(መሠረት ሚድያ)- የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የሪፐብሊካኖች የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ (GOP) አባላት በኢትዮጵያ በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት አርሲ ዞን ውስጥ ከ60 በላይ በሚሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸመውን ግድያና ጥቃት አስመልክቶ በዛሬው ዕለት መረጃ አጋርቷል።
ኮሚቴው በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈረው መልእክት “በኢትዮጵያ በክርስቲያኖች ላይ ያነጣጠረው ተከታታይ ጥቃት ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የሌለው ነው” ብሏል። ይሁንና ኮሚቴው በግጭቱ ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉም ወገኖች ከዚህ ጥቃትና ሁከት የሚጠበቁበትን እርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባና ድርጊቱን የፈጸሙ አካላትም ለሕግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት ማግኘት እንዳለባቸው ማሳሰቡ አነጋጋሪ ሆኗል።
አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ምዕመናኑ ሲገደሉ ግጭት ተቀስቅሶ ሳይሆን በመኖርያ ቤታቸው እንዳሉ መገደላቸውን በመግለፅ ላይ ይገኛሉ።
የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በዓለም አቀፍ ደረጃ አሜሪካ የምታደርገውን የውጭ እርዳታ፣ የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን፣ የብሔራዊ ደህንነትና የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮችን፣ የሰብዓዊ መብቶችንና የዴሞክራሲ ማረጋገጥ ሥራዎችን እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር (State Department) እና ከአሜሪካ ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (USAID) ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎችንና ሕጎችን የመከታተልና የመቆጣጠር ከፍተኛ ሕጋዊ ሥልጣን ያለው አካል ነው።
ኮሚቴው በጉዳዩ ላይ የሰጠው ይህ መግለጫ አሜሪካ በኢትዮጵያ ያለውን የሃይማኖት ነፃነት፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝ እና የንጹሐን ዜጎች ደህንነት ሁኔታ በቅርበት እየተከታተለችው መሆኑን የሚያሳይ መሆኑ እየተገለፀ ይገኛል።
የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ መግለጫ የወጣው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በአርሲ ዞን በንጹሐን ምእመናን ላይ የተፈጸመውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ በተመለከተ ዝርዝር መግለጫ መስጠቱን ተከትሎ እንዲሁም በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት የአሜሪካ ባለስልጣናት ጣልቃ እንዲገቡ ቅስቀሳ መጀመሩን ተከትሎ ነው።
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዳስታወቀው በኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ጥቅምት 10 እና 14 ቀን 2019 ዓ.ም በተፈጸመ ጥቃት በመርቲ ወረዳ አንጋዳ ቀበሌ (ልዩ ስሙ ጎራ ሲሊንጎ) 14 ምእመናን፣ እንዲሁም በሸርካ ወረዳ ጠሬታ ጮሌ ቢርቦ 46 ምእመናን፣ በአጠቃላይ ከ60 በላይ ንጹሐን በግፍና በጥልቀት ባደረ ጭካኔ ተገድለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ የ20 ምእመናን መኖሪያ ቤቶች ሙሉ በሙሉ የተቃጠሉ ሲሆን ከ20 በላይ የሚሆኑ ወገኖች ደግሞ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በሆስፒታል ሕክምና በመከታተል ላይ ይገኛሉ ብሏል።
ቅዱስ ሲኖዶሱ ባወጣው መግለጫ በአርሲ ሀገረ ስብከትና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ኦርቶዶክሳውያን ላይ የሚፈጸመው አሰቃቂ ጭፍጨፋ፣ መፈናቀል፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ገልጿል።
ድርጊቱ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠውን በሕይወት የመኖርና የመጸሐፍ መብት የሚጥስ፣ ከሃይማኖትና ከተፈጥሮ ሕገ-ሰብእና የወጣ፣ እንዲሁም የህዝቦችን ተከባብሮ የመኖር ዕሴት የሚያጠፋ እንደሆነ ጠቅሶ ምልአተ ጉባኤው በጽኑ አውግዞታል።
የመንግሥት የጸጥታ አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለምእመናን አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርጉና ወንጀለኞችን ለሕግ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርቧል።
| መሠረት ሚድያ |




በጣም ትክክል ናቸው
የሚሰማ ካለማ ጥሩ ነው