በማርበርግ ቫይረስ ምክንያት በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል አንድ ሰው ህይወቱ ሲያልፍ በአዲስ አበባ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ደግሞ ምልክቱ የታየባቸው ሰዎች ለይቶ ማቆያ መግባታቸው ታወቀ
(መሠረት ሚድያ)- ባሳለፍነው ሳምንት በጂንካ ከተማ እንደተገኘ ይፋ የሆነው የማርበርግ ቫይረስ ስርጭቱ እየሰፋ መጥቶ እንደ ሀዋሳ እና አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ምልክቶች መታየት መጀመራቸውን ሚድያችን ከጤና ባለሙያዎች ሰምቷል።
ከጂንካ ከተማ ሪፈር ተብለው ወደ ሀዋሳ ሪፈራል ገብተው ከነበሩ ሶስት ሰዎች መሀል የአንዱ ህይወት እንዳለፈ ሚድያችን ያረጋገጠ ሲሆን ሁለቱ ደግሞ በከፍተኛ ክትትል ክፍል (ICU) ውስጥ እንደሚገኙ ታውቋል።
ከስር የምትመለከቱት ምስል በሀዋሳ ሪፈራል ሆስፒታል ያሳለፍነው እሁድ የነበረውን ሁኔታ ያሳያል።
አንድ የሆስፒታሉ ባልደረባ "ታማሚዎቹ ከበርካታ ሰዎች ጋር ንክኪ ነበራቸው፣ ይህም ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጥሯል" በማለት ተናግሮ ሁሉም የጤና ባለሙያ መረጃውን እንዳያወጣ ማስፈራርያ እየደረሰው መሆኑን ጠቁሟል።
በሌላ በኩል ትናንት ምሽት ለዛሬ አጥቢያ የማርበርግ ቫይረስ ምልክት የሆኑትን በአፍንጫ እና አፍ ደም መፍሰስ ምልክቶችን ያሳዩ ታማሚዎች ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል መግባታቸውን የሆስፒታሉ ምንጮቻችን ነግረውናል።
"አንዳንድ ምልክቱ ያለባቸው ሰዎች ትናንት ምሽት ገብተዋል። ለብቻቸው ተለይተው የተቀመጡ ሲሆን በቀጣይ ቀናት በሚደረግ ምርመራ ምንነቱ ይረጋገጣል። በአፍ እና አፍንጫ ደም መውጣት ምልክቶችን አሳይተው ነበር" ብለው ምንጫችን ለመሠረት ሚድያ ተናግረዋል።
ይሁንና በአዲስ አበባ እስካሁን ያለፈ የሰው ህይወት እንደሌለ ጠቁመዋል።
በአርሲ ዞን አሰኮ ወረዳ ሁሉቆ ቀበሌ ላይ በማርበርግ ቫይረስ በሽታ እንደተጠቁ የተጠረጠሩ 13 ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን ሚድያችን ትናንት መዘገቡ ይታወሳል።
"የአካባቢው አመራሮች መረጃውን ካወጣችሁ ተጠያዊ ትሆናላችሁ ብሎ ፀጥ አስብሎናል። አሁን ላይ በአካባቢው የመንግስት ወታደሮች ተሰማርተው ማንም እንዳይወጣ ተከልክሏል" ያሉት የአካባቢው የጤና ባለሙያች በተለይ መረጃ ለህዝብ ግልፅ እንዳይሆን እየተጣለ ያለ እቀባ እና ማስፈራርያ ጉዳቱ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል እያሳሰቡ ይገኛሉ።
የጤና ሚኒስቴር እስካሁን 26 የላቦራቶሪ ምርመራ አድርጎ አራት ሰዎች ላይ ብቻ ቫይረሱ እንደተገኘ አስታውቋል፣ በቫይረሱ ህይወታቸው ያለፉ ሰዎችን ደግሞ ሶስት ብቻ እንደሆኑ በማህበራዊ ትስስር ገፁ አስቀምጧል።
-መሠረት ሚድያ-






ይሄ ፓርቲማ መረጃ ዝግ አድርጎ
አፍኖ ሊገለን ነበር ይሄ አፋኝ
የማፍያ ግሩፕ
ከበሽታው የሚድን የለም?