የሆርሙዝ ቀውስ እና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ፈተና፡ ከውጫዊ ተጽንኦች ባሻገር ጽናትን የመገንባት ጥበብ
(መሠረት ሚድያ)- ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ የጂኦ-ፖለቲካ ማዕበል እና በአገር ውስጥ መዋቅራዊ ድክመቶች ምክኒያት መስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች። በአገሪቱ የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ ላይ የተመዘገቡ ተስፋ ሰጪ ስኬቶች ከቁጥጥር ውጭ በሆኑ ውጫዊ ክስተቶች ሳቢያ ብርቱ ፈተና ተደቅኖባቸዋል።
በየማደያዎቹ የሚታዩት ረጅም ሰልፎች፣ የማዳበሪያ አቅርቦት መዘግየት እና የትራንስፖርት ወጪ መናር የችግሩን ጥልቀት ማሳያ ህያው ምስክሮች ናቸው።
የዚህ ቀውስ ማዕከል ከድንበራችን ሺህ ኪሎ ሜትሮች ርቆ የሚገኘው የሆርሙዝ ወሽመጥ ነው። በኢራንና በዙሪያዋ የተቀሰቀሰው ግጭት፣ የአለምን አምስተኛ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ንግድ የሚያስተናግደውን ይህንን ስልታዊ መስመር አናግቶታል።
እንደ ኢትዮጵያ ያለችለ ባህር በር አልባ አገር ፣ የነዳጅ እና የግብርና ግብዓቶችን ለማግኘት በባህረ-ሰላጤው እና በጅቡቲ ኮሪደር ላይ ያላት ጥገኝነት፣ አገሪቱን ለዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት እና ለውጭ ምንዛሬ ጫና ተጋላጭ አድርጓታል።
የዚህ መናጋት ትልቁ ማሳያ በኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አጋር በሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ የታየው ተፅዕኖ ነው። ግዙፍ የኢነርጂ መሠረተ ልማት ያላት ኤምሬትስ እንኳን፣ የዶላር ፍሰትን ለማረጋገጥ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የገንዘብ ልውውጥ (currency swap) ውይይት መጀመሯ፣ በግሎባላይዜሽን ዓለም ውስጥ ማንም አገር ከቀውስ ነፃ አለመሆኑን ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል።
ነዳጅ የኢኮኖሚው ደም ስር ሲሆን፣ ማዳበሪያ ደግሞ የኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ማዕከል ነው። የእነዚህ ሁለት መሰረታዊ ግብዓቶች በአንድ ጊዜ መስተጓጎል ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ጫናም ጭምር ነው።
ይህንን ውጫዊ ጫና ይበልጥ ያከበደው ግን የአገር ውስጥ “የቤት ስራዎቻችን” አለማጠናቀቃችን ነው። በስርጭት ሰንሰለቱ ላይ የሚታዩ የአስተዳደር ጉድለቶች፣ የሙስና ጥርጣሬዎች እና በጅቡቲ ኮሪደር ላይ ያለው ከፍተኛ ጥገኝነት እና የዲመሬጅ መስተጓጎል የህዝብን እምነት እየሸረሸሩት ይገኛል። መንግሥት ከቀውሱ በፊት የጀመረው የነዳጅ ድጎማ ማንሳት እርምጃ ዳግም ቢጀመርም፣ ከዓለም አቀፉ የዋጋ ንረት ጋር ተዳምሮ በዜጎች ጫንቃ ላይ ከባድ ሸክም ሆኗል።
የወደፊት የጽናት ስልቶች (Strategies for Resilience)
የአጭር ጊዜ እሳትን ከማጥፋት ባለፈ፣ ኢትዮጵያ ዘላቂ የመቋቋም አቅም (Resilience) መገንባት አለባት፦
አፋጣኝ ምላሽ
የማዳበሪያ ስርጭትን በዲጂታል የክትትል ሥርዓት በማገዝ ያለምንም መስተጓጎል ለአርሶ አደሩ ማድረስ እና ለትራንስፖርት ዘርፉ ቅድሚያ የሚሰጥ የነዳጅ አመራር መከተል።
የምንጭ ብዝሃነት (Diversification) ማጠናከር
በአንድ የባህር መስመር እና በጥቂት የንግድ አጋሮች ላይ ያለን ጥገኝነት መቀነስ። የነዳጅና ማዳበሪያ አቅርቦት ምንጮችን ከሩቅ ምስራቅ እስከ ምዕራብ በማስፋት አደጋን መቀነስ።
መዋቅራዊ ሽግግር
የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶችን በማፋጠን የነዳጅ ፍጆታን መቀነስ እና የማዳበሪያ ምርትን በአገር ውስጥ ለመተካት የሚደረጉ ጥረቶችን እንደ ብሔራዊ ደህንነት ጉዳይ መመልከት።
ማጠቃለያ
የ“ሆርሙዝ” ቀውስ ለኢትዮጵያ የማስጠንቀቂያ ደወል ነው። ታሪክ እንደሚነግረን ታላላቅ አገራት የሚገነቡት በፈተና ውስጥ ጸንቶ በማለፍ ነው። የኢትዮጵያ ሰፊ የግብርና አቅም፣ ይህዝብ ብዛት እና ወጣት የሰው ኃይል ከችግሩ ለመውጣት ትልቅ ግብዓቶች ናቸው።
ይህንን አቅም ወደ ውጤት ለመቀየር ግን ብልህ፣ ግልጽ እና ብቃትን ማዕከል ያደረግ አመራር ያስፈልጋል። ቀውሱን ለማርገብ አሁንም ጊዜ አለን፤ ነገር ግን ይህ የዕድል መስኮት ሁሌም ክፍት ሆኖ አይቆይም። አሁን የምንወስዳቸው እርምጃዎች ኢትዮጵያ ከቀውሱ አገግማ ትወጣለች ወይንስ ተንበርክካ ትቀጥላለች የሚለውን ይወስናሉ።
***መሠረት ሚድያ ላይ የሚቀርቡ አስተያየቶች በሙሉ የፀሀፊዎቹ እንጂ የሚድያው አቋም እንዳልሆኑ ልናስታውስ እንወዳለን።
-መሠረት ሚድያ-


