የአዲስ መሶብ አገልግሎት በአድሎአዊ ቅጥር እና በድብቅ በሚፈፀም ምደባ ቅሬታ ቀረበበት
- ተቋሙ በበኩሉ ቅሬታው ትክክለኛ እንዳልሆነ ገልፆ ስለ ሰራተኛ ቅጥር ሂደቱ ማብራርያ ለሚድያችን ሰጥቷል
(መሠረት ሚድያ)- በ2017 ዓ.ም በፌደራል ደረጃ በይፋ የተቋቋመው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልልና በከተማ አስተዳደር ደረጃ እንዲቋቋም በወረደው አቅጣጫ መሰረት በአዲስ አበባም የአዲስ መሶብ አገልግሎት ወደ ስራ እንዲገባ ተደርጓል።
መልካም አስተዳደርን ለማስፈን አስፈላጊ ነው የተባለው የመሶብ አገልግሎት በአዲስ አበባው ቅርንጫፉ በቅጥር ዙርያ ካሁኑ በርካታ ቅሬታ እየተነሳበት ይገኛል።
የአዲስ መሶብ አገልግሎት ለመለመላቸው ሰራተኞች ኦረንቴሽን በሰጠበት ወቅት በቀጣይ የመንግስትን አገልግሎት ወደዚህ ተቋም በመቀየር የክፍለ ከተማና የወረዳ ስራዎች ወደፊት ከስራ ውጭ ለሆኑ እንደሚችሉ ተጠቁሞ ነበር።
ይሁንና አንዳንድ ሰራተኞች በተቋሙ ውስጥ 'አሻጥር' እና 'የግለሰብ ፍላጎት የተጫናው አሰራር' አለ በማለት ለሚድያችን ተናግረዋል።
"ከተለያዩ ተቋማት ተመልምለን ለአዲስ መሶብ ስማችን ከተላለፈ በኋላ እንደገና የአዲስ መሶብ ተቋም ፈተና ተፈትነን ውጤት እንዳናውቅና በእነርሱ ፍላጎት ብቻ የፈለጉትን እየጠሩ ስልጠና እንዲገቡ አድርገዋል። አልፋችኋል ተብለን የተደወለልንም ወደ ስልጠና ሳንገባ ሳንጠራ ምንም እንዳልተፈጠረ ስራ ጀምረዋል" የሚሉት አንድ ቅሬታ አቅራቢ ናቸው።
"በመጀመርያ ከፈተናው ጀምሮ እስከ ምደባው የባለሙያ እና የቡድን መሪ ምደባው ላይ ከፍተኛ የሆነ የግልፀኝነት ችግር አለበት። በሁለተኛ ደረጃ ማንም መረጃ ሊሰጠን አልቻለም፣ በአካል የከተማው ፐብሊክ ሰርቪስም ብንሄድ መልስ የሚሰጥ የለም። ሲቀጥል ደግሞ ወደፊት በከተማ ደረጃ የአገልግሎት ሽግግር የሚደረግበት ይህ ተቋም የሰራተኛ ምልመላው በተቋም ሳይሆን በግለሰብ ደረጃ እየተደራጀ ነው" በማለት ጥቆማቸውን ለመሠረት ሚድያ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ ሌላ የመረጃ ምንጫችን አካታችነት በሚል ሰበብ የአዲስ አበባ ተወላጆች ከምደባ ውጪ እየሆኑ ነው ይላሉ።
"ፈተና ከተፈተንን በኋላ ውጤታችንን እንድናይ አልተፈቀደም፣ ብሄር ብቻ ነው መስፈርቱ። ምደባው በድብቅ ነው የተሰራው ስለዚህ የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ይጠየቁልን። ብልሹ አሰራርና ግልፀኝነትና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የተቋቋመ ነው የተባለው ይህ ተቋም ማንነትን መሠረት ያደረገ ቅጥር እየፈፀመ ነው። በአካታችነት ስም በተለይ ከአዲስ አበባ የሄዱ ምልምሎች በጣም መድሎ እየተደረገብን ነው" ብለዋል።
ይህን ጥያቄ ይዘን ሄደን የአዲስ መሶብ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተርን አቶ ዮናስ አለማየሁን ምላሽ ጠይቀናል።
አቶ ዮናስ አዲስ መሶብ ግልፅ የሆነ የቅጥር፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ያለው እና ዋና አላማውም ጥራት እና አስተማማኝ አገልግሎት ለደንበኞች መስጠት መሆኑን በማስረዳት ይጀምራሉ።
"ቅጥርን በተመለከተ ለተነሳው ቅሬታ ደግሞ የምንከተለው ከሀገሪቱ የፐብሊክ ሰርቪስ ፖሊሲ ጋር የተጣጣመ ነው። ይህ ፖሊሲ ደግሞ አካታች እና ከጾታ፣ ብሄር፣ ሀይማኖት እና አካል ጉዳተኝነት ወዘተን ታሳቢ አድርጎ ለሁሉም እኩል እድል የሚሰጥ ነው። አካታችነት ምርጫ ሳይሆን አስገዳጅ የውሳኔ አሰጣጣችን መመርያ ነው" ብለው ሂደቱን ያስረዳሉ።
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እና ከአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ የተመረጡ አዲስ ምሩቆች እንዲሁም ከተለያዩ ቢሮዎች የተውጣጡ ከፍ ያለ ልምድ ያላቸው ሰራተኞች ኦረንቴሽን ተሰጥቷቸው እንደነበር አንስተዋል።
ምልመላው የተስተካከለ እንዲሆን 50 ፐርሰንት ልምድ ካላቸው ሲኒየር ሰራተኞች፣ 50 ፐርሰንት ደግሞ ከአዲስ ምሩቆች እንዲሆን መደረጉን ያስረዱት አቶ ዮናስ የስራ መደቦችም በሶስት ቦታ፣ ማለትም በዜሮ አመት ልምድ፣ በሲኒየር ልምድ እና በቡድን መሪ መከፋፈሉን ተናግረዋል።
"ምደባው የተካሄደው በዚህ መሰረት ብቻ ነው። ስለዚህ የቀረቡት ቅሬታዎች ይህንን አሁን ያስረዳሁን መሬት ላይ ያለ የአሰራር ሁኔታ አያሳይም። እንደውም፣ በርካታ የአዲስ አበባ ተወላጅ የሆኑ ሰራተኞች ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ። እንዲህ አይነት ጉዳዮች ፖለቲካዊ ይዘት እንዲኖራቸው እና ሀቁን እንዲስቱ መደረግ የለባቸውም" ብለው የተቋማቸውን አቋም ለሚድያችን አጋርተዋል።
-መሠረት ሚድያ-




