የሰብል ኬሚካል እንዲረጩ በመንግስት የተገዙ አነስተኛ አውሮፕላኖችን ለማስተዳደር ከአንድ የግል ድርጅት ጋር የተፈፀመው አነጋጋሪው የ7.1 ሚሊዮን ዶላር ውል
(መሠረት ሚድያ)- በግንቦት ወር 2016 ዓ.ም ለህዝብ ይፋ ከተደረጉ መረጃዎች አንዱ በግብርና ሚኒስቴር አማካኝነት በ850 ሚሊዮን ብር የተገዙ አምስት ዘመናዊ የርጭት አውሮፕላኖች ስራ መጀመራቸው ነበር።
ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝና ሌሎች አደጋዎችን ለመቆጣጠር የራሷ የኬሚካል ርጭት አውሮፕላኖች ስላልነበራት ለኪራይ እስከ 13 ቢሊየን ብር ወጪ ስታደርግ እንደነበር የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያመለክታሉ፣ በዚህም ምክንያት የነዚህ አውሮፕላን ግዢ ከፍተኛ ተስፋን ፈንጥቋል።
እነዚህ 'ኤር ትራክተር' የሚባሉ አውሮፕላኖች የአንበጣ ወረርሽኝን ከመከላከል በዘለለ የደን ቃጠሎና የግሪሳ ወፍን መቆጣጠር የሚያስችል እንዲሁም የኬሚካል ርጭት እና ቅኝት ማድረግ የሚያስችሉ ናቸው።
አውሮፕላኖቹ ከኢትዮጵያ ባለፈም ለጎረቤት ሀገርና ለሌሎችም ጥቅም መስጠት የሚችሉ ናቸው። በዚህ ወቅት ይፋ እንደተደረገው ሀገር በቀሉ ናሽናል ኤርዌይስ አምስቱን ኤር ትራክተር የማስተዳደር ስራውን በጨረታ ተረክቧል።
ይሁንና መሠረት ሚድያ ያደረገው የምርመራ ዘገባ እንደሚያሳየው የግብርና ሚኒስቴር ከናሽናል ኤርዌይስ ጋር ያሰረው ውል ብዙ ጥያቆዎችን የሚያስነሳ ነው።
ጉዳዩ እንዲህ ነው፣
ከዛሬ አምስት ዓመት ወዲህ እየተከሰቱ ያሉ የአንበጣ መንጋ ወረራዎች በሰብል ላይ ከፍተኛ ውድመት በማስከተላቸው የግብርና ሚኒስቴር አሚባራ ኤርዌይስ እና ዘመን ኤዌይስ የሚባሉ ሁለት የግል ተቋማት የኬሚካል ርጭት የኮንትራት ስራ ወስደው እንዲሰሩ ጥያቄ አቀረበላቸው።
ይሁንና የሰብል ውድመቱ መጠን ትልቅ በመሆኑ ተጨማሪ አውሮፕላኖች እንደሚያስፈልጉ ተወሰነ፣ ይሁንና ሂደቱ ብዙ ጥያቄ ያስነሳ ሆኗል፣ ይህም መንግስት ከፍተኛ ገንዘብ እንዲያጣ ምክንያት ሆኗል።
መንግስት በወቅቱ ስሌት 850 ሚልዮን ብር ወይም 11 ሚልዮን ዶላር ከራሱ ካዝና ማውጣት አምስቱን አውሮፕላኖቹን ከገዛ በኋላ አውሮፕላኖቹን ለማስተዳደር ጨረታ አውጥቶ ነበር። የጨረታ ግዜውም አምስት ዓመት የሚቆይ እና በየአመቱ የሚከፈል እንደሆነ መሠረት ሚድያ የተመለከተው የጨረታ ሰነድ ያሳያል።
"ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ለተመረጡ ሁለት የግል ድርጅቶች፣ ማለትም ለዘመን ኤርዌይስ እና ለናሽናል ኤርዌይስ፣ ተሳተፉ የሚል ጥያቄ ቀረበላቸው። ቢያንስ ዘመን ኤርዌይስ ከዚህ በፊት ርጭት ያከናውን ነበር፣ ናሽናል ኤርዌይስ ግን በምን መስፈርት እንደተመረጠ ግልፅ አይደለም" የሚሉት አንድ የግብርና ሚኒስቴር ውስጥ አዋቂ ምንጭ ናቸው። አሚባራ ኤርዌይስ ጭራሽ አለመመረጡንም ያነሳሉ።
ተጨማሪ የተመለከትናቸው ዶክመንቶች እንደሚያሳዩት በመጨረሻ የተመረጠው ናሽናል ኤርዌይስ ነበር፣ ለአገልግሎቱ ደግሞ በአመት 1,958,400 ዶላር (አንድ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ሀምሳ ስምንት ሺህ አራት መቶ ዶላር) እንዲከፈለው ስምምነቱ ያስቀምጣል።
ይሁንና ዋናው ጥያቄ የተነሳው እዚህ ጋር መሆኑን ሌላ የግብርና ሚኒስቴር ምንጭ ያስረዳሉ።
"ናሽናል ኤርዌይስ በኬሚካል ርጭት ልምድ ባይኖረውም ተመረጠ፣ ከዚህ በበለጠ የሚገርመው ግን አንደኛው አመት ከተጠናቀቀ በኋላ ውሉን ለማስረዘም በታሰረ ሌላ ውል በአመት ለድርጅቱ የሚከፈለው የገንዘብ መጠን በአመት 7,126,897 ዶላር (ሰባት ሚሊዮን አንድ መቶ ሀያ ስድስት ሺህ ስምንት መቶ ዘጠና ሰባት ዶላር) መሆኑ ነው" የሚሉት ባለሙያው ይህ የግብርና ሚኒስቴር ሰራተኞች በሙሉ ማስገረሙን ያነሳሉ።
"ለጭማሪው ምክንያት ሆኖ የቀረበው የዋጋ ግሽበት ነው። ይህ የውል ማስረዘሚያ ውል ሲታሰር ማለትም የዛሬ ሶስት አመት ማለት ነው የማክሮ ኢኮኖሚው ማሻሻያ አልተደረገም ነበር። በምን መልኩ የ360 ፐርሰንት ጭማሪ ተደረገ? ይህ እስካሁን ያልተፈታ ጉዳይ ነው" ብለዋል።
በዚህ ምክንያት መንግስት አሁን ላይ ባለው የውጭ ምንዛሬ ስሌት የገዛቸውን አውሮፕላን ለሚያስተዳድርለት የግል ተቋም በአመት ከአንድ ቢልዮን ብር በላይ እየከፈለ መሆኑ ታውቋል። ከዚህ ወጪ በተጨማሪ መንግስት በየአመቱ ለአውሮፕላኖቹ ኢንሹራንስ እና መለዋወጫ ግዢ ከ200 ሚልዮን ብር በላይ እንደሚያወጣ ታውቋል፣ ይህም አመታዊ ወጪውን ከ1.2 ቢልዮን ብር በላይ ያደርገዋል።
ታድያ ይህ ሁሉ ገንዘብ ተከፍሎስ ምን ስራ?
