በዝዋይ ማረሚያ ቤት የሚገኙ ታራሚዎች በቂ ምግብ እየቀረበላቸው ባለመሆኑ ለርሀብ እና ለበሽታ እየተጋለጡ መሆኑ ተሰማ
(መሠረት ሚድያ)- በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የዝዋይ ማረሚያ ቤት ማዕከል ለታራሚዎቹ በቂ ምግብ እያቀረበ አይደለም ሲሉ የታራሚ ቤተሰቦች ለመሠረት ሚዲያ ገለፁ።
ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የታራሚ ቤተሰቦች እንደሚሉት ማረሚያ ቤቱ ለታራሚዎቹ ምሳ እና እራት እያቀረበ ያለው የበቆሎ ቂጣ በመሆኑ ታራሚዎቹ በምግብ እጥረት ምክንያት ለበሽታ እየተጋለጡ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የገንዘብ አቅም ያላቸው የሕግ ታራሚዎች ከዝዋይ ከተማ ምግብ እንዲመጣላቸው ቢጠይቁም መከልከላቸውንም አክለው ገልፀዋል።
ቤተሰቦቻቸው ጨምምረው እንደተናገሩት ይህ የበቆሎ ቂጣም ቢሆን በወቅቱ ባለመድረሱ ታራሚዎች በየቀኑ ለርሀብ እየተጋለጡ መሆኑን ጠቁመዋል።
አንድ ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉ የዝዋይ ማረሚያ ቤት አስተዳደር ሰራተኛ እንደገለፁት "ማረሚያ ቤቱ በቂ በጀት ስላልተመደበለት የበቆሎ ቂጣ ለማቅረብ ተገዷል፣ የሚችለውም ይህንን ነው" ሲሉ ለሚድያችን ተናግረዋል።
የአስተዳደሩ ባልደረባ አክለውም "የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ለአንድ ሺህ ታራሚ አንድ ኪሎ ሽንኩርት፣ አንድ ሊትር ዘይት እና አምስት ኪሎ ሽሮ በሚል ሒሳብ ነው በጀት የተመደበልን" ሲሉ ገልፀዋል።
"በየጊዜው እየታየ ባለው የምግብ ዋጋ ሸቀጦች መናር ምክንያት ማረሚያ ቤቱ ከተመደበለት በጀት አንፃር ለታራሚዎች ምግብ ወደ የማያቀርብበት ደረጃ ደርሷል" ሲሉ ነው የተናገሩት።
በማረሚያ ማዕከሉ ውስጥ ከአራት ሺህ በላይ ታራሚዎች ሲኖሩ በምግብ እጥረት ምክንያት ውጥረት መንገሱንም ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል።
መረጃን ከመሠረት!




