚወስድ መሆኑን አሳውቃለሁ" ብሏል።
-መሠረት ሚድያ-



