#አስተያየት 'ተከበናል፣ ድምፃችንን አሰሙልን'
ከከተማው ነዋሪ ለመሠረት ሚድያ
(መሠረት ሚድያ)- እንደሚታወቀው የደብረ ማርቆስ ከተማ ኤርፖርት ግንባታው የተጀመረው ከአመታት በፊት የነበረ ቢሆንም ከዛ በኋላ ግንባታቸው የተጀመሩ ኤርፖርቶች ሲጠናቀቁ የከተማችን ኤርፖርት ግን ሜዳ ላይ ቀርቷል።
ግንባታው እየተጓተተም የቀጠለ ቢሆንም አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል። የተቋረጠበት ምክንያት ደግሞ በአማራ ክልል እየተካሄደ በሚገኘው ጦርነት ምክንያት ነው።
ከዚህ በፊት ሁለቱም ተፋላሚ ሀይሎች ፈቅደው ግንባታው ሲካሔድ ቆይቷል።
አሁን ግን መንግስት ክልሉን ተቆጣጥሪያለሁ ብሎ አውጆ ደብረ ማርቆስ በተለያዩ የፌደራልና የክልሉ ወታደሮች የተጨናነቀች ቢሆንም የአካባቢው ፋኖ ግንባታው እንዲቆም ማዘዙን ተከትሎ ግንባታውን ሲያካሂድ የነበሩ ሰራተኞች አካባቢውን ለቀው ወጥተዋል።
ያ ሁሉ በከተማዋ የሚገኝ የፀጥታ አካል ቦታውን ተቆጣጥሮ ግንባታውን ማስቀጠል አልቻለም። ይሔ ሁሉ የሚሆነው ከከተማው በ5 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ነው።
ግንባታውን ያስቀጥላል የተባለው የከተማ አስተዳደርም ስራውን ከማስቀጠል ይልቅ ግንባታ ያቋረጠውን ፋኖን አወግዛለሁ እያለ ከመለመን ያለፈ አቅም እንደሌለው ታይቷል።
በዚህም የደብረማርቆስ ህዝብን ጨምሮ የፍኖተሰላም፣ የዳንግላ፣ የደምበጫ፣ የቡሬ፣ የአማኑኤል፣ የሞጣ፣ የግንደወይን፣ የአምበር፣ የሉማሜና ደጀን ህዝብ ወደ አዲስ አበባ ለመሔድ ከእገታ ይታደገኛል ብሎ ሲጠብቀው የነበረው ፕሮጀክት የውሀ ሽታ ሆኖበት ቀርቷል።
ከሰሞኑም በኦሮሚያ ክልል መንገዶች ላይ የሚፈፀመው እገታ መጨመሩን ተከትሎ ከአዲስአበባ- ጎጃም የህዝብ ትራንስፖርት ሙሉ ለሙሉ ተቋርጧል።
ባህር ዳር ሔዶ ወደ አዲስ አበባ በፕሌን ለመሔድም ጦርነቱን ተከትሎ መንገዱ በታጣቂዎች በመያዙ ይሔ ህዝብ ወደ ባህር ዳርም ወደ አዲስ አበባም እንዳይንቀሳቀስ ተከቧል፣ ታፍኗል።
በመሆኑም በግራም በቀኝም እየታገተ በሚሊዮኖች የሚዘረፈው ህዝብ አስቸኳይ መፍትሔ ይፈልጋል። ወይ ፋኖ ግንባታውን ፈቅዶ ያስቀጥልልን ወይ መንግስት ቦታውን በደንብ ተቆጣጥሮ ግንባታውን ያጠናቅቅ።
በሁለቱ ዝሆኖች ፍልሚያ ምክንያት በጦርነቱ ካለቀው ህዝብ ባልተናነሰ ህክምና በማጣት በየቤቱ የሚያልቀውና ለስራ ፍለጋ መንቀሳቀስ ባለመቻሉ የተከከበበው ህዝብ ጨምሯል።
መልዕክታችንን እንደምታደርሱልን ባለ ሙሉ ተስፋ ነን። እናመሠግናለን!
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
-መሠረት ሚድያ-