"በመጀመሪያዎቹ ሶስት አመታት ማኔጅመንቱን የተረከበው ድርጅት አንዳንድ ጥገናዎችን አከናውኗል። አብዛኛውን ግዜ ግን አውሮፕላኖቹ ቦሌ ኤርፖርት ውስጥ ቆመው ይገኛሉ። በቅርቡ አንዳንድ የርጭት አገልግሎት በመስጠት ገቢ ለማግኘት ሙከራዎች አሉ፣ ይህም ግን የሰብል ወቅት ሲደርስ ብቻ የሚሰራ ነው" የሚሉት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች መንግስት ጉዳዩን በድጋሜ እንዲያጤናው ጠይቀዋል።
"እንዴት መንግስት ራሱ ለገዛቸው አውሮፕላኖች በአመት ከአንድ ቢልዮን ብር ይከፍላል? ይህ እንደ አንድ ዜጋ ያሳስበናል" ብለዋል።
መሠረት ሚድያ በዚህ ዙርያ የግብርና ሚኒስቴርን የግዢ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የውል ሰነዶቹ ላይ የፈረሙትን አቶ ደጋየሁ ደሶን ለማናገር ሙከራ አድርጎ ነበር።
አቶ ደጋየሁ መረጃ እንደሚሰጡ ካሳወቁን በኋላ ሀሳባቸውን በመቀየር፣ "እረፍት ላይ ነኝ" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
-መሠረት ሚድያ-







Selam Meseret: ጥቆማ መስጫ መንገድ ስላላገኘሁ: ምልከታዬን በዚህ አስተያየት መስጫ አስምጨዋለሁ::
በቅርቡ እንደሰማነው የ12ኛ ክፍል(ዩኒቨርሲቲ መግቢያ) ፈተና ውጤት ተለቆ አጠቃላይ ስታቲስቲክስ በሚንስትሩ ተገልጿል:: ሆኖም በተከታዩ ቀን እንደተስተዋለው በሁለተኛው ዙር የተፈተኑ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የፊዚክስ ውጤታቸው ወደ 100 ሳይቀየር ጥሬ ውጤቱ ይፋ በመደረጉ የአብዛኛዎቹ ተማሪዎች ውጤት ስህተት ነበረ ድምር ውጤቱም ስሌቱ ትክክል አልነበረም:: ይህንንም ስህተት በመረዳት በ 3ኛው ቀን የነዚህ ተማሪዎች ውጤት Update ተደርጎ ትክክለኛ ውጤታቸው ከ 100 ተለቋል::
3 ጥያቄዎች
1. ይህን ያክል ረጅም ጊዜ የወሰደ እርማት ለምን Accurate መሆን አልቻለም!? የተቋሙን Precision ጥያቄ ውስጥ ያስገባል!
2. የህን የሚያክል ትልቅ ስህተት ሰርተው ለምን ይቅርታ አይጠይቁም ?
3. በዚህ መሰረት ብርሀኑ ነጋ የሰጠው Statistics በሙሉ አሁን Invalid መሆኑን ልብ በልልኝ!!
ከ 50% በላይ ያመጡ ተማሪዎች ብዛት , የወደቁ ብዛት ሁሉም አሁን መከለስ አለበት ምክኒያቱም ከመግለጫው በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ውጤቶች (Physics Subject) Update ተደርገዋል!! ይሄን የሚያክል ትልቅ መረጃን ችላ ማለት የመንግስትን ንቀት/ሀላፊነት አለመሰማት ያሳያል::
ይህ መልእክት ከደረሰህና ካነበብከው የፃፍኩበት ቦታ Irrelevant ስለሆነ Delete እንድታደርገው I give my consent.
መንግሥት ለአንድ ብሔር እያደረገ ያለው የኢኮሜዊ ግንባታ እንደ ሀገር ክህደት ወይም ሌላውን ያገለለ የጎጠኝነት ማሳያውን በግልፅ ያረጋገጠ ነው። መንግስት ከኦሮሚያ ውጭ ሌላውን እያለማና ለሌሎች ክልሎች እኩል የልማት ጠጠቃሚ እንዳይሆኑ እያደረገ እንደሆነ የተረጋገጠ ነው።